Tuesday, 08 December 2020 13:35

"አዲሱ ትውልድ ራሱን መምራት ይችላል"

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ  በቀለ የተወለደው እዚሁ አዲስ አበባ ባሻ ወልዴ ችሎት በተባለ ሰፈር ነው - የዛሬ 76 ዓመት ገደማ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ባልንጀሮቹ በ1952 ዓ.ም ባቋቋሙት “የምኒልክ አበባዎች” የተሰኘ ክበብ ውስጥ አባል ሆኖ ቴአትር በመጻፍ፣ በመተወን፣ በማዘጋጀትና ዘፈን በማቀንቀን ጭምር በንቃት ይሳተፍ እንደነበር ያስታውሳል። ዕድሜውን ሙሉ ከስነ ፅሁፍ ያልተለየው አፈወርቅ በቀለ፤ በሚወደው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ውስጥ ለረዥም ዘመናት በተለያዩ ሃላፊነቶች አገልግሏል።  በርግጥ አሁን እንደ ቀድሞው ከቤት ውጭ አያዘወትርም፡፡ በህመም ሳቢያ እንቅስቃሴው ተገድቧል።  ሰሞኑን ግን  ብርሃንና ሰላም በነፃ ያተመውንና የራሱን ጨምሮ የ35 አንጋፋ ደራሲያንን ታሪክ የያዘው መጽሐፍ የርክክብ  ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝቶ ነበር።  የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ አጋጣሚውን በመጠቀም  ከደራሲ አፈወርቅ በቀለ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አውግታለች፡፡ እነሆ፡-

                ጋሽ አፈወርቅ እንዴት ነህ---?  
እግዚአብሄር ይመስገን፣ እኔ እንዳለሁ አለሁ፣ አይደል የአገሬ ሰው የሚለው?! እንዲያ ነኝ፡፡
ዛሬ የአንተን ታሪክ ጨምሮ የ35 አንጋፋ ደራስያንን ታሪክ ያካተተ “ማህደረ ደራሲያን” የተሰኘ መፅሐፍ የርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ ለመታደም መጥተህ ነው ያገኘሁህ፡፡ ጓደኞችህ ደግሞ መታመምህን ነግረውኛል፡፡ ታዲያ እንዴት መጣህ?
ይሄውልሽ የኔ ልጅ… ሰው ወደዚህ ምድር ሲመጣ ዝም ብሎ አይደለም የሚመጣው። መንፈሳዊ እሳቤ ይኑርሽም አይኑርሽም፣ ሰው እዚች ምድር ላይ ዝም ብሎ የተወረወረ አይደለም -- አላማ አለው። የመጀመሪያውና የሰው ልጅ እዚህ ምድር ላይ የመገኘቱ  ምስጢርና ጉዳይ ህይወትን ለማስቀጠል ነው። የሰው፣ የተፈጥሮን በአጠቃላይ ህይወት ያላቸውን ነገሮች እንዲቀጥሉ ለማድረግ ነው፡፡ ይህን አንድ በይልኝ፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው አልሽ?------- እኔ ደግሞ ሰው የራሱን ህይወት ያስቀጥላል፣ የተፈጥሮን የእፅዋትን፣ የአየሩን ሕይወቶች እንዲቀጥሉ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ የመጀመሪያ ተልዕኮ ሕይወት በምድር ላይ እንድትቀጥል የማድረግ ተልዕኮ ነው፡፡
ሁለተኛው ተልዕኮ ደግሞ እንደ ሰው ከተፈጥሮ ጋር በመሆን በልምድ ውስጥ ለማለፍ ነው፡፡ ልምድ ስንል ምን ማለታችን ነው?  ለምሳሌ አንቺ እሳት ማቃጠሉን ታውቂያለሽ፤ ግን  በምን አወቅሽ?
ያው እሳት አቃጥሎኝ ስለሚያውቅ…?
አዎ በእሳት ማቃጠል ልምድ ውስጥ ስላለፍሽ ታውቂዋለሽ። ለምሳሌ ይበርድሻል---- ይቀዘቅዝሻል። በዚህ ልምድ ውስጥ ስላለፍሽ ታውቂዋለሽ፡፡ ረሀብ አለ ጥጋብ አለ፣ ማግኘት አለ፣ ማጣት አለ፣ መውደቅ  እንደዚሁ አለ። ወድቆ መነሳትም አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች የሰው ልጅ  በህይወት ዘመኑ የሚያልፍባቸው ልምዶች ናቸው፡፡ ሰው እንደ ሰው ተፈጥሮ በልምዱ ወይም በሌላው ልምድ ውስጥ ሳያልፍ መኖር አይቻልም፡፡ ጤንነት አንዱ የሰው ልጅ ልምዱ ነው፡፡ መታመም ደግሞ ሌላው የህይወት ልምዱ ነው፡፡ አሁን እኔ አዎ ያመኛል፣ አዎ ቃንዛ አለኝ። እድሜዬ 78 ዓመት ነው፡፡ 78ቱንም ዓመት ስኖር በህመም ልምድ ማለፍ አልችልም፡፡ አሁን ግን  በህመም ልምድ ውስጥ እያለፍኩ ነው፡፡ ተቀብየዋለሁ፤ በዚህ ልምድ ውስጥ ማለፌ ግድ ስለሆነ።
ግን ህመምህ ምንድን ነው?
በዝርዝር መነጋገሩ አስፈላጊ ቢሆንም ባይሆነም----- በአጠቃላይ ግን ያመኛል። የመጀመሪያው ትልቁ ችግሬ የአከርካሪ አጥንቴ ዲስክ መንሸራተት ነው፡፡ ያ ዲስክ ተንሸራቶ ነርቮቼን ተጭኗቸዋል፡፡ ነርቮቹ ጭነት በሚደርስባቸው ጊዜ ሌሎች የአካላችን አባል አካላት ይረበሻሉ፤ አይታዘዙም፡፡ እግሬን ይደነዝዘኛል፤ እጄን  ያቃጥለኛል፡፡ ብዙ ነው ነገሩ። እግዚአብሔር የሰጠኝ ፀጋ ምንድን ነው… ሌሊት አልጋ ላይ አረፍ ካልኩኝ እንቅልፍ ይወስደኛል፡፡ የአዕምሮዬን ኳኳታ ዞር በል እለዋለሁ፡፡
የአዕምሮን ኳኳታ ዞር በል ብሎ ማዘዝ ይቻላል?
  አዎ ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ እኔ የአዕምሮዬ ጌታ እንጂ አእምሮዬ የኔ ጌታ አይደለም፡፡ ስለዚህ “አሁን አታንኳኳ፣ አሁን ሰላም ማግኘት እፈልጋለሁ” ስለው ኳኳታው ጥሎኝ ይሄዳል። ያን ጊዜ ሰላም አገኛለሁ፡፡ ቀን ቀን ደግሞ በንቁ ህሊና መዋል አይችልም። ገና አእምሮዬ ወደ ንቃት ደረጃ ከፍ አላለም፡፡ አስተውለሽ ከሆነ …መንገድ ላይ ማንም ሰው የሚረግጠውን መሬት አስተውሎ ሲረግጥ አይታይም፡፡ ስለዚህ ማህበረሰቡን ስታይ፣ አንድም በንቃት የሚንቀሳቀስ የለም፡፡
ታዲያ በምን ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነው የምንንቀሳቀሰው?
…በግማሽ ንቁ ህሊና ውስጥ ሆነን ነው የምንንቀሳቀሰው ----- ማለት ነው፡፡ አእምሮአችን በሙሉ ንቁ ህሊና ውስጥ ሲሆን 360 ዲግሪ ያለውን ነገር ሁሉ ይቆጥራል፡፡ ይሄ የሚሳካው በተመስጦ ነው። ይሄ ደግሞ ወደ ሌላ ፍልስፍና ይወስደናል። ስለ ህመሜ ይህንን ያህል ካልኩኝ ይበቃኛል፡፡ ቤቴ ግንፍሌ ሺ ሰማኒያ አካባቢ ነው፡፡ ከዚያ እዚህ ድረስ መምጣት ለኔ ፈተና ነው፡፡ እኔ ደግሞ አልተኛም፡፡ በፍጹም እጅ ሰጥቼ አልተኛም ብዬ እንቀሳቀሳለሁ። የህመም ሁኔታዬ ይሄ ነው። ህመሙን በፀጋ ተቀብዬዋለሁ፡፡ እንደ ሰው ማለፌ አይቀርም፤ በህይወት ውስጥ የህመም ልምድ ምን እንደሆነ አውቄ፤ሳልፍ አልፋለሁ ማለት ነው።
በዛሬው ዕለት ለምትወደው ለአንጋፋው የደራሲያን ማህበር ህንጻ ማሰሪያ የሚሆን ሁለት የትርጉም መጻህፍትህን በስጦታ ታስረክባለህ፡፡ አሁንም ትፅፋለህ ትተረጉማለህ ማለት ነው?
አሁን እንደዚህ እያመመኝ አልጽፍም፤ ለነገሩ እፅፋለሁም አልጽፍምም ማለት ይቀላል። እፅፋለሁ ስልሽ የዚህ ትውልድ ወጣቶች ግጥሞች፣ ስነ ፅሁፎች ደስ ይሉኛል፤ ትውልዱ ደግሞ እንደ አባቱ አድርጎ ስለሚመለከተኝ፣ “እባክህ ጋሽ አፈወርቅ ግጥማችንን እይልን----አርትኦት ስራልን፣ እባክህ ልብወለድ ስራችንን እይልን ---- ይሆናል ወይም አይሆንም በለን” ብለው ወደ እኔ ይመጣሉ፡፡ እነሱ እንድንቀሳቀስ እድል ይሰጡኛል፡፡ የሚሆነውን ይሆናል እላለሁ። ንግግሬ አንድና አንድ ነው። የማይሆን ከሆነ አይሆንም፡፡ ”ግጥሙን ትተህ ሌላ እንጀራ ፈልግ፣ ግጥም የአንተ እጣ ፈንታ አይደለም፤ ለድርሰት አልተፈጠርክም” ብዬ በግልጽ እናገራለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የለሰለሱ መሬቶች… ቢዘሩባቸው የሚያበቅሉ ከሆኑ አበረታታቸዋለሁ፡፡ በዚህም መልኩ ብዙ ታዳጊዎችን አውጥቼዋለሁ፡፡ በዚህም ደስ ይለኛል፡፡
ዛሬ ለማህበርህ በስጦታ (ከእነ ቅጂ መብቱ) ያበረከትካቸው መፃህፍት ምንድን  ናቸው?
አንደኛው መጽሐፍ ጆርጅ ኦርዌል የሚባል የእንግሊዛዊ ደራሲ ስራ ነው። “Animal Farm” በሚል መፅሃፉ ይበልጥ ይታወቃል፡፡ እኔ የተረጎምኩት “1984” የተሰኘ ሌላ ሁለተኛ መፅሐፍም አለው። መፅሐፉ ኮሙኒዝም የሚባለውን ርዕዮተ ዓለም በደንብ አድርጎ የሚተችና የሚያጋልጥ ነው። “ዩቶጵያ“- የማይሆን እሳቤ እንደሆነ ያጋለጠበት ነው። ኦርዌል  መፅሐፉን ሲፅፈው የራሱን ዓለም ሰርቶ ነው፡፡ ገፀ ባህሪያቱ የራሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን በራሱ ዓለም ውስጥ ሆኖ ሶሻሊዝምን --- ኮሚኒዝምን ይተቻል፡፡ ሀሳቡ ምን መሰለሽ ---- ኮሙኒዝም በ1984 ካልተገታ ዓለም እንደዚህ ትሆናለች የሚል እሳቤ ነው፡፡ ደንበኛ መፅሀፉ (ኦርጅናሉ ማለቴ ነው) አንብቦ ለመረዳት--- እንግሊዝኛውን እንግሊዞች እንኳን አንብበው መረዳት አይችሉም፡፡  ይህ ፅሁፍ እንግሊዝኛ ለማያነቡ የአገሬ ሰዎች ወደ አማርኛ ቢመለስላቸው አንዳች ፋይዳና ትምህርት ያገኙበታል በሚል ነው የተረጎምኩት፡፡ ወደ አማርኛ የተረጎምኩት ግን አሁን ባለሁበት ሁኔታ ሳይሆን  ቀደም ብሎ ነው፡፡ ብዙ ገፆች አሉት፡፡ ራሱን አማርኛውን ለመረዳትም ያስቸግራል፤ ምክንያቱም የተተረጎመው በኦርዌል የቋንቋ ከፍታ ነው። ለአማርኛ ቋንቋ ዕድገትም አስተዋፅኦ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። መፅሀፍቱ ዝም ብለው ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ ዛሬ ባይታተም የዛሬ ዓመት ወይ የዛሬ 10 ዓመት፣ ወይም 20 ዓመት የልጅ ልጆቼ ሊያሳትሙት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የኔ ፍላጎት አንደኛ አንባቢ ዘንድ እንዲደርስ፣ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር እንዲገለገልበት ስለፈለኩ ነው፤ ከእነ አዕምሮ ንብረት ጥበቃው  ያበረከትኩት፡፡
አሁንም ታመህ እንኳን  በመፅሔት ላይ ፅሁፎችህን  እያየሁ ነው ---
አዎ አልፎ አልፎ እጽፋለሁ። ባለፈው ቅዳሜ “ጊዮን” መፅሄት ላይ አንድ ፅሁፍ አለ እይው። ስለ ቋንቋ ነው። ቀጣዩ ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት ይወጣል። ከዛ በፊት በንባብ ዙሪያ ፅፌ ነበር። አጫጭር ልቦለዶች --- በነገራችን ላይ ግጥምም እፅፋለሁ፡፡ ለማህበረሰቡ መዝናኛ ይሆናሉ፣ ያስተምራሉ ይለውጣሉ ብዬ ወደ አማርኛ ከመለስኳቸው መጻህፍት መካከል አንዳንዶቹን ልንገርሽ። “The power Now” (የአሁንነት ሀይል) አንዱ ነው። ሌላው "የአምላክ ፈዋሽነት ሀይል” (The healing power of God) የተሰኘ ነው፡፡ ሶስተኛው "የመጨረሻ መጀመሪያ" የተሰኘና በጄምስ ሬድፊልድ የተጻፈ እጅግ መሳጭ መፅሀፍ ነው። “የአሁንነት ሀይል” አማርኛውን ገበያ ላይ አታገኚውም - ጠፍቷል። እንግሊዝኛው በ47 ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ወደ 30 ሚሊዮን ቅጂ ተሸጧል። አሁንም ኦን ላይን እየተሸጠ ነው። አማዞን ላይ ብትገቢ ታገኚዋለሽ። ኦሪጂናሉ “ዘ ሰላስታይን ፕሮፌሲ” ይባላል። በቀጥታ ወደ አማርኛ ስትመልሺው “የሰማየ ሰማያት ትንቢት”  ነው የሚለው። እኔ ግን “የሰማየ ሰማያት ትንቢት” ብለው ብዙ ወጣቶች እንደምታውቂው መንፈሳዊ ነገር ማንበብ አይወዱም፤ እናም ይገፈትራል በሚል እሳቤ ርዕሱን  “የመጨረሻው መጀመሪያ” አልኩት፡፡ ሌሎችም አሉ።
አንተ ካሳለፍከው የህይወት ልምድና ተሞክሮ አንፃር የአሁኑን ትውልድ ሁኔታና ክፍተት እንዴት ታየዋለህ?
ሲጀመር በየትኛውም ጊዜ ቢሆን የትውልድ ክፍተት ይኖራል። የትውልድ ክፍተት መኖር በዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ነው። ጥንትም በአያቶቻችን፣ በአባቶቻችን የትውልድ ክፍተት ነበር። በእኛና በአሁኑ ትውልድም መካከል ክፍተት አለ። በሚመጣውና በአሁኑ ትውልድም ክፍተት ይኖራል፤ ተፈጥሮአዊ ነው። ችግሩ ምንድን ነው? እኛ በዚህ ዘመን ክፍተቱን ለማጥበብ ጥረት አላደረግንም። ክፍተቱ እንዲጠብ ለማድረግ የእኛን ጥረት ይሻ ነበር። የሚገርምሽ ነገር በብዙ መድረኮች ላይ ተናግሬዋለሁ፤ ዛሬም ደግሜ እናገረዋለሁ። ይህ ትውልድ የታመቀ ሀይል ነው።
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ 130 ሚሊዮን ይደርሳል ይባላል። 110 ሚሊዮን ሊሆንም ይችላል። ነገር ግን ከዚህ 110 ወይም 130 ሚሊዮን ህዝብ መካከል 70 በመቶው ወጣት ነው። ይህ ትውልድ ደግሞ -- የታመቀ ሃይል ነው ብዬሻለሁ። ቢያሳዩት ያያል፣ ቢመክሩት ይመከራል፣ ቢያሰሩት ይሰራል። --- ያጣው የሚያሰራው የሚመራው አካል ነው። ትውልዱ ራሱን መምራት ይችላል፣ የራሱን ህግ መጻፍ ይችላል፣ የራሱን መንገድ መቀየስ ይችላል። ስለዚህ የትውልዱን ክፍተት ማጥበብ ያቃተን እኛ አባቶች ነን። እኔ ብዙ ወጣቶችን በመምከርና በመቅረብ ከተያያዙት የተሳሳተ መንገድ መልሼአለሁ፡፡ በዚህ በጣም ደስ ይለኛል። ስለዚህ ችግሩ ከትውልዱ አይደለም። ከእኛ ከትልልቆቹ ነው። ትውልዱ  እድለኛ ነው፤ በብዙ ነገር ከእኛ ይሻላል።
ለምሳሌ በምን -- ከእናንተ ይሻላል?
አይገርምሽም… በአእምሮ፣ በቁመናና በመልክ ከእኛ ይሻላል። ይሄ ተፈጥሮአዊ ነው።
የማርክሲዝም ፍልስፍና ምን ይላል መሰለሽ? የዳይሌክቲክ ህግ የሚሉት አለ፤ ሁልጊዜ ከቀላል ወደ ውስብስብ፣ ከትንሽ ወደ ብዙ ነው ሂደት ያለው። የዛሬው ትውልድ አዕምሯቸው ከእኛ የተሻለ ነው። የተሻለ የመቀበል ችሎታ አላቸው። በዛ ላይ ደግም አስቢው… ቴክኖሎጂ ረድቷቸው በቴክኖሎጂ ተዓምር መፍጠር ይችላሉ። ዋናው ነገር ወጣቱን ወደ ንቃተ ህሊና ማድረስ ነው። አንደኛ ነገር ወጣቱ የሚመራው በአዕምሮው ሳይሆን በራሱ መሆኑን መገንዘብ አለብን። አዕምሮ ለሰው ልጅ መገልገያ እንጂ ሰው የአእምሮው መገልገያ አይደለም። ሰው እንደ ሰው ነፍሱ አለ፤ ስጋው የነፍሱ ማደሪያ ቦታ ነው። ሌላው የሰው ልጅ አባል አካላት፣ እጅ፣ እግር፣ አይን፣ አፍንጫ-  የሰው ልጅ  የነፍሱ አገልጋዮች ናቸው። ከነፍሱ መገልገያዎች አንዱ አዕምሮ ይባላል። ስለዚህ ሰው አዕምሮን መጠቀም መገልገል አለበት።
አሁን ደግሞ ስለ ልጅህ ትንሽ አውጋኝ፡፡ ማህሌት አፈወርቅ--- በልጅነቷ ነው አይደል መፅሐፍ ያሳተመችው?
ማህሌት እኮ በቅርቡ ያሳተመችው ሁለተኛ መፅሀፏ ነው። ማህሌት የመጀመሪያውን የግጥም መፅሀፍ ያሳተመችው በ12 ዓመቷ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ በ12 ዓመት የግጥም መጽሐፍ ያሳተመ የለም። የሪከርዱ ባለቤት ናት ማለት ነው። ከእሷ በፊት ታገል ሰይፉን ታውቂዋለሽ? በ16 ዓመቱ ነው ያሳተመው። ማህሌት ሁለተኛውን መፅሐፏን በ20 ዓመቷ ነው ያሳተመችው። የሚደንቅሽ ርዕሱ ራሱ “ሀሳብ ነኝ” የሚል  ነው። ገረሜታን የሚጭር ነው። በነገራችን ላይ ሰዓሊም ናት። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስዕል ት/ቤት፣ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበረች። አሁን በኮሮና ረቂቱ ምክንያት አቋረጠችው።
“ረቂቱ” -- ምንድን ነው…?
ረቂት ማለት ቫይረስ ማለት ነው። በዚህ በኮሮና ረቂቱ ምክንያት ቤት ሆና ግጥም ትፅፋለች፤ ስዕልም ትስላለች…በጣም ጎበዝ ናት።
መቼም  ወደ ስነ- ፅሑፍ የሳባት ያንተ ተፅዕኖ ይመስለኛል…..
 የኔ ተፅዕኖ የለባትም። ከእርሷ ጋር ሰባት ልጆች ናቸው ያሉኝ። ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ቢኖረኝ፣ ሁሉንም ደራሲ አደርጋቸው ነበር። ሲጀመር ያ ሊሆን አይችልም።  ስነፅሁፍና ስነ ስዕል ከራስ ፍላጎትና መገፋት የሚመጣ ነው። እኔ ያደረግሁት ፍላጎቷንና ህልሟን በማየት ሁኔታዎች ማመቻቸት ነው። መሆን የምትፈልገውን እንድትሆን ረድቻታለሁ።
በጡረታ ደሞዝ እየኖርክ እንደሆነ ነው የሰማሁት-- የጡረታ ገንዘብህ ብዙ ነው እንዴ--ማለቴ ዘና አድርጎ የሚያኖር ነው? እንዳንተ ያለ ታዋቂ ሰው ሲታመም እኮ የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ ድጋፍ ይሰባሰብለታል፡፡ አንተ ግን መታመምህም አልተሰማም--- ለምንድን ነው?
ለምን መሰለሽ….. ከማህሌት ጋር ሰባት የተባረኩ ልጆች አሉኝ። ከሰባቱ ስራ ያልያዘችው ማህሌት ብቻ ነች። ስድስቱም ስራ አላቸው፡፡ ከስድስቱ ዘጠኝ የልጅ ልጅ አግኝቻለሁ። ሶስቱ አግብተው ሶስት ሶስት ልጅ አበርክተውልኛል። እድሜና ጤና ብድሩ ይድረሳቸው፤ እነሱ ናቸው ተንከባክበው የያዙኝ። ያለ ምንም ችግር ነው የምኖረው። ቸግሮኝ አያውቅም። ጡረታ ከወጣሁ 23 ዓመቴ ነው።
የምትኖረው ከባለቤትህ ጋር ነው ወይስ--?
 አዎ 47 ዓመት ነው አብረን የኖርነው። እና ፈጣሪ የሰው መውደድ ስለሰጠኝ “ጋሽ አፈወርቅ ለመድኃኒት መግዣ ይሁን”  እያሉ 5 ሺህ ብር፣  7 ሺህ ብር፣ 10 ሺህ ብር ይልኩልኛል። ጭራሽ የገንዘብ ጉዳይ ጭንቅ ሆኖብኝ አያውቅም። አሁንም ቢሆን ምንም እርዳታ አልፈልግም። ሁሉም የከንቱ ከንቱ መሆኑን ተረድቻለሁ። ሲጀመርም የቁስ አካል ፍላጎት አልነበረኝም።
የራስህ መኖሪያ ቤትስ አለህ?
የመንግስት ቤት አለኝ፡፡ ቤቴን በላይ በሰማይ እያዘጋጀሁ ነውኮ። አንድ ነገር ሳልነግርሽ ማለፍ አልፈልግም። ስማቸውን ባልጠቅስም፣ የአከርካሪ ዲስክ መንሸራተት ህመሜን ለማሳከም፣ በራሳቸው መጓጓዣ ደርሶ መልስ የአየር ትኬት ቆርጠው ባንኮክ ወስደው አሳክመው፤ ከዛም ህክምናው በጣም አዳጋች በመሆኑ በፊዚዮቴራፒ፣ በአካል እንቅስቃሴና በመድሃኒት ብታከም እንደሚሻል ተመክሬ ነው የተመለስኩት። እዚህ አገር ብታከም ኖሮ ቀዶ ህክምና እናድርግ ብለው ሕይወቴም ሊያልፍ ይችል ነበር። ለ20 ቀን ደረጃውን በጠበቀ ሆቴል አኑረውኝ፣ ህክምና አግኝቼ እንድመለስ ያደረጉት ጥሩ ወዳጆቼ ናቸው፤ ስማቸው ቢጠቀስ ደስተኛ እንደማይሆኑ አውቃለሁ፤ ቢሆንም በደፈናው አመሰግናቸዋለሁ።
በመጨረሻ ---"ፈጣሪ ዕድሜ ቢሰጠኝ ይህን አደርግ ነበር" የምትለው ነገር አለ?
ምንም የለም! ለምንድነው ከዚህ በኋላ መኖር የምመኘው? ለገንዘብ ነው? ለሀብት ነው? ያላየሁት ነገር የለም። እኔ እግዚአብሔር አምላክ ከስቃይና ከህመም ትንሽ በረድ አድርጎልኝ፣ በሚጠራኝ ጊዜ ብሄድ ደስ ይለኛል። በነገራችን ላይ የዛሬ 3 ዓመት የቁም ኑዛዜዬን ሁሉ ጨርሼ፣ ሀብት ንብረት የለኝም ነገር ግን ኑዛዜዬ በውልና ማስረጃ በኩል ለቤተሰቤ ተሰጥቶ ዝግጁ ሆኜ እስክጠራ እየጠበቅኩኝ ነው።


Read 1786 times