Saturday, 05 December 2020 17:55

በኮንሶ ጥቃትና ግጭት 66 ሰዎች ተገደሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ከ130 ሺህ በላይ ተፈናቅለዋል

              በቅርቡ በኮንሶ ዞንና አጎራባቾች በተከሰተው ግጭትና የታጣቂዎች ጥቃት 66 ሰዎች መገደላቸውንና 39 መቁሰላቸውን ያመለከተው የደቡብ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሪፖርት፤ ከ130 ሺ በላይ ሰዎች መገደላቸውንም ጠቁሟል።
ጥቃቱ በኮንሶ ዞን፣ አማሮ፣ ደራሼና አሌ ወረዳዎችን ያካለለ ሲሆን በድርጊቱ  ተሳታፊ ናቸው የተባሉ 137 ተጠርጣሪዎች በክልሉ የፀጥታ ሃይሎች መያዛቸውም ተመልክቷል።
በአካባቢው በሚገኙ 17 ቀበሌዎች የተዳረሰው ይህ ግጭትና ጥቃት በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችና የመንግስትና ግለሰቦቹ ሃብት የወደመበት መሆኑም ሪፖርቱ ይጠቁማል። በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት 4 አባላት ያሉት የህግ ምርመራ ቡድን ወደ አካባቢው አምርቶ ተጨማሪ ምርመራዎችን እያደረገ መሆኑንም አስረድቷል- የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ።
በአካባቢው በዋናነት ጥቃቱን እየፈጸመ ያለው በህወሃት ሲደገፍ የቆየው የኦነግ- ሸኔ ታጣቂ ቡድን መሆኑንም ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኮንሶ ዞንም ሆነ አጎራባች አካባቢዎች፣ ለሁለት ሳምንታት ከዘለቀው ግጭትና ጥቃት ወጥተው ወደ መደበኛ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሱ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።
 ከየአካባቢዎቹ ለተፈናቀሉት ወገኖች ከረድኤት ተቋማት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ የክልሉ መንግስት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።


Read 14374 times