Saturday, 05 December 2020 17:45

በአዲስ አበባ በየዕለቱ 4 ሰዎች በኤች.አይ.ቪ ይያዛሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 በአዲስ አበባ ከተማ  የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎችን ቁጥር 110 ሺ እንደሚጠጋና በከተማዋ በየዕለቱ 4 ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙ መረጃዎች ጠቁመዋል።
በከተማዋ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል 67 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች መሆኑንና ይህም በሽታው ወጣቱን የማህበረሰብ ክፍል በእጅጉ እያጠቃ መሆኑን አመላካች ነው የሚለው የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ መግለጫ በየዓመቱም ከ1800 በላይ ሰዎች በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ አመልክቷል::
የአዲስ አበባ ኤች አይቪ ኤድስ የመከላከያና የመቆጣጠሪያ ፅ/ቤት፣ አለም አቀፉን የኤች አይቪ ቀን አስመልክቶ ሰሞኑን ባወጣው መረጃ በየዓመቱ ከ1400 የሚልቁ ሰዎች በበሽታው የሚያዙ ሲሆን 1800 የሚሆኑት ደግሞ ይሞታሉ፡፡
የፅ/ቤቱ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ወ/ሮ ፈለቀች አንዳርጌ በዚሁ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ባለፋት ሶስት ዓመታት በበሽታው የሚያዙና ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥራቸው  እንደቀነሰ ቢናገሩም አሳሳቢነቱ እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡
ፅ/ቤቱ ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው፤ በበሽታው ሕይወታቸውን ከሚያጡት ሰዎች መካከል 62% የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ምክንያቶቻቸው ደግሞ ድህነት፣ ተገዶ መደፈርና ያለ ዕድሜ ጋብቻም እንደሆነ ጥናቱ ጠቁሟል። በቫይረሱ ይበልጥ የሚጠቁት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የኤች አይቪ ኤድስ በከፍተኛ መጠን ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል አዲስ አበባ ከተማና ጋምቤላ ክልል ዋንኞቹ ሲሆኑ ከሶማሌ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልል በስተቀር ሁሉም ክልሎች በበሽታው ወረርሽኝ ውስጥ እንደሚገኙ የፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት አመልክቷል።
በአገሪቱም በየዓመቱ ከ28 ሺ በላይ ዜጎች በበሽታው እንደሚያዙና ከ11 ሺ የሚበልጡት ደግሞ በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Read 870 times