Tuesday, 08 December 2020 13:40

«የማይሸተው ጠረን»

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(9 votes)

  ፩
ያመኛል።  ከእግር ጥፍሬ እስከ ጭንቅላቴ ድረስ ትኩሳትና የሚያደነዝዝ የህመም ስሜት ይሰማኛል።  ዝንተ ዓለም ሆድን የሚጎረብጥ ህመም ... አስፋልት ደርዝ ላይ የተቀመጡ ልጆች አሉ፣  ለእነሱ ሳንቲም የሚወረውር ወጣት ደረቱን ነፍቶ (ምናልባት በወረወረው ሳንቲም ምክንያት) ይሄዳል።  የፀሃዩን ግለት በጃንጥላ የምትከልል ጠይም ውብ እንስት እያየሁ... እራመዳለሁ። ከዚያ ጠዋይ ሽማግሌ  የሚነጥለኝ ተዓምር እየፈለኩ እራመዳለሁ። ህመሜን እያሰብኩ እራመዳለሁ። ትላንት ላይ እንደመሸገ ድኩም  ሽማግሌ እየተክተለተለ ከሚንጠኝ  ጭንቀት ጋር ...እራሴን እጠይቃለሁ።  ስናደድ እረጅም መንገድ የመጓዝ ልምድ አለኝ። አንዳንዴ ንዴቴን  በእግሮቼ መዛል የምተፋው ይመስለኛል። ዛሬም እንደሁሌው ለንዴቴ ምክንያት የሆነው እርጉሙ አባቴ ነው (ይኼን በማለቴ ቅር ትሰኙ ይሆናል! ቢሆንም በፍፁም ልሰርዘው አልሻም።  ስፅፈው አንዳች ጥሩ ስሜት ተሰምቶኛል) ...
ለመሆኑ አባቱን የሚጠላ ልጅ አለ? አዎ! ከማንም በላይ አባቴን እንደምጠላ  ታውቃላችሁ? ዘውትር ስለሚወርፈኝ እጠላዋለሁ። ቀን ከሌለት በነገር አንጎሌን ስለሚያዞር እጠላዋለሁ። በአጠቃላይ ጥላቻ እንደ
ዛር የሰፈረብኝ ነኝ... ፍቅር የማላውቅ... መውደድ የሚያቅረኝ ዓይነት ሰው ነኝ...
አይኑን ማየት ያሳምመኛል። ድምፁን መስማት ያስከፋኛል። ደስታው ሳይቀር ሃዘኔ ነው። ምቾቱ እንደ እሳት ላንቃ ያቃጥለኛል። ምንም ሳይናገር በዝምታው እናደዳለሁ... ሲናገር ንግግሩ አይጥመኝም።  ይኼኔ እታመማለሁ። መላው አካሌ በትኩሳት ይደነዝዛል። እንባ ከዓይኔ መውረድ ይጀምራል። እልህ፣ ሳግ አንቆ ይይዘኛል። እራሴን እጠላለሁ። ዓለምን እጠላለሁ። ከመቼውም ጊዜ በላይ አባቴን እጠላለሁ። ህይወቴ ባዶ ይሆንብኛል። የምንምነት ጅራፍ ይገርፈኛል። በጥላቻ መስቀል ላይ እሰቀላለሁ። ታዲያ ያለ ምክንያት ጠዋት ተነስቶ  እንዲህ አለኝ:-
“የእንግዴ ልጅ”
ተናደድኹ። መናደድ የፈለገ መረዳት ምኑ ነው?  ሊቃጠል የሚያኮበኩብ ጅስም ማስተዋል የት ያውቃል?  ብቻ ተነስቼ እዚህ አስፋልት ላይ መራመድ እንደጀመርኩ አስታውሳለሁ። ማንንም ማየት አልፈለኩም።   የማንንም አፅናኝ ቃል የተጎዳ ልቤን እንደማይጠግን አውቃለሁ። በዝምታ መራመድ ብቻ። አለም ላይ እንደ ተራሳ ግዑዝ ሆኜ በእግሮቼ መንደርደር፣ ቁልቁለቱን። ብቻዬን አቀበቱን መውጣት ሆነ።  መላው አካሌን ይደክመኛል። ብቸኝነቱ ይታክተኛል። እግዜር ስለ  ምን  እንዲህ ብቸኛ እንዳደረገኝ እጠይቃለሁ። ስለ ምን አልቦ ዘመድ አደረገኝ? አምላክ ጠላቴ ይመስለኛል። አዎ! እግዜርን መክሰስ ያምረኛል። ልቤ ሰው ትናፍቃለች። ነፍሴ የሚሞቅ እቅፍ ትሻለች። ሁሉም ነገር አድካሚ ይሆናል። እንባ ያዘሉ አይኖች፣  በእርምጃ የተዳከሙ እግሮች... የብቸኝነት ብርድ የሚፃማው ጅስም ታቅፌ አዘግማለሁ...
ሰዎች እያወሩ ሲያልፉ አያለሁ... ሰዎች ተቃቅፈው ያዘግማሉ። ደማቅ በሆነ ፍቅር ተያይዘው ይከንፋሉ። እኔም ብቻዬን እራመዳለሁ። ከንዴቴ ስበርድ ወደ ቤት መመለስ እንዳለብኝ እያሰብኩ ነበር።
ተመልሻለሁ... ነገር ግን አንዳች የሚያስጨንቅ ነገር ሰፈረብኝ.. ፊቴን ደጋግሜ አሻለሁ። ክፍሌ ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ለመንቀሳቀስ እሞክራለሁ። ሁሉም ነገር ይጠፋኛል....
ዓለም ዳርቻ እንደ ቆመ ህፃን አይኖቼ ይቁለጨለጫሉ። ከንፈሬን እመጣለሁ።
 ከዚያች  ቀን ጀምሮ ህይወቴ ውሉ እንደጠፋበት ልቃቂት ተወሳሰበ። መዓልት በእኔ ጨለመ። ስቃዬ ኑረቴ ላይ ነገሰ። ምቄ ብዝቶ  ሰው ሁሉ ተጠየፈኝ። አንዳች መጥፎ ነገር ወረረኝ። የሚሳፍር  ክስተት ሰርክ  በህይወቴ ተከሰተ።
መኖሬን ጠላሁ። ህይወትን ጠላሁ። ከትንሿ   ክፍሌ ብቻዬን መሸሸግን ምርጫዬ አደረኩ። ሰው ሁሉ ከጀርባዬ ይተፋብኝ ጀመር። ይሄ ልጅ ምን ነካው የሚለኝ ሰው በዛ።
ሁሉም ነገር ተመሰቃቀለ... የቁም ቅዠት ... ከሞት የከፋ አሳፋሪ ክስተት  በእኔ ተላገደ... ህመም ይሁን ልክፍት... ነገርየው ታጣ. .. ሰይጣን ይሁን አምላክ... ከማን እንደመጣ አልታወቀም...
በቁሜ ብዥ ይልብኛል። እነዚያ የምወዳቸው የብርሃን ዘሃዎች እየጠፉ... እየጠፉ... መጡ... ከዋክብት አያበሩም... ጨረቃ ተደብቃለች... ፅልመት በወረሰው ዓለም እንዳክራለን...እዳክራለሁ
[እየቀጠልኩ...]
• • •
ደጋግሜ ህልም አያለሁ። አንዳች ጥቁር ነገር ከኋላዬ እያባረረኝ ምናምን። አንዳንዴ ከገደል ለመውጣት ስለፋ እነቃና  ላብ ያሰምጠኛል ...አይኖቼ በርበሬ ይመስላሉ። አካሌ ይዝላል።

እንዲህ ነበር የሆነው::
ጠንካራ  ሽታ  ሰፈሩን መበከል ከጀመረ ሰነባበተ። አፍንጫን የሚሰነጥቅ ከባድ ሽታ፣ አላፊ አግዳሚውን የሚያስነጥስ፣ ሳል የሚለቅ ከባድ ሽታ መጣ። የዚህ ሽታ ምንጭ ማን እንደሆነ ለጊዜው  ባይታወቅም፣ ሰፈሩ ገምቶ አላሳልፍ አለ። ያለፈው ሰው ሁሉ ይተፋል። አንዳንዴ “ምንድነው የሚሸተው” እየተባባሉ ይጠያየቃሉ። ለስራ  ለሊት የሚነሳ አባቴ፤ “አቤት ግማት” እያለ ሃክታውን ማፍረጥ ከጀመረ ሰነባብቷል። ይሄ ነገር ለእኔ አዲስ ነበር። ምክንያቱም ይሄ ሽታ የሚሉት ነገር ለእኔ በፍፁም የሚሸት አልነበረም። ታዲያ ሁሉም በዚህ ባልታወቅ ሽታ ሲበከሉ  አይ ነበር። ሁሉም ትፋታቸውን ጥለው ሲሄዱ እሰማ ነበር። እዛች ትንሽ ክፍሌ ውስጥ ቁጭ ብዬ ሁሉንም ነገር እከታተላለሁ።
ስለ ምን እኔን አይሸተኝም እያልኩ ማሰብ ቀጠልኩ።
ሁሉም ነገሮች ትናንት በሚመስል ግራጫ ኩነት የተድበሰበሱ ህመሞች ነበሩ። ሰው ሁሉ በዚያ ሽታ ተበከለ። ብዙዎች ግራ ገባቸው።  እዚህ መንደር ውስጥ እንዲህ የሚገማ ነገር ከየት መጣ? እያሉ እርስ በእርሱ ይተያያሉ። አንዳንዴ ከመንደሩ ፊት የነበረውን ቱቦ እያሳበቡ፣ እዚያ ላይ ሽታውን ማላከክ ጀመሩ።
አሁንም ደጋግሜ  አስባለሁ።
እኔን ስለ ምን አይሸተኝም?
ታዲያ በዚህ ሁናቴ ውስጥ ሆኜ እኔም ግራ መጋባት ጀመርኩ። ይሄ ሽታ የሚሉት ነገር ከእኔ አካል  ይሆን የሚመጣው ስል  እራሴን ጠረጠርኩ።  ልብሴን አገላብጬ ማሽተት ጀመርኩ። አንሶላዬን፣ ብርድልብሴን ሁሉ አውጥቼ አጠብኩ። አፍንጫዬ ወደ ገላዬ ማነፍነፍ ጀመረ። ታዲያ ምንም ሊሸተኝ አልቻለም።  አንዳንዴ የእጣን ሽታ ውል ይልብኛል። ከየት እንደመጣ የማላውቀው የእጣን ሽታ ያውደኛል። ታድያ ስለዚህ ሽታ እያሰብኩ እግረ መንገዴን ቀጠልኩ።
በአጠገቤ የሚያልፉት ሰዎች አፍንጫቸውን ሲይዙ አየሁ። አንዳንዶች ያስነጥሳሉ።  አንዳንዶች እያሳሉ  ያልፋሉ። አንዳንዱ ደሞ “እፍፍፍፍፍፍ” እያለ ይሄዳል።  ይኼኔ ጥርጣሬዬ  ልክ እንደሆነ አወቅኩ። ይሄ አፍንጫ የሚሰብር ሽታ ከእኔ አካል እንደሚወጣ ገባኝ። ከእኔው አካል ነበር ይኼ አፍንጫ የሚሰብር ግማት የሚወጣው። እራሴን ተጠየፍኩ። እቤቴ እስክገባ ድረስ ጨነቀኝ። ክፍሌ ውስጥ መሽጌ እስክቀመጥ ድረስ ጠበበኝ። አንድ ሽማግሌ አጠገቤ ደርሶ አክታዉን ተፍቶ አለፈ። ተመልሼ እኔን እንዴት ሊሸተኝ አይችልም ስል እራሴን እጠይቃለሁ። ምናልባት አፍንጫዬ አንድ ችግር ይኖርበት ይሆናል እንጂ ሽታው በሄድኩበት ሁሉ እኔን መከተሉን አልተወም።  በአጠገቤ የሚያልፉ አንዳንድ ሰዎች፤ “ሽንት ቤት አለ እንዴ እዚህ?” ይላሉ። የሽንት ቤት ጠረን ነው እኔ ጋ ያለው ብዬ አሰብኩ።
ስለዚህ ሽታ እያሰብኩ አይኔ እንባ ያረግዛል። አንዳንዴ ብቻዬን አወራለሁ። ብዙ ጊዜ ስለዚህ ሽታ ተብሰለሰልኩ።
ቀናት ያልፋሉ። ከቤት መውጣት አቆምኩ። ከማንኛውም ሰው ጋር መገናኘት አልቻልኩም። ሽታዬ አጠገቤ ሰው የሚያስቆም አይደለም። ማንም ሰው ያን አፍንጫ የሚቆርጥ ሽታ ችሎ አጠገቤ አይቆምም። ይባስ ብሎ ከእሩቅ  መሽተት ጀመረ። የሆዴ ህመም ብሶ ከፍተኛ የጩኸት ድምፅ ያሰማል። ፊንጢጣዬ አካባቢ የሚጮህ ነገር ነበር። ፈስ  እየወጣ መሆኑ ባይታወቀኝም፣ይሄ አፍንጫ የሚቆርጥ ሽታ ከፊንጢጣዬ ውስጥ እንደሚወጣ ገባኝ። ሌሊት ሌሊት በጣም ያልበኛል። ይሄ ላብ የሚሸት ስለሚመስለኝ ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ ሽቶ መቀባት ጀመርሁ። ይሄም መፍትሔ ሊሆን አልቻለም።
 ሽታው ከቤታችን ፊት ለፊት ያሉት ሱቆች ውስጥ ይገባል። እኔም የሚያስል ሰው ስሰማ መሸማቀቅ ጀመርኩኝ። አባቴ መሳደቡን ቀጥሏል። እርግማኔ ነው እንዲህ እንድትሸት ያደረግህ አለኝ። እንዲህ ያለኝ ዕለት አምርሬ አለቀስኩ። ስቃዬን እያየ  በእርግማኑ የሚኮራ አባት መስሎ ታየኝ። የማላውቃት እናቴን  ናፈቅሁ። ሰርክ ማልቀስ ሆነ ስራዬ። የሰፈሩ ሰው ሁሉ ሽታው የሚወጣ ከእኔ እንደሆነ አወቀ። ተሸማቀቅኹ፤  ተሳቀቅኹ.. ትልቅ ፍራቻ ልቤ ላይ ነገሰ። መኖር አስጠላኝ። እራሴን ለማጥፋት አሰብኩ። በገመድ እራሴን ልሰቅል የቤታችን አጥር ላይ የተቋጠረውን ገመድ ፈትቼ ወደ ክፍሌ ገባሁ። ከዚህ ሽታ ጋር ከመኖር ሞት ሰላማዊ መፍትሄ እንደሆነ ማሰብ ጀመርኩ። ግን ቅዋዉን አጣሁ። አቅሙ ከዳኝ። ምናልባት ሊጠፋስ ቢችል ህይወት መክኖ.. ያለ ምንም ስራ ተራ ሆኜ ሞቼ  መረሳቴን እያሰብኩ፣ ሞት አማራጭ እንዳልሆነ ደጋግሜ ለራሴ መንገር ቀጠልኩ። ገመዱን ይዤ አሰላስላለሁ። ህይወቴን ለማትረፍ ያለኝን አማራጭ አያለሁ...
ገመዱን አልጋዬ ስር ደብቄ ምናልባት ሽታው እያደር ሊቀንስ... እና ሊጠፋ ይችላል የሚል  ተስፋ አደረብኝ። ህይወት ያጓጓችኝ ይመስላል። ሁለተኛ እድል ፈለግሁ። ድጋሜ መኖር፣ ድጋሜ ህይወት  አዲስ ሆነች።
አንድ ቀን  ሁሉንም ነገር ልነግረው አሰብኩ - ለአባቴ። ሳሎን ቁጭ ብሎ ቴሌቭዥን ያያል። ፊት ለፊቱ ቁጭ አልኩ። ለአፍታ ዝም አልኩኝ። ጥቁር መልኩ ወዝቷል።  የግንባሩ መስመሮች ደምቀው ታዩኝ።  የሸሚዙን እጅጌ ወደ ላይ ሰብስቦ፣ ክሳዱን አቁሟል። አይኑ እንደ በርበሬ ቀልቷል። አይኖቹ አተኩረው እያዩኝ ለምን ፊቱ እንደተቀመጥኩ የሚጠይቁ  ይመስላሉ።  
ጥቂት ተንተባትቤ መናገር ጀመርኩ።
“እኔ እኮ ይሄ ሽታ የምትለው ነገር አይሸተኝም... እናንተን የሚሸታችሁ ነገር ፍፁም ለእኔ አይሸትም። ምናልባት ሆስፒታል ሄጄ ብታየው መፍትሄ ሊኖረው ይችላል፤ ሳንቲም ስጠኝና..."
አቋረጠኝ... “የምን ሃኪም ቤት? ለምን አትሞት! እኔ ሳንቲም የለኝም” አለኝ...
ተነስቼ ወደ ክፍሌ ገባሁ። ጥላቻዬ ትክክል እንደነበር ገባኝ። በእርግጥም ይሄ ሽማግሌ የተረገመ ነው። በእርግጥም ሰይጣን ሽማግሌ ነው።
ውጪ እየወጣሁ ሰዎችን መጠየቅ ጀመርኩ። የማላውቃቸውን ሰዎች ሳይቀር ምን ምን እንደሚሸታቸው እጠይቃለሁ። ዝም ብለውኝ አፍንጫቸውን እየነካኩ ያልፋሉ። አንዳንዶች እየሳቁ “የሽታውን ታሪክ እናውቀዋለን” ይሉኛል። እኔ ምንም እንደማይሸተኝ ምዬ ተገዝቼ እነግራቸዋለሁ። ይስቃሉ። ሲስቁ ይበልጥ እናደዳለሁ።
“ዞር በል ወደዚያ ግማታም” ይሉኛል። ዐይኔ በእንባ ተሞልቶ “አይሸተኝም እኮ” እላቸዋለሁ። እየሳቁ ያልፋሉ። ልቤ ቆስሎ ወደ  እዚያች በኣቴ ገብቼ እደበቃለሁ።  እንዲህ አይነት ነገር በእኔ መድረሱ እያስከፋኝ ተጠቅልዬ እተኛለሁ። እንቅልፌ ባለ ብዙ ህልም ነው። ብዙ ጊዜ የምነቃው ሰውነቴ ሁሉ በላብ እርሶ ነው።  በዚህ መሃል የአባቴን ትፋት እሰማለሁ። “አቤት ግማት” ይሉት ቋንቋው ልቤን ይረብሻል።
ሰዎች ሁሉ ስለዚህ ሽታ በሹክሹክታ ማውራት ጀመሩ። ሩቅ ዘመዶቼ ሳይቀሩ፣ ይሄን ሰምተው እኔን ለመጠየቅ ወደ ቤት ጎረፉ። ተሸማቀቅሁ። ፊቴ በሃፍረት ቀላ። የአዕምሮ ሀኪም ሊያየኝ እንደሚገባ ነገሩኝ። ይሄን ያለችው የአጎቴ ሚስት ናት።
ሀኪም ጋ ቀረብኩ። ጠይም ዶክተር ነው። ፊቱ ላይ ብዙ ፈገግታ አየሁ። የመጠየፍ ነገር አላየሁበትም።
“ምንድነው ችግርህ?” አለኝ።
“ሽታ”
“የምን ሽታ?”
“በፈስ መልክ ከፊንጢጣዬ የሚወጣው ጋዝ ከሩቅ ይሸታል። አፌም ሰው አያስቀርብም። ብዙ ጊዜ ሆዴን ያመኛል። እኔ ግን አይሸተኝም።” አልኩት።
“አንተ ካልሸተተህ ታዲያ እንደሚሸት በምን አወቅህ?”
“ሰዎች እኔ አጠገብ ሲደርሱ ይተፋሉ። አንዳንዶቹ አፍንጫቸውን እየያዙ “ እፍፍ” ይላሉ። በዚህ ጊዜ ነው ሽታው ከእኔ እንደሚወጣ  የተረዳሁት።”
“ትታከማለህ አይዞህ” አለኝና ወረቀት ላይ አንድ ነገር ፅፎ ሰጠኝ። አነበብኩት፤ “somatic delusion” ይላል።
“ምርመራ አዝልሃለሁ” አለኝ። አፍንጫውን መንካት ሲጀመር አተኩሬ አየሁት። ተረዳኝና “ደግሞ እኔንም ሸቶት ነው ብለህ እንዳታማኝ” አለኝ። ስቄ ዝም አልኩ፡፡
[ድ ህ ራ ይ]
አምኑኤል ሆስፒታል አስገቡኝ። የማየውን ሰው ሁሉ ስለዚያ ሽታ እጠይቃለሁ። “አይሸተኝም” እያልኩ እንዲያምኑኝ  እለማመጣለሁ።  ብዙዎች አፍንጫቸውን እየነካኩ በዝምታ ያልፋሉ።  ታዲያ በዚህ ጊዜ እንባ ጉንጮቼን ያርሳል።
“ሸቷቸው ነው የተፉት ተመልከቱ" እያልኩ አለቅሳለሁ። የሆስፒታሉ ዘበኛ አጠገባቸው እንዳልደርስ አስጠንቀውኛል።  እንደ ህፃን እያለቀስኩ ከታማሚዎች ጋር እቀላቀላለሁ።
እነሱም “እፍፍ” እያሉ ይርቁኛል። ይኼኔ አንዳች የመጨነቅ ስሜት ይጠናብኛል። ሁሌ የሚገርመኝ የሃኪሜ ነገር ነው። አፍንጫውን ሳይነካ በፈገግታ ተቀብሎ ይጠይቀኛል።
“አሁንም ሽታው አለ” ይለኛል።
“እኔን አይሸተኝም! ሰዎች ግን የሚሸታቸው ይመስለኛል”
ሁሉም ሰዎች ይሸሹኛል።  ትንሽ የሚጥጠጉኝ እንኳን አፍንጫቸውን እየነካኩ፣ አንዳንዴ ዞር ብለው እየተፉ ነው።
ታዲያ መንፈሴ ከተዳከመ ቆየ። እዚያው አልጋዬ ላይ ሆኜ “አይሸተኝም እኮ” እያልኩ መጮህ ጀመርኩ።
“አይሸትም... አይሸትም”
ነርሶች መጥተው መርፌ ይወጉኛል። ወደ ጥልቅ እንቅልፍ እገባለሁ። አዲስ ህልም ይታኛል። አዲስ ተስፋ ይታየኛል። ስነቃ ከመዳን የነገ ተስፋ ጋር ሆኜ ነው። ስነቃ ሽታው እንዲጠፋ እየተመኘሁ ነው። ስነቃ ልቤ በሃዘን ተጎሳቅሎ ነው። ስነቃ አንድን ሰው የማቀፍ ጉጉት አድሮብኝ ነው።
አዎ! አንድ ሰው የማቀፍ... አንድ ሰው የማፍቀር ጉጉት... ከሰው ታዛ የመከለል ጉጉት ... ከሰው ጋር ብቻ... ከሰው ጋር... ነገን መናፈቅ... በነገ ውስጥ የመዳን ተስፋ... የመዳን ጉጉት...


Read 2242 times