Saturday, 05 December 2020 18:15

ጠ/ሚኒስትሩ የቀጣዩን ምርጫ ደህንነት ለማስጠበቅ እየሰራን ነው አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ፓርቲዎች በገንዘብ የተደለሉ አባላቶቻቸውን እንዲለዩ አሳስበዋል

                 ዘንድሮ ይካሄዳል የተባለውን ሃገራዊ ምርጫ ውጤታማ ለማድረግ መንግስት የነደፋቸውን ዋና ዋና እቅዶች ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ፣ ሰሞኑን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ይፋ አድርገዋል። ምርጫውን ውጤታማና በሁሉም ዘንድ ተአማኒ ለማድረግ፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች አስቀድመው ውስጣቸውን ማጥራት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
ፓርቲዎች  በገንዘብ ተደልለው ያልተገባ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ አባላቶቻቸውን ለይተው እንዲያጣሩ ያሳሰቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ መንግስት ከመሆናቸው በፊት ሌብነትንና ሙስናን መቆጣጠር ካልተለማመዱ ችግር ላይ ይወድቃሉ ብለዋል፡፡
ብልፅግና ሳያሸንፍ በስልጣን ላይ ለመቀጠል እንደማይፈልግ የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በምርጫው የሚያሸንፍ ከሆነም ከተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ብቃት ያላቸውን መርጦ በሚመሰረተው መንግስት ውስጥ ሊያሳትፍ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
የምርጫውን ደህንነት በሚመለከት መንግስታቸው ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ከተቋማትና ከምርጫ ቦርድ የተውጣጡ አባላት ያሉት የክትትል ኮሚቴም እንደሚቋቋም አስታውቀዋል፤ኮሚቴው  የራሱ ዘመናዊ የሁኔታዎች መከታተያ (Situation Room) እንደሚኖረው በመግለፅ፡፡  ኮሚቴው ከምርጫው በፊት፣ በምርጫው እለትና ከምርጫው በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ተንትኖ ያቀርባል፤ ደህንነትና ፀጥታውንም ይቆጣጠራል ተብሏል።
ሁሉም ፓርቲዎች የምርጫ ስነ-ምግባር ደንቡን እንዲያስከብሩ ያሳሰቡት ዶ/ር ዐቢይ፤ብልጽግና  የራሱን ተጨማሪ የስነ-ምግባር ደንብ ቀርጾ አባላቱን ለማሰልጠን መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በምርጫው ሂደት የሚገጥሟቸውን እንደ አባላት መታሰር፣ የፅ/ቤት መዘጋትና ሌሎች ተያያዥ  ችግሮችን ጨምሮ እልባት የሚያበጅ ኮሚቴም ከራሳቸው  ከተቃዋሚዎችና ከምርጫ ቦርድ ይቋቋማል ተብሏል፡፡
የምርጫ ታዛቢዎችን በተመለከተም 99 በመቶ የሃገር ውስጥ ታዛቢዎች ቢሳተፉ የተሻለ እንደሚሆን ምክረ ሃሳብ ያቀረቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይህም ምርጫውን ከውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትና ውዝግብ የፀዳ ለማድረግ እንደሚረዳ አስረድተዋል። መንግስት የዘንድሮ  ምርጫ ለቀጣይ ምርጫዎች ትልቅ መሰረት የሚጥል እንዲሆን በጥንቃቄ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ።


Read 14576 times