Saturday, 05 December 2020 17:46

የነፃነት ታጋዩ አንዳርጋቸው ፅጌ ለመከላከያ የ100 ሺህ ብር ድጋፍ አደረጉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የቀድሞ  የ”ግንቦት 7” ዋና ፀሃፊ ፖለቲከኛና የነፃነት ታጋይ  አንዳርጋቸው ፅጌ በቅርቡ ለንባብ ካበቁትና  ባለፈው ቅዳሜ በጊዮን ሆቴል ከተመረቀው “የታፋኙ ማስታወሻ” የተሰኘ መፅሃፋቸው ሽያጭ የተገኘውን 100ሺህ ብር ለመከላከያ ሰራዊት ለግሰዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ድጋፉን ከትናንት በስቲያ ለመከላከያ የውጭ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ብ/ጀነራል ቡልቲ ታደሰ ያስረከቡ ሲሆን ድጋፉ ጉዳት ለደረሰባቸው ወታደሮች ቤተሰብ ይውላል ብለዋል።  በድጋፉ ርክክብ ወቅት ንግግር ያደረጉት አቶ አንዳርጋቸው፤በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ በህወሃት የተፈጸመው አሳዛኝ በደል ታሪክ ይቅር የማይለው መሆኑን ገልፀው በድርጊቱ በእጅጉ ማዘናቸውን ተናግረዋል።
ጥቃቱ በሟችና አካላቸው በጎደለ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ችግርና መከራ እንደሚፈጥር ስለሚታወቅ “ከጐናቸው ነን” ለማለት ድጋፉን ማበርከታቸውን  የገለፁት  አቶ አንዳርጋቸው፤ ሌሎችንም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በ2006 ዓ.ም ከየመን ሰነዓ በህወሃት ደህንነቶች ታፍነው ለ4 ዓመታት በከባድ እስር ላይ የቆዩት የነፃነት ታጋዩ፤ “የታፋኙ ማስታወሻ” የተሰኘው መፅሀፋቸው ከታፈኑበት ጊዜ አንስቶ ከእስር ተፈተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እስከተገናኙበት ድረስ ያለውን ታሪክ ያስቃኛል፡፡

Read 876 times