Monday, 23 November 2020 00:00

“ከመደነጋገር መነጋገር”ን እንዳነበብኩት

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(0 votes)

 በአጋጣሚ ከእጄ የገባው “ከመደነጋገር መነጋገር” የተሰኘ  የዶ/ር ሳሙኤል ወልዴ የተግባቦት (የንግግር) መፅሐፍ  ውሎ አድሮ የተሰማኝን በቃላት እንድከትብ አስገድዶኛል፡፡ በእርግጥ ይህ ፅሁፍ ስለ መፅሐፉ የተሰማኝን አስተያየት በጥቂቱ ለመግለፅ ያህል እንጂ ጥልቅና ሙያዊ የሆነ ሒስ ለማቅረብ እንዳልሆነ አንባቢ እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ፡፡
መናገር ወይም ንግግር ቋንቋን መሠረት ያደረገ ሠብዓዊና አንደበታዊ የመግባቢያ ክህሎት ነው፡፡ይህ ክህሎት በህልውናችንና በኑሯችን ላይ ያለው ሚና ወደር የለሽ ነው፡፡ የህልውናችን መስፈሪያዎች ወይም ሚዛኖች ሁሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ የሚመሰረቱት በንግግር ችሎታችን ላይ ነው። ለዚህም ነው፤ዶ/ር ሳሙኤል ወልዴ፤ “...ንግግርም የማያቋርጥ የሕያውነት ምልክትና የማይታየው የምናቡ ዓለም ነጸብራቅ ነው” የሚለው (ገፅ 45)፡፡ እዚህ ላይ ንግግር ለሠብዓዊ ፍጡር ሁሉ የተሰጠ መለያ ባህሪው ነው፡፡
“ባህሪ ሁሉ ቋንቋ ነው! ...ሐሳብ የሚተረጎመው በቋንቋ ነው፡፡ የሚቀዳውና የሚንሸራሸረው በቃላት፣ በዝምታ፣ በድርጊትና ባለማድረግ ነው፡፡ የስውሩ ዓለም ጠሊቅ ምክር በአንደበት ቃል፣ በአቋቋም፣ በአቀማመጥ፣ በአካሔድ፣ በአስተያየት፣ በአይን አከፋፈት፣ አዘጋግ  ከአንዱ ወደ ሌላው ይተላለፋል፡፡ እንዲሁም በአብዛኛው እጅ፣ አንዱ ከአንዱ ጋር የሚነጋገረውና ሐሳቡን ለመግለጽ የሚወናጨፈው፣ቃላት አልባ በሆኑ የሰውነት ውዝዋዜዎችና የፊት ገጽታ ነው” (ገፅ 45)
የሐሳብና የስሜት ተራክቦ የሚደረግባቸው ስልቶችና መንገዶችን ዘርዘር ባለ ሁኔታ ያሰፈሩት የተግባቦትን ሂደትና አስቸጋሪነት ለማመልከትም ጭምር ይመስላል። በእርግጥ ጥያቄ የሚያስነሳ አሻሚ ጉዳይንም የያዘ አገላለፅ ነው፡፡ ምክንያቱም የተግባቦትንና የንግግርን እንዲሁም የሃሳብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን በግልፅና በማያሻማ መንገድ ማስፈር አልቻሉምና ነው፡፡
በመፅሐፉ “ስለ ስሜት” ሠፋ ያለ ትንታኔ ተሰጥቷል፤ማለትም ስሜታዊነት የሚያስከትላቸው ቀውሶች፡፡ ያም ሆኖ በአብዛኛው የሚያመዝኑት ወደ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነው፡፡
“...ስሜታዊነት ኅብረተሰብን ለተግባር “ሆ!” ብሎ በጅምላ ለማነሳሳት የማነቃቂያ ሞተር ቢሆንም በአግባቡ፣ በቅን ምክር ካልተቃኘ ግን የሚያስከትለው ጉዳት በደረሰ መስክ ላይ ከዘመተ የአንበጣ መንጋ አይተናነስም፡፡ የስሜት ፍንዳታ አይሎባቸው፣ ለመሰንበቻቸው የሚያዛልቅ ምክር አልሰማ ብለው ከትልቅነት ግባቸው የታቀቡ፣ የሌሎችን ተሞክሮ፣ ግራና ቀኝ በመቃኘት ትምህርት ሊቀስሙበት ይገባል። በስሜታዊነት ብቻ ሰክረው፣ በአየር ላይ ሲንሳፈፉ የከረሙ ግለሰቦች ዛሬ መሬት ላይ መውረድ ብቻ ሳይሆን አመድ ነስንሰው በቁጭት መነፍረቃቸው እሙን ነው” (ገፅ 35)
ፀሃፊው “ስሜት” እና “ስሜታዊነት”ን ቀላቅለው የገለፁባቸው በአንድ ከጨፈለቁባቸው አገላለፆች ውስጥ ከላይ ያሠፈርኩት “ጥቅስ” አንድ ማሳያ ነው። ለስሜት ያላቸውን የመረረ ጥላቻ ከመፅሐፉ መግቢያ እስከ መደምደሚያ (ማጠናቀቂያ ) ምዕራፎች ሁሉ በመረረ መንገድ ገልፀውታል፡፡ በእኔ እምነት ፅንፈኛ አቋማቸውን እንዲያንፀባርቁ ያደረጓቸው ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም በዋናነት ግን የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ወቅታዊው የሐገራችን ፖለቲካ ምስቅልቅልና ለውጡን ተከትሎ የመጡ አመፆች ቅጥ ማጣት ከስሜታዊነት የመነጩ በመሆናቸውና ስሜታዊነትን መግሪያው ብቸኛ መንገድ ምክንያታዊ ንግግር (ምክክር) ነው፤ ብለው ማመናቸው ናቸው፡፡
በእርግጥ “የመደነጋገር ዋናው ምክንያት አለመነጋገር ነው” የሚለው ሐሳብ ስለሚጎላ ለአጠቃላይ የተግባቦት ችግሮች መሠረታዊ የመፍትሔ ሐሳብ የሚጠቁሙ በርካታ ጭብጦችን መፅሐፉ አካትቷል፡፡ አለመነጋገር የሚያስከትላቸው ጉዳቶችም በዝርዝር ተጠቁመዋል፡፡ ለማሳያ ያህል የሚከተለውን እንመልከት፡፡
“አለመነጋገር መደነጋገርን ይፈጥራል። በቤተሰብ በኅብረተሰብ እንዲሁም በዜጎች መካከል ጥርጣሬን ያረባል ያራባል፡፡ በግልፅነት ካለመነጋገር የተነሳ በቤተሰብ በማህበረሰብ እንዲሁም በዜጎች ዘንድ ክፍተት ሲፈጠር፣ በሒደት ጥርጣሬ ይንሰራፋል፡፡ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ክፍተቶች፣ ትክክለኛው የመረጃ መንሸራሸሪያው እንዲስተካከል  ካልተደረገ፣ የማህበረሰቡ አባላት እንደገባቸው፣ ክፍተቱን ለማጥበብ መላምት እንዲመቱ ይገደዳሉ”  (ገፅ 36)
የትኛውም ግለሰብ ለሚገጥመው ችግር ስነልቦናዊና አካላዊ ቀውሱን ለመቋቋም በራሱ መንገድ መፍትሔ ይፈልግለታል። ሆኖም ግን እንደ ህብረተሰብ የጋራ ችግር በጋራ ለማስወገድ ወሳኙ መንገድ የጋራ ግንዛቤ መያዝ መሆኑም አጠያያቂ አይደለም። ስለሆነም እንደ ህብረተሰብ በርጋታ የመነጋገር ባህል ማዳበር የሚከተሉት ጥቅሞች እንዳሉት በመፅሐፉ ተጠቅሷል፡፡ እነሱም ፦
1. “በመነጋገር የጋራ አላማን ማስጠበቅ ይቻላል”፣
የህብረተሰብ መሠረቱ የጋራ ጉዳይ መቅረፅ ሲሆን የጋራ ዓላማ ደግሞ ከነቃ ተሳትፎ ይመነጫል፡፡ ስለሆነም በግልፅ የተመከረበት ሀሳብ፣ በጋራ የዳበረ ጉዳይ ሩቅ ለመራመድ ጉልበት አለው፡፡
2. በመነጋገር የጋራ ግንዛቤ ይፈጠራል እና
3. በመነጋገር ጥርጣሬና ሐሜት ይጠፋል የሚሉት ናቸው፡፡
በአጠቃላይ መፅሐፉ በስምንት ምዕራፎች የተዋቀረ ቢሆንም አቀማመጣቸው  ምክንያታዊ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ግን ለሐገራችን ወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ ነጥቦችን አካተዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1329 times