Saturday, 05 December 2020 17:23

የፌደራልና የክልል መንግስታትን ግንኙነት በህግ የሚወስን አዋጅ ፀደቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው፤ ከሶስት ዓመታት በፊት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውና በፌደራልና በክልል መንግስታት መካከል የሚኖረውን የግንኙነት ስርዓት ለመወሰን የሚያስችለውን ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ የህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በሚመለከታቸው አካላት በጥንቃቄ ሲታይ ቆይቷል።
ሁሉም የክልል መንግስታት ከፌደራል መንግስታቱ ጋር በመሆንና አቅማቸውን በማቀናጀት ህጋዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም ህዝቦች እኩል የሆነ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የግንኙነት ስርዓት መዘርጋት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል። የፌደራል መንግስትና የክልል መንግስታት በተናጠልና በጋራ  የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር በግልፅ በማስቀመጥ፣ አገራዊ የልማት ስራዎችን በተናበበ መልኩ መስራት እንደሚገባቸውም ተመልክቷል።
በአገሪቱ ቀደም ሲል የነበረው የአንድ ፓርቲ ስርዓት የመንግስት ስራ በህግ አግባብ ሳይሆን በመንግስታቱ በጎ ፍቃድ ብቻ እንዲመራ ሲያደርግ መቆየቱንና ይህም በፌደራልና በክልሎች መካከል የተናበበ ውጤታማ ስራ እንዳይሰራ ሲያደርግ መቆየቱም ተወስቷል።
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ከዚህ ቀደሞ ሲያወጣቸው ከነበሩ ህጎች በተለየ ጊዜ ወስዶ በከፍተኛ ጥንቃቄ ማየቱን የገለጹት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በቂ የሆነ ውይይት ካደረጉበት በኋላ ያፀደቁት መሆኑንም ተናግረዋል።

Read 949 times