Sunday, 29 November 2020 16:18

"ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ እንግዲህ ታከተኝ"

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

  "ምን መሰላችሁ... እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... መገለባበጥ እኮ በሁሉ ነገር አለ፡፡ መገለባበጥ ማለት የሆነ ሚዛን ወዴት እንዳጋደለ አይቶ ሄዶ ልጥፍ ነው... በየጊዜው ማለት ነው፡፡--"
               
               እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ እንግዲህ ታከተኝ
የሆዴን ጠይቆ ማን ባሰናበተኝ…
እንግዲህ ላይፍ ‘ፌይር’ አለመሆኑን ቀጥሎበታል...እኛም ላይፍ ላይ ማማረሩን ቀጥለንበታል፡፡ “ምን ይሻላል፣ ምን ይበጃል...” ስትል የዘፈነችው ማን ነበረች?!... እናማ...አለ አይደል....“ምን ይሻላል፣ ምን ይበጃል...” የሚያስብሉ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ በ‘መደበኛዎች መንገዶች’ና በ‘አቋራጭ’ መንገዶች የሚሄዱት ታክሲዎች እኩል አልደርስ እያሉን ነው የተቸገርነው... አቆራራጮቹ መንገዱን ጎምደው፣ ጎምደው ቀድመው እየደረሱ፡፡
“ደርሰሃል እንዴ?”
“አይ በአራት ኪሎ በኩል ፒያሳ የሚሄደው ታክሲ ላይ ተሳፍሬ አሁን መናኸሪያን እያለፍን ነው፡፡ አንተስ?”
“በእሪ በከንቱ በኩል ፒያሳ የሚሄደው ታክሲ ላይ ተሳፍሬ እኛም መናኸሪያን እያለፍን ነው፡፡ እዛው እንገናኝ”
እናላችሁ... አሰባብራ የሄደችው የእሪ በከንቱዋ ታክሲ፣ ‘እሪ’ እያለች ፒያሳ ከች ስትል የአራት ኪሎዋ ገና ራስ መኮንን ድልድይ ነች፡፡
እናማ...ምን ለማለት ነው፣ ነገሮች እንዲህ እየሆኑ ነው የተቸገርነው... እኩል እየተነሱ አሳባባሪዎቹ ሲቀድሙ ቀጥ ብለው የሚሄዱት አጨብጭበው እየቀሩ፡፡
“ስማ፣ አሁን ምን እየሠራህ ነው?”
“ምን እየሠራህ ነው ማለት...”
“ማለት፣ ምን ሥራ ላይ ነው ያለኸው?”
“ያው በፊት የምሠራው ሥራ ላይ ነኛ! ምነው፣ የሆነ ኤንጂኦ ምናምን ልታስገባኝ አስበሀል እንዴ?!”
“አንተ ሰውዬ፣ አንተን ለማሰልጠን ስቶቭ ውስጥ ምናምን ከትተን በሦስት መቶ ሃምሳ ምናምን ዲግሪ ማብሰል አለብን! አሁን የኤንጂኦ ዘመን አይደለም፡፡ ትሰማኛለህ፣ አሁን ‘ዘ ሩል ኦፍ ዘ ጌም፣’ ተለውጧል፣ የጂምናስቲክ ዘመን ነው፡፡ ወይ ተገለባብጠህ ጂ ፕላስ ስሪ ቤትህን ገጭ ታደርግና አናቱ ላይ ፀሀይ እየሞቅህ ቡናህን ትጠጣለህ፤ ወይ መገለባበጡን የቻሉበት ይገለባብጡህና እየዞርክ “የምትከራይ አንዲት ክፍል ሰርቪስ ቤት ካለቻችሁ--” እያልክ ከተማዋን ስታስስ ትኖራለህ”
“ዌል እንግዲህ...” ያለው ማን ነበር፡፡ እናማ... ዌል እንግዲህ ‘መገለባበጥ’ ይህን ያህል “ሠላሳ ምናምኑ የስኬት ምስጢሮች” ምናምን ለሚል መጽሐፍ ርእስነት የሚበቃ ከሆነ፣ መደበኛ ስልጠና የማይዘጋጅሳ! የአስራ ምናምን የውጭ ቋንቋዎች አስራ ምናምን ኮርሶች ከምንወስድ አንዲትዬ የ‘መገለባበጥ’ ኮርስ ቢሰጠን አሪፍ ነው። አንዴ ጂ ፕላስ ስሪ ላይ ከተደረሰ በኋላ ‘የቋንቋዎች ሁሉ እናት’ ብርዬዋ ትሆናለቻ!
ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ እንግዲህ ታከተኝ
የሆዴን ጠይቆ ማን ባሰናበተኝ…
ነው የዘንድሮው ነገር፡፡
“ጌታው እኔ የቀኑ ላይፍ መስመር በያዘልኝ እላለሁ፣ አንተ ጭራሽ ተገልበጥ፣ ተከርበት ትለኛለህ!”
“አየህ ምን አልኩህ፣ አንተ ስቶቭ ውስጥ ከተውህ እንደ አሮስቶ ቢያሽከረክሩሀም የምትበስል አይደለህም፡፡ እኔ እየነገርኩህ ያለሁት ሪያሊቲውን ነው፡፡ ምሳሌዎች ልስጥህ እንዴ!”
“ምን አይነት ምሳሌዎች?”
“እነማን ተገለባብጠው እላይ እንደደረሱ የስም ዝርዝራቸውን...”
“ቆይ፣ ቆይማ ዝርዝሩን ተወው፡፡ ‘ይሄ ሰውዬ ትክ ብሎ የሚያየኝ ለምንድነው’ የሚል በበዛበት ጭራሽ ልታነካካኝ...”
እናላችሁ... የተሳካለት እያጨበጨበ “እሽከም እናኑ...” ሲል… ያልተሳካለት በቁጭት አጨብጭቦ ሲቀር…ነገርዬው “ምን ታደርገዋለህ?” አይነት ነው፡፡
የሆነ ህግ እንኳን ባይሆን በሰርኩላር ነገር...“የትናንቱን መተንተኑን ለታሪክ ጸሀፊ ተዉትና ይልቁንም ስለሚመለከትህ ዛሬ አውራ; የሚባል ሰርኩላር ቢተላለፍልን፤ እኛም አንድ ጊዜ ከመቁረጣችን በፊት ሁለት ጊዜ መለካቱን እንለማመድ ነበር፡፡
እናላችሁ... ስለ ታሪክ ካነሳን አይቀር ምን ይመስለኛል መሰላችሁ....ወደፊት የሆነ መጽሐፍ መደብር ሄዳችሁ “የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ይኖራችኋል?” ስትሉ መልሱ ምን ሊሆን ይችላል መሰላችሁ.... “እነማን የጸፉትን?” ወይ ደግሞ የሚሸጥላችሁ ትንሽ ‘ነገር የገባው’ የሚባል፣ ከምሽቱ ሦስት ሠዓት በድቅድቅ ጨለማ ጥቁር የፀሀይ መነጽር የማያደርግ (ቂ...ቂ...ቂ...) ከሆነ ወደ ጆሯችሁ ጠጋ ብሎ “የታሸገውን ኦሪጂናሉን ነው የምትፈልገው ወይስ የ‘አውርድልኙ’ን ነው? (ቂ...ቂ...ቂ.... የምትለዋን ደግመናታል።)
በዛ ሰሞን ስለ አገራችን የሆነ የቀድሞ ዘመን ‘የታሪክ ክስተት’ ትንታኔ ስትሰጠኝ የነበርከው ወዳጄ... የፈጠራ ችሎታህ አድናቂ ነኝ፡፡ ግን ፊልሙን መቼ ነው የምናየው! ቂ...ቂ...ቂ...  እናማ የታሪክ ትንታኔ የሆነ መገላባበጥ ነገር ሆኖላችኋል፡፡
ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ እንግዲህ ታከተኝ
የሆዴን ጠይቆ ማን ባሰናበተኝ…
ነው የዘንድሮው ነገር፡፡
እናማ...  የሆዳችንን የሚጠይቀን ቢኖር ስንቱን ነገር በዘረገፍን ነበር፡፡ ልክ ነዋ.... “እንዴት ነው እኛ በአስራ አምስትና በሀያ አምስት ዓመት ያልሆነልንን፣ አንዳንዱ በአስራ አምስት ቀንና በወር ከአስራ አምስት ቀን የሚሳካለት?” ብለን እንጠይቅ ነበር... የሚሰማን ከተገኘ ማለት ነው፡፡ እናማ... እዚህ ላይ ነው ‘መገለባበጥ’ የሚሏት ነገር የምትመጣው፡፡ አስራ አምስት ዓመት እንደ እነ እንትና ግቢ እድሜ—ጠገብ ዛፍ ተገትሮ የኖረና ወር ከአስራ አምስት ቀን እንደ ኦሎምፒክ ጂምናስቲከኞቹ የተገለባበጠ ማረፊያቸው እኩል እንዲሆን ተፈጥሮም መፍቀዷን እንጃ!
ምን መሰላችሁ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...  መገለባበጥ እኮ በሁሉ ነገር አለ፡፡ መገለባበጥ ማለት የሆነ ሚዛን ወዴት እንዳጋደለ አይቶ ሄዶ ልጥፍ ነው... በየጊዜው  ማለት ነው፡፡
ስሙኝማ... ምን የሚባል ነገር አለ መሰላችሁ... “ብድር መውሰድና እንግሊዝኛ መናገር የሚፈልገው ድፍረት ብቻ ነው፡፡” አሪፍ አይደል! የምር እኮ ነው...
እኛም እንላለን ለመገለባበጥ የሚፈለገው እውቀት፣ የአስተሳሰብ ምጥቀት ምናምን ሳይሆን ድፍረት ብቻ ነው፡፡
“መገለባበጥና የጦቢያ ቦተሊካ” የሚል መጽሐፍ ይጻፍልንማ፡፡ ምን አለ በሉኝ ‘ኒውዮርክ ታይምስ ቤስትሴለር’ ምናምን ሊስት ላይ ዓመት ከዘጠኝ ወር በመሪነቱ ስፍራ ላይ ባይቆይ፡፡ ደግሞም በአርባ ምናምን የዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ባይተረጎምና ሆሊዉድ የፊልም መብቱን ለመግዛት ሚሊዮኖች ‘ዶላሬውን’ ቁጭ ባያደርግ! አሀ...ለሌሎች ትምህርት ይሰጣላ!
ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ እንግዲህ ታከተኝ
የሆዴን ጠይቆ ማን ባሰናበተኝ…
ነው የዘንድሮው ነገር፡፡
“ተገለባብጠህ ጂ ፕላስ ስሪ ቤትህን ገጭ  አድርገህ...” ምናምን ያልከኝ ወይም ልትለኝ ያሰብከው ወዳጄ...‘ኢን ፕሪንሲፕል’ ባልከው ባልስማማም እስቲ እንመከርበትና...ማን ያውቃል፣ ‘ኮንቪንስ’ አድርገኸኝ ‘ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ...’ ከማለት ትገላግለኝ ይሆናል! (ቂ...ቂ...ቂ...)
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1914 times