Saturday, 05 December 2020 17:49

አትሌት ኃይሌ በሆቴል አገልግሎት ላይ ለመከላከያ ሰራዊቱ የ25 በመቶ ቅናሽ አደረገ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ በሆቴልና ሪዞርቶቹ ለሚስተናገዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሙሉ የ25 በመቶ ቅናሽ ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን ሌሎች ባለሀብቶችም ተመሳሳይ የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ  አህመድ ሰሞኑን በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፤ ዜጎች የሃገር ዳር ድንበር ጠባቂ ለሆነውና የመከላከያ ሰራዊት ተገቢውን ክብር እንዲሰጡ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ አትሌት ኃይሌ ለእድሜ ልክ የሚዘልቅ የ25 በመቶ የአገልግሎት ዋጋ ቅናሽ ለማድረግ ቃል የገባ ነው። የናሁ ቴሌቪዥን እንዲሁም የጎልደን ኮፊ፣ የጎልደን ሮያል ሆቴልና የጉዞ አስጐብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራውም  በሁሉም አገልግሎቶች ላይ ለመከላከያ ሰራዊት የ25 በመቶ ቅናሽ ለማድረግ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
የባለሀብቱ የአቶ ቴዎድሮስ ንብረት በሆነው “ጉዞ ጐ” በኩል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሃገር ውስጥ በረራ መስተንግዶ ለሚፈልጉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የ25 በመቶ ቅናሽ እንደሚያደርጉ በሆቴልና በሌሎች አገልግሎቶች ላይ ደግሞ እስከ 25 በመቶ ቅናሽ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት እስከ ዕድሜ ልካቸው የሻለቃ ሃይሌና የአቶ ቴዎድሮስ ድርጅቶችን አገልግሎቶች በቅናሽ እንደሚያገኙም ተገልጿል፡፡
የቅናሽ አገልግሎቶችን ለማግኘት መታወቂያ ብቻ ማሳየት በቂ  ነው ተብሏል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ለአገሩ ዳር ድንበርና ሉአላዊነት  የህይወት መስዋዕትነት ለሚከፍለው የመከላከያ ሰራዊት ዜጎች ክብር እንዲሰጡ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ፣ሌሎች ተቋማት ተመሳሳይ የዋጋ ቅናሽ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አንድ የት/ቤት ባለቤት በበኩላቸው ለወታደር ልጆች ነፃ የትምህረት እድል እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በትግራይ የህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚደረገው ድጋፍም የቀጠለ ሲሆን የነፃነት ታጋዩ አንዳርጋቸው ፅጌ በቅርቡ ለንባብ ካበቁትና ባለፈው ቅዳሜ ከተመረቀው “የታፋኙ ማስታወሻ” መፅሀፍት ሽያጭ ላይ የ100 ሺ ብር ስጦታ ለሰራዊቱ አበርክተዋል፡፡  

Read 758 times