Sunday, 06 December 2020 00:00

በአለማችን ከ40 ሚ. በላይ ሰዎች “የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ናቸው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አለም በስልጣኔና በቴክኖሎጂ በረቀቀችበት በዛሬው ዘመን በመላው አለም ከ40 ሚሊዮን በላይ ሰዎች “የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ሆነው እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ የስራ ድርጅት ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ በመላው አለም ከአስር ህጻናት አንዱ ወይም 150 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ለዕድሜያቸው የማይመጥንና አደገኛ የግዳጅ የጉልበት ስራ በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ተጨማሪ 1 ሚሊዮን ያህል ህጻናትም በህገወጥ የሰዎች ዝወውር በቂ ክፍያ የማያገኙበትን ሥራ እንዲሰሩ ወይም ወሲባዊ ብዝበዛ እንዲፈጸምባቸው እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
“የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ከሆኑት 40 ሚሊዮን ያህል ሰዎች መካከል 25 ሚሊዮን ያህሉ የግዳጅ የጉልበት ስራ እንደሚሰሩና 15 ሚሊዮን ያህሉም ያለፈቃዳቸው ተገድደው ወደ ትዳር እንዲገቡ መደረጋቸውንም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
የጉልበት ስራ፣ የግዳጅ ጋብቻ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በተለያዩ የጥቃትና የሃይል ድርጊቶች ዜጎችን “የዘመናዊ ባርነት” የሚያደርጉ አካላት፣ በየአመቱ 150 ቢሊዮን ዶላር ያህል ትርፍ ያለአግባብ በማካበት ላይ እንደሚገኙ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በበኩላቸው፤ “የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ሆነው ከሚገኙት የአለማችን አገራት ዜጎች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ልጃገረዶች መሆናቸውን በትዊተር ገጻቸው ባወጡት ጽሁፍ ገልጸዋል፡፡

Read 2608 times