Monday, 07 December 2020 00:00

የፖለቲካ ለውጥ በኢትዮጵያዊያን ታሪክ ውስጥ

Written by  ፊደል ችሎ
Rate this item
(1 Vote)

 የሰው ልጅ የፖለቲካ ተሳትፎው፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲሁም የማህበራዊ መስተጋብሩ  ከዘመን ዘመን ይለያያል፡፡ በየዘመኑ፤ ሀገርን ለማሻሻል የሚደረገው የፖለቲካም ይሁን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደ ዘመኑ መንፈስ ይወሰናል። በአንድ ወቅት ኑሮን ለማሸነፍ አደንና ፍሬ መልቀም የቅርብ  አማራጮች ነበሩ። በተጨማሪም የፖለቲካ ንቃቱም እንደ ዘመኑ፣  እንደ ባህሉና እንደ ማህረሰቡ ተሳትፎ  ይለያያል፡፡
በአንድ ዘመን አምባገነንን ለማውረድ ጠመንጃ ወሳኝነት ነበረው፡፡ የዓለም ፖለቲካዊ ታሪክ እንደሚያስረዳን፤ ከብዙ ሀገሮች ጀርባ ሰፊ የደም መፋሰስና  እርስ በርስ መገዳደል ተከስቷል፡፡ ዛሬ የስልጣኔ ምሳሌ የምናደርጋቸው ሀገሮች ጭምር የተጓዙበትን የለውጥ ጉዞ ብንመረምር፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን ሀቅ ተጠቅመው የተሻለ ሥርአት ማቆም እንደቻሉ እንረዳለን፡፡ አውሮፓውያን  ጨቋኝና አደገኛ ከነበረው ሥርአት ለመላቀቅ የቻሉት በሂደት ከራሳቸው ታሪክና ባህል የተሻለ ስልጣኔ ማዋለድ ስለቻሉ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ነገስታትና ልሂቃን የፖለቲካ ባህሉን ለማሻሻል፣ ባህላችን ከዘመኑ መንፈስ ጋር ለማስማማት እንዲሁም ጥሩ የአስተዳደር ሥርአት ለማቆም ብዙ ደክመዋል፡፡ የለውጥ ሂደቱን ለማፋጠንም ትምህርትና የተማረ ሀይልን መካከለኛ አደረጉ፡፡ ቢሆንም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የፖለቲካም ሆነ የማህረሰብ ንቃተ ህሊና አንዳንዴ ለውጥን የሚፈራ፣ ሌላ ጊዜ ለውጥን የሚያደናቅፍ መሆኑ ታሪክ የሚነግረን ሀቅ ነው፡፡  ይህንንም ለማስተካከል፣ እንደ ገ/ህይወት ባይከዳኝ ያሉ ምሁራን፤ ትምህርት ባህላችንን ለማሻሻል፣ ለሀገር እድገት እንዲሁም ጥሩ የአስተዳደር ስርአት ለማቆም አስፈላጊ  ነው ሲሉ ሞግተዋል፡፡
በታሪካችን የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት፣ ማህበራዊ ፍትህን እውን ለማድረግ እንዲሁም ህዝባዊ አስተዳደርን ለማቆም ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ይህንን እውነት ለማለት ከአፄ ዘ-ድንግል ታሪክ ጀምረን፣ ልጅ እያሱ የደረሰበትን ሁነት ቆጥረን፣ ኃይለስላሴ የሆነባቸውን  አስበን፣  ደርግ ታሪክ የሆነበትን ብንመረምር የለውጥ ጥያቄው የተነሳበትን ሁነትና የተመለሰበትን መንገድ  ለማወቅ እንችላለን፡፡  ቀደም ሲል በተለይ ከአብዮታዊት ኢትዮጵያ በፊት የለውጥ ጥያቄን በመምራት የቤተ ክህነት ሰዎች ሚናቸው ከፍተኛ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ዶክተር ጳውሎስ ሚልክያስ በአንድ ጥናታቸው፤ በለውጥ እንቅስቃሴ የቤተ ክህነት ሰዎች ሚና የጎላ እንደነበር ያስረዳሉ። እንደ ምሳሌም በሱስንዮስ ዘመንና በእያሱ ጊዜ የሆነውን ዋቢ ያደርጋል፡፡ እያደር ከግዝት ይልቅ ዓለማዊነት ነገሰና፣ የለውጥ ጠያቂዎቹ ደብተራዎች ሳይሆኑ የፈረንጅ ትምህርት የቀመሱ ትውልዶች ሆኑ፡፡ በዚህ ምክንያትም የሚጠየቀው ጥያቄ፣ የሚፈለገው መልስም የተለያየ መሆኑ እውነት ነው፡፡
ግርማዊኒታቸው ኢትዮጵያን አዘምናለሁ ብለው ተነሱ፡፡ የፈረንጅ ትምህርትን ወሳኝ የአዘማኝነታቸው ጉልበት አደረጉት፣ ህገ-መንግስት ሰጠናችሁ አሉ፡፡ ቢሆንም ያቆሙት አስተዳደር ከመኮነን አልፎም ለተጠያቂነት አበቃቸው፡፡ ያረቀቁት ህገ-መንግስት፣ የፈጠሩት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስርአት ታሪክ ሊሆን ተገደደ፣ ተለወጠም። የለውጥ እንቅስቃሴውንም ጉልበት ለመስጠት ጠመንጃ አስፈላጊ ነበር። የሰለሞናዊ መንፈስ ተሽሮ፣ ባላባታዊ ባህል ተገርስሶ ደርግ የሰራተኛውን አስተዳደር ለማቆም የማርክስን ፍልስፍና እውነቴ አለ፤ ስለ እርሱም ገዞየ እስከ ቀራንዮ ነው ብሎ ማለ፡፡
የ”ኢትዮጵያ ትቅደም; መርሁን ይዞ ሀገሪቱን ይመራ ዘንድ እድል አገኘ፡፡ ኢትዮጵያም ከደብተራ ቃል ይልቅ ሌሊንን የሚጠቅስ፣  እንደ ቼ ጉቬራ እያለ የሚፎክር  ጎበዝ አየች፡፡ ማርክሲዝም የዘመን መንፈስ ነውና በኢትዮጵያችን ገብቶ ነገሮች ሁሉ ከፍልስፍናው አንፃር ይጠየቁም፣  ይፈረጁም ዘንድ ሆነ፡፡ ለግርማዊነታቸው ሲሰግድ የነበረ ህዝብም ለስድብና ለውግዘት ጎዳና ወጣ፡፡ አዲሱን መንግስትም እልል ብሎ ተቀበለ፡፡ ወዲያውም አዲሱን የመንግስት አስተዳደር ድምጥ የሰጠ ህዝብ ስለ ነፃነት ሲል ጥያቄውን አበዛ፡፡ በየቦታው ለውጥ፣ ህዝባዊ መንግስት የሚሉ ጥያቄዎች በዙ፡፡ በጠመንጃ የተገኘው ወንበርም በጠመንጃ መነቅነቅ ጀመረ፡፡ ስርአቱም በጨፍላቂነትና በአምባገነንነት ተከሰሰ፡፡ ብሔር በኢትዮጵያ የተገፋ ማንነት ነው የሚሉ ጠያቂዎች ብቅ አሉ፡፡ አሁንም ለውጥ የመካከለኛ ጥያቄ ሆነ።   
የለውጥ ታሪክ በኢትዮጵያ ጥያቄ ያልሆነበት ዘመን አለ ለማለት ይከብዳል። ታሪክ ጎላ የሚያደርጋቸውን እንኳን ብንቆጥር፤ ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን የታገሉለትን የባህል ማሻሻያ ጥያቄ ልብ ማለት እንችላለን። እንደ ዶክተር መአምሬ መረዳት፣ እስጢፋኖሳውያን ትግላቸውና እሳቤያቸው ትኩረት የሰጠው ነፃነትን ነው። የቤተ ክህነት ስርአትን መሰረት አድርገው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የጭቆናና የመገለል ባህል ይቅር ሲሉ ተከራከርዋል። ዛሬም ቢሆን አብዮተኛ የሚያስብላቸው ወሳኝ የፖለቲካና ማህበረሰባዊ ሁነቶች ሊስተካከሉ ይገባል  ሲሉ ተፈትነዋል፡፡
ኢትዮጵያና ለውጥ በተለይም ፖለቲካዊ ለውጥን ስንመለከት፣ እጅግም ከጠመንጃና ከደም መስዋእትነት ያልራቀ ታሪክ አላቸው። በየዘመኑ የተከሰቱትን የለውጥና የማሻሻያ ሙከራዎች መለስ ብለን ብንቃኛቸው፣ ጠመንጃ ወሳኝ ድምፅ ሆኖ እናገኛለን፡፡ ስለ ነፃነት የሚኬደው ርቀትም ሆነ ፖለቲካውን ለመቆናጠጥ የሚደረገው ትግል፣ ከውይይት ይልቅ ለምንሽር ልቡን ሰጥቶ እናገኛዋለን፡፡
ከ1953 የለውጥ ሙከራ ጀምረን፣ ደርግ እውን የሆነበትን ታዝበን፣ የ1983 አብዮታዊ መርህን ቆጥረን፤ በፖለቲካ ታሪካችን የወጣን የወረድናቸውን ተጋድሎዎች ብንጠይቃቸው፣ ምንም ያህል ከጥርስና ጥፍር ያልተላቀቀ ተፈጥሮ እንዳላቸው እንረዳለን፡፡ የፖለቲካ ታሪካችን በእጅጉ የደም መስዋእትነት የሚፈለግ እስኪመስል ድረስ በየዘመኑ የተደረጉት የለውጥ እንቅስቃሴዎች፣ ብረት ለብሰው ብረት ጎርሰው መከሰታቸው፣ ይህንን ያረጋግጥልናል፡፡
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ግንዛቤ በትክክል ለመረዳት፤ ወደፊት የሚሆነውንም ለመተንበይ የሚከብድ ነው፡፡ እንደ በጎ ባህል የሙጥኝ ያልነው የብሔርተኝነት መንፈስ የፖለቲካ መረዳታችንን፣ የታሪክ ግንዛቤያችንን እንዲሁም ነገ የምንመኛትን ሀገር ጭምር በእጅጉ ለያይቶብናል፡፡ የፖለቲካ ባህላችንን   ለማዘመን የተደረጉ ሙከራዎች የተነሱበትን ህልም ከማሳካት አንፃር ሲመዘኑ፤ የህዝብን ጥያቄ መካከል ከማድረግ አኳያ ሲጠየቁ፤ አማራጭና የተሻለ የፍትሕ ተቋማትን ከማቋቋም አንፃር ሲታዩ ብዙ እንከንና ክፍተት ይታይባቸዋል።
አብዛኛውን ጊዜ በታሪካችን የታየው የፖለቲካ ለውጥ አንዳንዴ የማህበረሰቡን እውነት ሳያገናዝብ፣ ሌላ ጊዜ ከሚስተዋሉት ታሪካዊና ማህበራዊ ችግሮች ሳይስተካከል ቀርቶ ይዞ የተነሳውን ሳያሳካ ቀርቷል።
በየማህበረሰቡ የእኩልነት፣ የፍትሕና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች የመኖራቸውን ያህል ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚታሰብበት መንገድ  ከጠመንጃ ባህል መላቀቅ አለመቻሉ ይበልጥ የፖለቲካ ባህላችንን ተገታሪ አድርገውታል፡፡




Read 3385 times