Monday, 30 November 2020 00:00

የሕወሓት መወገድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለው አንደምታ?!

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

 ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ
በሕወሓት እና በማእከላዊው መንግሥት መካከል፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተከስቶ የነበረው መገፋፋት፣ በታሪክ አጋጣሚ ከተፈጠረ ኹነት ጋር ኩታ ገጠም ነው። ከደርቡሽ ጋር ጦርነት ገጥመው መተማ ላይ የተሰውት ዐፄ ዮሐንስን ተከትሎ፤ ትግራይ ላይ የሥልጣን ክፍተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በሌላው የሀገራችን ክፍል ግን፤ የሸዋው ንጉሥ ዐፄ ምኒልክ ኃይላቸውን አደራጅተው ይጠባበቁ ስለነበር፤ ዙፋኑን ለመረከብ ብዙም አላዳገታቸውም፡፡
የትግራዩ ራስ መንገሻ የንጉሠ ነገሥትነቱ ሥልጣን፣ ለእርሳቸው እንደሚገባ በመወሰን፤ የዐፄ ምኒልክን ንግሥና እውቅና ነፈጉት፡፡ ምንም እንኳን፤ እኚህ የጦር አበጋዝ ዐፄ ምኒልክን የሚቋቋሙበት አቅም ባይኖራቸውም፤ ትግራይን የሙጥኝ ብለው ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን፣ ማንገራገራቸው አልቀረም፡፡ ይህንን የተረዱት ዐፄው፣ ጥቂት ጊዜ ከመከሩ በኋላ ትግራይን በጉልበት ወደ መሀል የሚጠቀልሉበትን ቀን ጠብቀው፤ ቁርጡ ቀን ሲደርስ ወደዚያው ዘመቱ። ራስ መንገሻ በያዙት አቋም ቢቀጥሉ፣ ሊደርስባቸው የሚችለውን አይቀጡ ቅጣት አስቀድሞ በመገንዘብ፣ አንዲት ጥይት ሳይተኩሱ ለምኒልክ ገቡላቸው፡፡
ይህንን በተመለከተ፣ በተክለጻዲቅ መኩሪያ #ዐፄ ሚኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት; የታሪክ ድርሳን ላይ በገጽ 34 እንዲህ ሰፍሮ እናገኛለን፣
“ንጉሠ ነገሥቱ የካቲት 20 ቀን ከመቀሌ ተነሥተው በማይመክዳን፣ በአጽቢ እንዳሥላሴ፣ በአጽቢ ደራ፣ በጸዓዳ አምባ አልፈው ሐረማት በተለይ አጉዴ ከሚባለው ቀበሌ ሰፍረው ሳለ፣ ሲላላኩ የቆዩት ራስ መንገሻና ራስ አሉላ የመቃወም ጉዳይ እንደማያወጣ በመንገዘብ መጥተው እጅ ነሥተው ገቡላቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ስለ ክብራቸው ጠመንጃ፣ መድፍ እየተተኮሰላቸው በደስታ ተቀባሏቸው፡፡”  
እንግዲህ፤ የለውጡ አስተዳደር፣ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት፣ ከሕወሓት ጋር የገባው ግጭት፤ በተወሰነ ደረጃ በዐፄ ምኒልክ የመጀመሪያ የንግሥና ዘመን ላይ ከተከሰተው መቃቃር ጋር የመመሳሰል ጠባይ ነበረው፡፡ ሕወሓት ግን፤ በዛ ዘመን ከነበረው ሽኩቻ በከፋ ሁኔታ ብዙ ርቀት የሄደ ሽብርተኛ ድርጅት ነው፡፡
ከአፈጣጠሩ ጀምሮ፣ የለመደውን የክህደት ተግባሩን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ለመድገም ምንም አላቅማም። ይኽንን ክህደት፣ እንደ ትልቅ ጀብድ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ወጥተው የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ መስክረዋል፡፡ መንግሥት፣ ድርጅቱን ለመደምሰስ ከበቂ በላይ ምክንያት አግኝቷል፡፡ ለመሆኑ፤ የዚህ ጠንቀኛ ድርጅት መሞት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የሚኖረው አንደምታ ምንድን ነው?
ሕወሓት እና የዘውጌ ፖለቲካ
ሕወሓት፣ ለአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ያለው ፍቅር ከልክ በላይ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች፣ ሰፊውን የኦሮሞ ማኅበረሰብ የማይመጥን፣ የሰለባ ትርክትን በማስተጋባት፤ ለሕዳጣኑ ድርጅት እድሜ ሲቀጥሉ የኖሩ ናቸው፡፡ የሀገረ መንግሥቱን አፈጣጠር የሚበይኑበት መንገድ፣ የሕወሓት ግልባጭ ነው፡፡ ሁለቱም ኃይሎች በጋራ ሲቆምሩ የኖሩት፣ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ የሚገኘውን በረከት ነበር፡፡
የኦሮሞ ብሔርተኛነትን በኢ-መደበኛ አደረጃጀት ሲያቀጣጥል የነበረው ቄሮ የተባለው የወጣቶች ስብስብ፤ አሁን  ከሞላ ጎደል ሰክኗል፡፡ ኦሜን የተባለው የፕሮፓጋንዳ ማሽን፣ ከጨዋታ ውጪ መሆን፤ የእነ ጃዋርና ሌሎች አክራሪ ኃይሎች ወህኒ መውረድ፣ በአደረጃጀቱ ላይ የቆመው አክራሪነት ለመከስም አንድ ሐሙስ እንዲቀረው ምክንያት ሆኗል፡፡
ቄሮ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ ሲፈጽመው የነበረው ዘግናኝ ጥቃት፤ ለሕወሓት ሰዎች ሰርግና ምላሻቸው ሆኖ ቆይቷል። ከንጹሐን ዜጎች የመስዋዕት በግ መሆን ጀርባ፣ የድርጅቱ ረጀም እጅ አለ። አሁን ወደ ወህኒ የተወረወሩት ግለሰቦች፣ የሕወሓትን ቡራኬ ለማግኘት ወደ መቀሌ መለስ ቀለስ ማለታቸውን ስናስታውስ፣ የነገሮችን ተያያዥነት ለማስላት እንገደዳለን። የድርጅቱ መሞት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ በኦሮሚያ ክልል ብልጭ ድርግም የሚለውን የአክራሪዎች ጥቃት እንደሚያዳክመው እሙን ነው፡፡
የሕወሓትን ማሸለብ ተከትሎ፣ በቆየው በኦነግ የሰለባ ትርክት የቆረቡ ሹማምንቶች፣ በኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ይጠፋሉ ማለት ግን የዋህነት ነው፡፡ ግለሰቦቹ አሁንም ችግር መፍጠራቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ጽንፈኛ ግለሰቦች  ወደ መሀል ፖለቲካ በመጣው በአብዛኛው የኦሮሞ ልሂቃን እንደ ሰም መቅለጣቸው ግን አይቀርም። የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኛነት ወታደራዊ ክንፍ፣ ኦነግ ሸኔ፣ ከሞላ ጎደል እያከተመለት ነው። ደጋፊው፣ አልባሽ አጉራሹ ሕወሓት፤ #ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጪ; ሆኖ በሞት አፋፍ ላይ ይገኛል፤የጣር ድምጽ በማሰማት ላይ ነው፡፡
የሕወሓት እና የአማራ ብሔርተኝነት ግንኙነት ፀጉረ ልውጥ ነው፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት አፈጣጠር፣ እንደ ሌሎች የዘውግ ድርጅቶች ከውስጥ በፈለቀ /ፕሮአክቲቭ/ ኡደት ሳይሆን፤ ለተፈጠረው ጽንፈኝነት እንደ ምላሽ /ሪአክቲቭ/ ሆኖ ነው ብቅ ያለው፡፡ በአጠቃላይ፤ ጽንፈኛው ድርጅት በአማራው ማኅበረሰብ ላይ ያደረሰውን ክልክ በላይ ግፍን ለመመለስ የበቀለ አጸፋዊ የፖለቲካ ንቅናቄ ነው። በተለይ፤ በወልቃይትና ራያ ሕዝብ ላይ ሕወሓት ላለፉት ሁለት ዐስርት ዓመታት ያዘነበው መከራ፤ ለአማራ ብሔርተኝነት መወለድ እንደ ምክንያት የሚቆጠር ነው ቢባል፤ ከእውነታው ጋር መጋጨት አይሆንም፡፡
ከሕወሓት ውድቀት በኋላ፤ የለውጡ አስተዳደር በእነዚህ ሥፍራዎች ላይ የሚያሳልፈው ውሳኔ፣ በሥርዓቱም ሆነ በሀገሪቱ መጻኢ እድል ላይ ግዙፍ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ ድርጅቱ ተምኔታዊቷን ትግራይ ሪፐብሊክን በሁለት እግሯ ለማቆም፤ ከጎንደርና ከወሎ ጠቅላይ ግዛት ቆርሶ የወሰዳቸው፤ በ1984፣ ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ ቀደም ብሎ ነው። እነዚህን ግዛቶች በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለመፍታት መሞከር፣ አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታን መጫወት ነው የሚሆነው። ግዛቶቹ ወደ ቀድሞ  ሥፍራቸው ተመልሰው፤ መሬት ላይ ያለው ሕዝብ፣ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ሥልጣን ሊጠበቅለት ይገባል፡፡
ምናልባትም፤ ጉዳዩን ፖለቲካዊና ሕጋዊ ልባስ ለማላበስ የድንበርና ማንነት ኮሚሽንን ምክረ ሐሳብ እንደ ግብአት መጠቀም ይቻላል፡፡ ግዛቶቹ ወደ ነባር ይዞታቸው ይመለሱ ማለትና  አሁን ያለውን ፌዴራላዊ ሥርዓት መደገፍ ማዶ ለማዶ መሆናቸው እዚህ  ጋ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይኽ ሁኔታ፤ በተገቢው መልኩ ምላሽ ካገኘ፣ ሌላ ሕልውናን የሚቀናቀን ጽንፈኛነት አደጋ ሆኖ ካልመጣ በስተቀር፤ የአማራ ብሔርተኝነት ዝግመተ ለውጡን ጨርሶ ይሞታል፡፡
ሕወሓት እና ሕገ መንግሥቱ
ሕገ መንግሥቱን የብሔር ብሔረሰቦች የቃል ኪዳን ሰነድ ነው የሚለው የሕወሓት ማጭብረበሪያ፤ ላለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ተላላ ሲያደርግ ኖሯል፡፡ በርግጥም፤ ሰነዱን ልብ ብለን ከመረመርነው የሕወሓት እንጂ የብሔር ብሔረሰቦች ቃል ኪዳን አይደለም። ገና ከመንደርደሪያው፤ ኢትዮጵያን ሉአላዊ ሀገሮች /ዲፋክቶ ስቴትስ/ ተማምለው የፈጠሯት አገር እንደሆነች አድርጎ ነው የደነገገው፡፡ ይኽ ደግሞ፤ ድርጅቱ በበረሃ በ1968 ማኒፌስቶው፣ ታላቋን ትግራይ የመመስረት ሕልም ግልባጭ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ይሕንን የአንድ ጠባብ ማኅበራዊ መሠረት ያለው ድርጅት የፖለቲካ ፕሮግራም ቅጂ የሆነን ሰነድ ለማሻሻል በሚደረግ ትግል ውስጥ የድርጅቱ መውደቅ ተጨማሪ ኃይል ይሆናል፡፡
የልዩ ኃይል ዕጣፈንታ
ከሕገ መንግሥቱ ማእቀፍ ውጪ የተደራጀው ልዩ ኃይል፣ ውሎ አድሮ፤ የሀገሪቱን ሉአላዊነት ጥያቄ ውስጥ ይጥላል ብለው የሰጉ የፖለቲካ ታዛቢዎች በርካቶች ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ወደ ኮንፌዴሬሽን ያደላ ወይም ትንሽ ማእከላዊ መንግሥትና ፈርጣማ የክልል መንግሥታትን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ማሳያው፣ የዚህ ወታደራዊ ክንፍ /ፓራሚሊተሪ/ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበት መሄድ ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ለቁጥር የሚታክት ልዩ ኃይል በየጊዜው ቢያስመርቅም፤ በጉሊሶ፣ በዶዶላ፣ በሻሸመኔ ንጹሐን ዜጎች የመስዋዕት በግ ሲሆኑ ሊደርስላቸው አልቻለም፡፡ በክልሉ እንደ ልቡ የሚፈነጨውን ኦነግ ሸኔን አክርካሪ ለመስበር ብዙ ጊዜ ወስዶበታል፡፡ ይኽን ሁሉ የሀገሪቱን በጀት እየበላ፣ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ያልቻለ ልዩ ኃይል ምን ሊፈይድ ነው? ተብሎ ከየአቅጣጫው ሒስ ሲዘነርበት ቆይቷል፡፡ በአንጻሩ፤ የአማራ ልዩ ኃይል በሰሞኑ ምስቅልቅል ላይ የተጫወተው ሚና፣ ብዙዎች ስለ ጸጥታ አወቃቀሩ ቆም ብለው እንዲያስቡ አስገድዷቸዋል፡፡
ጽንፈኛው ሕወሓት፣ በምእራቡ ግንባር የሰነዘረውን የሽብር ጥቃት በመመከት ረገድ፤ ልዩ ኃይሉ የፈጸመው ጀግንነት ለታሪክ የሚቀመጥ ነው፡፡ ለመከላከያ ኃይል፣ በየግንባሩ ደጀን በመሆኑ ብዙ ጥፋቶችን ታድጓል፡፡ በዚህም ምክንያት፤ ይኽንን የጸጥታ ክንፍ ዳግም የማዋቀር ትልቅ የቤት ሥራን ትቶ አልፏል፡፡ በአግባቡ ከያዙት ሀገርንም ሆነ ወገንን መታደግ ይችላል፡፡ ከመከላከያ ሰራዊት በታች፣ ኅብረ ብሔራዊ በሆነ አደረጃጀት፣ በየክልሉ የሚፈጠሩትን የጸጥታ ችግሮች የሚፈታ ተወርዋሪ ኃይል ሆኖ፤ እንደገና ቢዋቀር ፋይዳው ለሀገር አንድነት የላቀ ይሆናል፡፡
የግርጌ ማስታወሻ
የሕወሓት መውደቅ፣ ለሀገራችን ፖለቲካ የሚያበረክተው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ይኽ፤ የዘውጌ ፖለቲካ የአድባር ዛፍ መገንደስን ተከትሎ፤ በአምሳሉ የተፈለፈሉት ደንገጡሮች እስትንፋስ መቆራረጥ ይጀምራል፡፡ በየክልሉ ያሉት ጽንፈኛ ብሔርተኞች አቅም ሲከዳቸው፣ አፋፍሶ ጉልበት የሚቀጥልላቸው ይህ የሽብር ድርጅት ነበር፡፡ ከሕወሓት ማሸለብ ጋር ጽንፈኝነት አብሮ ይጠወልጋል። አክራሪነት እየለዘበ በምትኩ የሐሳብ ፖለቲካ ሥፍራውን ይረከባል፡፡ መንግሥት ከወታደራዊው ዘመቻ በኋላ ስለ ድርጅቱ ዕጣ ፈንታ ቆም ብሎ ማጤን ይጠበቅበታል። ሕወሓት፤ እንደ ሞሶሎኒ ፋሽስትና እንደ ሂትለሩ ናዚ ፓርቲዎች፣ህልውናው በሕግ መጥፋት ይኖርበታል፡፡

Read 2205 times