Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Friday, 10 August 2012 16:24

እኛና ሰላማዊ ትግል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሰላማዊ ትግል በሀገራችን ፍሬያማ ያልሆነበትን ምክንያት በርካቶች ከማንነታችን ጋር ያያይዙታል፡፡

የጥንቱን ትተን ዘመናዊ ታሪካችንን ብንመለከት እንኳ በስልጣን ላይ ያለ ቡድንንም ሆነ ግለሰብን ከስልጣን ለማውረድ የሚፈልጉ ኃይሎች ለአላማቸው ማስፈፀሚያ ይጠቀሙ የነበረው የትጥቅ ትግልን ወይም ደግሞ ሌላ የኃይል እርምጃ መሆኑ የአሁኑ እኛነታችን ላይ ያሳደረው ተፅእኖ አለ፡፡ እንደ ሀሳቡ አራማጆች እምነት ይህ ተፅእኖ በሰላማዊ ትግል ለውጥ የማምጣት እምነትና ተስፋን ይገድላል፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች የማይፈልጉትን ስርዓት አስወግደው በምትኩ የሚፈልጉትን ለመተካት ይችሉ ዘንድ ሰላማዊውን የትግል አማራጭ ለመከተል ተነሳሽነት እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡ እንዲህ አይነቶቹ ዜጎች የወቅቱ የዓለም ሁኔታና ሌሎች ውጫዊ ተፅእኖዎች በሰላማዊው የትግል ማዕቀፍ ውስጥ ለጊዜው እንዲሰባሰቡ ቢያደርጓቸው እንኳ በሙሉ ልባቸው አምነው የሚደግፉትና የገቡበት አማራጭ ባለመሆኑ ሲፀኑበት አይታዩም፡፡ ፅናት የሌለበት ትግል ደግሞ የትም እንደማያደርስ ይታወቃል፡፡

እነዚሁ ወገኖች በሰላማዊ ትግል ስኬትን ላለመጎናፀፋችን በምክንያትነት የሚጠቅሱት ሌላው የእኛነታችን ክፍል ደግሞ ለጀግንነትና ለጀግኖች ያለንን አመለካከት ነው፡፡ እንደነዚህ ወገኖች አስተያየት ጀግኖቻችን ጠላታቸውን በጦር በጎራዴ በማርበድበድ የሚታወቁ፣ ጎበዝ አልሞ ተኳሾች፣ በጠላት እጅ ከመሞት ይልቅ ራሳቸውን ማጥፋት የሚመርጡና ተመሳሳይ ማንነት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ እርግጥ ነው የእነዚህ ሰዎች ጀግንነት ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ጀግኖቻችን እንደዚህ አይነቶቹ ብቻ ከሆኑ ግን የሰላማዊ ትግል አማራጭን ምርጫቸው በማድረግ ላመኑበት አላማ በፅናት ለመታገልና ለመሞት የቆረጡ ሰዎችን እንደ ደካሞች እንድንቆጥርና ሰላማዊ ትግሉን በምንችለው ሁሉ እንዳናግዝ እንቅፋት ይሆናል፡፡

የቅንጅት መሪዎች ከእስር ከተፈቱ በኋላ የመረጧቸው የትግል ስልቶች በተለይ ከዲያስፖራው ያስገኘላቸውን ድጋፎች ወይም ደግሞ ያመጡባቸውን ውግዘቶች ለዚህ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በሰላማዊ መንገድ ኢህአዴግን ለመታገል በመወሰኗ በውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያውያን ድረ-ገፆች መሃል በወቅቱ “ተንበርካኪዋ እመቤት” በማለት የገለጿት ነበሩ፡፡ በአንፃሩ እነዚህ ድረ-ገፆች ሰላማዊ የትግል ስልት እንዳበቃለት በመግለፅ መስመራቸውን የለወጡትን ፖለቲከኞች “ጀግና” በማለት አሞካሽተዋቸዋል፡፡ የጠቀስናቸውና ሌሎች ተመሳሳይ ስብዕናዎችን ለሰላማዊ ትግሉ ውጤታማ አለመሆን ትልቅ ሚና እንዳላቸው በመጥቀስ የሚከራከሩ እንዳሉ ሁሉ ለሰላማዊ ትግሉ ፍሬያማ አለመሆን ህዝቡ ተጠያቂ እንደማይሆን ማስረጃ በማስደገፍ የሚከራከሩም አልጠፉም፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው መምህር ወንድወሰን ደጀኔ (ስሙ ተቀይሯል) ህዝቡ በሰላማዊ ትግል እምነት እንዳለው የ1997 ዓ.ም ምርጫ ምስክር እንደሆነ በመጥቀስ በወቅቱ ለቅንጅት ድጋፉን ለመስጠት ወጥቶ የነበረውን የሚያዝያ 30 ሰልፈኛ ያስታውሳል፡፡ እንደ ወንድወሰን እምነት ህዝቡ በተለይ በደርግ ስዓት የነበረው፣ ልጆቹን ለጦርነት እንዲገብር ምክንያት የሆነው የትጥቅ ትግል አማሮታል፡፡ በመሆኑም የመንግስት ለውጥ እንዲመጣ የሚፈለገው በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ ህዝቡ ሰላማዊ ትግሉን የሚመሩ ትክክለኛ መሪዎች ማግኘት አለመቻሉ ግን በሀገራችን ሰላማዊ ትግል ውጤታማ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል፤ እንደ ወንድወሰን ገለፃ፡፡

ከሰላማዊ ትግል ጋር በሚገባ ያልተዋወቁ ሰላማዊ ታጋዮች

ለሰላማዊ ትግሉ ስኬታማ አለመሆን ራሳቸው በሰላማዊ ትግል ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጠያቂዎች መሆናቸውን የሚያምኑት ጥቂቶች አይደሉም፡፡

እነዚህ ሰዎች ይህንን አመለካከት የያዙበት የተለያዩ መነሻ ምክንያቶችም አሏቸው፡፡ አንደኛው መነሻ ምክንያት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ አባላት የተገኙት ከህብረተሰቡ እንደመሆኑ በቀደመው ንዑስ-ርዕስ ስር የተገለፀው በሰላማዊ ትግል ከልብ ያለማመን ችግር በእነዚህ አካላትም ላይ መስተዋሉ እንደማይቀር ከማመን የመጣ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ችግሩ ከማንነታችን ጋር የመያያዝና ያለመያያዙ ጉዳይ አከራካሪነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ላይ የተባለው አይነት በሰላማዊ ትግል ከልብ ያለማመን ሁኔታ እንደሚታይ ግን መካድ አይቻልም፡፡ ይህንን ለማለት ካስደፈሩን ሁኔታዎች ውስጥ አንዳንድ የቅንጅት መሪዎች ከእስር ከተፈቱ በኋላ ያደረጉት የአቋም ለውጥ ይጠቀሳል፡፡ ሰላማዊ ትግል እንደሞተ ያወጁት እነዚህ የፖለቲካ መሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ስር ነቀል የሆነ የአቋም ለውጥ ሊያካሂዱ የቻሉት ቀድሞውኑም በሰላማዊ ትግል ላይ የፀና  አቋም ስላልነበራቸው እንደሆነ መጠርጠሩ ከጤናማ አእምሮ የሚጠበቅ ሀሳብ ነው፡፡ የፀና አቋም ሳይያዝበት የሚደረግ እንቅስቃሴ ደግሞ የትም የማያደርስ በመሆኑ ለሰላማዊ ትግሉ የትም አለመድረስ በግማሽ ልባቸው ሰላማዊ ትግሉን የተቀላቀሉ ፖለቲከኞች እንደ አንድ ችግር መወሰዳቸው አይቀርም፡፡ በሰላማዊ ትግሉ ውጤታማ አለመሆን ተቃዋሚዎች ከሚተቹባቸው ጉዳዮች ውስጥ የሰላማዊ ትግል ግንዛቤ መጓደል ወይም ግንዛቤው ቢኖር እንኳ የተገነዘቡትን በስራ ለማዋል አለመቻል ይገኙበታል፡፡ የአባባሉን እውነትነት ለመረዳት በተቃዋሚዎች እየተተገበሩ ያሉ የአመፅ አልባ ትግል አይንቶችንና ቁጥራቸውን ብቻ ማስታወሱ ይበቃል፡፡ ጄን ሻርፕ “From dictatorship to democracy” በተባለው መፅሀፋቸው ከዘረዘሯቸው ወደ 198 የሚደርሱ የአመፅ አልባ ትግል አይነቶች ውስጥ በሀገራችን ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አምስቱን እንኳ በትክክል ስለመጠቀማቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ያህል በሌላው አለም ሰላማዊ ትግል የሚያካሄዱ ፓርቲዎች የሚቃወሟቸው መንግስታት መሪዎች የሚያደርጓቸውን ንግግሮች ሊገዳደሩ የሚችሉ የአፀፋ ንግግሮች በማዘጋጀት ለህዝብ እንደሚቀርቡ ይታወቃል፡፡ የሀገራችን ፓርቲዎች ግን ይህን ቀላል ነገር እንኳ ሲያደርጉ አይታይም፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያቷን የሰጠችን አንዲት ወጣት ፓርቲዎቹ የሰላማዊ ትግል ስልት መንገዶችን እየተጠቀሙ ላለመሆናቸው ለማሳያነት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መሪ የወ/ሪት ብርቱካንን መታሰር በተመለከተ ፓርቲዋን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚዎች በተገቢው መጠን አለመንቀሳቀሳቸውን ትገልፃለች፡፡ የወ/ሪት ብርቱካንን መታሰር ለመቃወም እንደሚደረግ የሚነገርለትንና ወር በገባ በ20ኛው ቀን የሚከናወነውን “የቃሌ ምሽት” ፋይዳ ሳይቀር የምትጠይቀው ወጣት “ሰዎቹ ሰላማዊ ትግልን አያውቁም”  ባይ ናት፡፡ እንደ ወጣቷ እምነት የታሰረችበትን ቀን ጠብቆ ከፓርቲው ፅ/ቤት እንኳን ሳይወጣ የሚከናወነው የሻማ ማብራት ሥነ-ስርዓት የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ “ህዝቡ፣ የመንግስት ባለስልጣናትና አለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ተቃውሟቸውን በማያዩበት ሁኔታ የፓርቲዎቿ ሰዎች ተቃውሟቸውን የሚያሰሙት ለማን ይሆን?” ስትልም ትጠይቃለች፡፡

አስተያየቷን የሰጠችንን ወጣት ጨምሮ በርካታ ሰዎች የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰላማዊ ትግል በሀገራችን ገና ጫፉም እንዳልተነካ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡/  ከጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ “ኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ” መፅሃፍ ላይ የተቀነጨበ/

 

 

 

Read 2011 times Last modified on Friday, 10 August 2012 16:31