Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 04 August 2012 13:09

“ትክክለኛው የማህጸን ቅርጽ...”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ከላይ የምትመለከቱት ስዕል የማህጸን ቅርጽ ነው። ማህጸን በተፈጥሮው የምትመለከ ቱትን ስእል ሲመስል አንዳንድ ገዜ ግን የተዛባ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ያጋጥማል። ለመሆኑ ማህ ጸን በመጀመሪያ ሲፈጠር በምን መልክ ነው? የሚከሰተው ተፈጥሮአዊ ችግርስ ምን መሳይ ነው? መፍትሔ ውስ? እነዚህን ጥያቄዎች ይዘን ያመራነው በቀድሞው አጠራሩ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በአሁን ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ነው። በሆስ ፒታሉ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አብዱልፈታህ አብዱልቃድር አብዶሽ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች መልሰውልናል። የአምዱ አዘጋጆችም ለንባብ አቅርበነዋል።

ኢሶግ፡ ማህጸን የሚባለው የሴቶች የስነተዋልዶ አካል አፈጣጠር ምን ይመስላል?

ዶ/ር አብዱልፈታህ፡ ማህጸን ሲፈጠር ከመጀመሪያውኑ የራሱ ሂደቶች አሉት። እነዚያ ሂደቶች ትክክለኛውን የማህጸን ቅርጽ እንዲይዝ የሚረዱት ናቸው። ማህጸን የሶስትዮሽ ቅርጽ ያለው ሲሆን ከላይ ሰፋ ከታች ደግሞ ጠበብ ያለ አቀማመጥ ያለው ነው። ማህጸን በግራና በቀኝ በኩል የየራሳቸው ቀንድ ካላቸው ሁለት የተለያዩ ተፈጥሮዎች የሚገኝ ነው። እነዚህ የተለያዩ ቀንድ ያላቸው ሁለት የማህጸን አካላት በሂደት በመዋሀድ አንድ የሆነውን ማህጸን ይፈጥራሉ።

ኢሶግ፡ ማህጸን ተፈጥሮው ሲጀምር በሁለት አቅጣጫ መሆኑ እና በሂደትም እየተገናኘ መሄዱ የሚዛባበት ሁኔታ ያጋጥማልን?

ዶ/ር አብዱልፈታህ፡ በግራና በቀኝ የሚፈጠሩት ሁለት የማህጸን ክፍሎች የማይገናኙበት ሁኔታ ያጋጥማል። የማህጸን አፈጣጠር ዋና ዋናዎቹ በሶስት ወይም በአራት ሊከፈሉ ይችላል። የላይኛው የማህጸን ክፍል፣ የማህጸን አካልና የማህጸን በር ሲሆን እነዚህ ክፍሎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ላይፈጠሩ ይችላል። የማህጸን በሩ የውስጥና የውጭ በመባል የሚታወቅ ሁለት በር ያለው ሲሆን በተዛባወ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ዝግ ሊሆን ይችላል። ማህጸንን ሙሉ የሚያደርጉት ሁለት ቀንዶች እርስ በእርስ ሳይዋሃዱ የማህጸን ዋሻው ሊኖር የሚ ችልበት የተፈጥሮ ሁኔታም ያጋጥማል። አንዱ የማህጸን ቀንድ በደንብ ከሌላኛው ጋር ሳይዋሀድ ወይንም ሳይቀናጅ ይቀርና ባለአንድ ቀንድ ማህጸን የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖ ራል። ወይንም ሁለቱም ቀንዶች ተገናኝተውም ግን ሙሉ ለሙሉ ሳይዋሃዱ በማህጸን ተፈጥሮ ላይ ችግር የሚፈጥሩበት ሁኔታ ይኖራል። ባጠቃላይም ማህጸን በሚፈጠርበት ሰአት በዘመናችን በሳይንስ በትክክል ባልተደረሰበት ሁኔታ ሂደቱ ላይ ችግር ሊከሰት ይችላል።

ኢሶግ፡ በግራና በቀኝ የሚፈጠሩት የማህጸን ቀንዶች ለየራሳቸው አፈጣጠራቸው ምን ይመስላል?

ዶ/ር አብዱልፈታህ፡ ሁለቱ በተለያየ ሁኔታ የሚፈጠሩት የማህጸን ቀንዶች የየራሳቸው አካል ያላቸው ሆነው የሚፈጠሩ ናቸው። ነገር ግን በሂደት ሁለቱ እየተቀናጁ እና በተለያዩ አካላዊ ቅመሞች አማካኝነት በመሀከላቸው ያለው ግድግዳ እየፈረሰ በመሄድ ወደ አንድ አካልነት ይለወ ጣል። የማህጸን ዋሻውም በሂደት እየተፈጠረ ይሄዳል። ነገር ግን የማህጸን ዋሻው ሳይፈ ጠር ሊቀር ይችላል ። ወይንም አንዱ ሲኖረው ሌላዋ ላይኖረው ይችላል። ዋሻዎቹ ካል ተገናኙ በየወሩ የወር አበባ ማየት በሚጀመርበት ወቅት በትክክል መፍሰስ ስለማይችል ደሙ እየተጠራቀመ በየወሩ የህመም ስሜትን ያስከትላል።በየወሩ መፍሰስ የሚገባው ደምም በሰውነት ውስጥ እንዲጠራቀም ይሆናል።

ኢሶግ፡ የወር አበባው በትክክለኛው መንገድ ሳይፈስ በሰውነት ውስጥ በሚጠራቀምበት ወቅት እርግዝና የመከሰት እድል ይኖር ይሆን?

ዶ/ር አብዱልፈታህ፡ ይህ እንደየአፈጣጠሩ ችግር ሊለያይ ይችላል። እርግዝና ሊፈጠር ወይንም ላይፈጠርም ይችላል። ዋሻዎቹ ከመደሰቻ አካል ጋር ግንኙነት ካላቸውና የማህጸን ቱቦ ክፍት ሆኖ የዘር ፍሬም የሚፈጠር ከሆነ ያለምንም ችግር እርግዝናው ተከስቶ እስከመጨረሻው ድረስ ሊቀጥል ይችላል። ሁለቱ የማህጸን ቀንዶች ግንኙነት ከሌላቸውና አንዱ ግን ከመደሰቻው አካል ጋር ግንኙነት ኖሮት እስፐርም በዚያ ገብቶ የዘር ፍሬውን እስካገኘ ድረስም እርግዝና ሊፈጠር ይችላል። ከዚህ ውጪ ግንኙነት የሌለው የማህጸን አካል ውስጥም እርግዝናው ሊከሰት የሚችል ሲሆን ይኼኛው ግን በትክክል ሂደቱን ሳይጨርስ ሊጨናገፍ ይችላል። ስለዚህ እንደዚህ ያለ ችግር ያለባቸው ሴቶች እርግዝናው ቢቀጥ ልም ነገር ግን ጊዜውን ያልጠበቀ ምጥ የመምጣት ፣ከወለዱም በሁዋላ ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ኢሶግ፡ ሁለቱ የማህጸን ቀንዶች ሳይገናኙ ሲቀሩ ሁለቱም የየራሳቸው የዘር ፍሬ የመሳሰሉት ተፈትሮዎች ይኖሩዋቸዋልን?

ዶ/ር አብዱልፈታህ፡ ሁለቱ የማህጸን ክፍሎች ካልተገናኙ ሁለት እራሱን የቻለ ማህጸን ፣ሁለት የመደሰቻ አካል፣ ሁለት የዘር ፍሬ ፣ሁለት የማህጸን አንገት ይኖራቸዋል። የመደሰቻ አካሉን ግርዶሽ የሚከፍለው ከሆነ የተለያየ ክፍል ይኖረዋል። እርግዝናም በሁለቱም ክፍል ሊፈጠር ይችላል። በእርግጥ አብዛኛውን ጊዜ ችግር ሳያስከትል ሊወለድ ወይንም ያለጊ ዜው መውለድ ሊኖር ይችላል። እንደዚህ ያለው ማህጸን ባይነካ እና እንዳለ ቢቀጥል ይመረጣል።

ኢሶግ፡ አንዱ የማህጸን ቀንድ ከሌላው ጋር ግንኙነት ከሌለው እና ምንም አገልግሎት የማይሰጥ ከሆነ ችግር አያስከትልንም?

ዶ/ር አብዱልፈታህ፡ ሁለቱ የማህጸን ቀንዶች እርስ በእርስ ምንም ግንኙነት ሳይኖራቸው በአንደኛው ብቻ እርግዝና ሊከሰት የሚችል ከሆነ ሌላኛው ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል እና ለጤንነት ችግር ማስከተሉ ስለማይቀር በቀዶ ሕክምና ቢወገድ ይመረጣል። እርግዝና እየተከሰተ ባልታሰበ ጊዜ የሚጨናገፍ ከሆነ ምናልባትም ከማህጸን አፈጣጠር ችግር ጋር በተያያዘ ሊሆን ስለሚችል ሁለቱ የማህጸን ቀንዶች ለየብቻ ተቀምጠው ያልተዋሀዱ ወይ ንም በመጠኑ የተዋሀዱ ከሆነ የቦታ ችግር ስለሚኖር ጽንሱን ለማጨናገፍ ወይንም በተገቢው ሁኔታ እንዳያድግ ምክንያት ስለሚሆን የህክምና ክትትል ያስፈልጋል። በሕክ ምናው አገልግሎት የሚሰጠው መፍትሔም ሁለቱም ያልተዋሃዱት የማህጸን ክፍሎች ተቀደው እንዲዋሀዱ ይደረጉና አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ ይዘጋጃሉ። የአፈጣጠር ችግር ያለበት ማህጸን በዚህ መልኩ ከተዘጋጀ በድግግሞሽ የሚከሰተውን የጽንስ መጨናገፍ ለማስወገድ ያስችላል።

ኢሶግ፡ የማህጸን ተፈጥሮአዊ መዛባትን ለማስወገድ የሚያስችለውን ሕክምና በተሟላ መልኩ በአገራችን ለመስጠት ይቻላልን?

ዶ/ር አብዱልፈታህ፡ ሕክምናው በኢትዮጵያም ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የአለም ክፍል ሊሰራ የሚችል እና ከባድ ያልሆነ ነው። በሀገራችን ባለው የህክምና አገልግሎት አሰጣጥም ይህ ችግር እንዲወገድ ይደረጋል። እስከአሁን ባለው ሁኔታም ብዙ ባይሆኑም ሕክምናውን አግኝተው ከችግሩ የተላቀቁ እና አርግዘው የወለዱም ብዙ ናቸው።

ኢሶግ፡ ሴቶች የማህጸን አፈጣጠር ችግር መኖሩን አስቀድሞውኑ ሊገምቱ የሚችሉበት ዘዴ ይኖራልን?

ዶ/ር አብዱልፈታህ፡ የማህጸን አፈጣጠር ችግር አለ ሲባል ከእርግዝና መጨናገፍ ከመሳሰሉት ጋር ብቻ ማያያዝ አይቻልም። ምክንያቱም እርግዝናውን ካልሞከሩት ሊታወቅ ስለማይችል ነው። ከዚህ ውጭ ግን ፡- ሴቶች ግንኙነት በሚፈጽሙበት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ሕመም የሚሰማ ቸው ከሆነ፣ የወር አበባ ከጊዜ ወደጊዜ የሕመም ደረጃውን እየጨመረ የሚመጣና የሚያሰቃይ ከሆነ፣ የወር አበባ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከነጭርሱንም የማይታይ ከሆነ፣ ወደሕክምና በመቅረብ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ተገቢ ይሆናል።

ኢሶግ፡ ሴቶች በሚወልዱዋቸው ልጆች ላይ ይህ ችግር እንዳይከሰት ምን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይችላሉ?

ዶ/ር አብዱልፈታህ፡  በመጀመሪያው የእርግዝና ወቅት ማለትም በሶስት ወር ...በተለይም በመጀመሪያው ስምንት ሳምንት የተለያዩ የጽንሱ የሰውነት አካሎች የሚፈጠሩበት ወቅት ስለሆነ በዚያን ጊዜ ሐኪም ያላዘዘውን መድሀኒት መውሰድ፣ ለጨረር መጋለጥ የመሳሰሉት እና ከምግብ ጋር የሚወሰዱ ንጥረ ነገሮችም ጽንስ ላይ ችግር ሊያመጡ ስለሚችሉ ይህንን ማስወገድ ይመከራል። እንደዚህ ያሉ ችግሮች ለማህጸን አፈጣጠር መዛባት ብቻም ሳይሆን የተለያዩ የአካል እና ጤንነት መጉዋደልንም ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ይሆናል።

 

 

 

Read 3445 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 13:12