Tuesday, 08 December 2020 13:48

ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የካንሰር ህክምና ማሽን ስራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በአፍሪካ በጥቂት አገራት የሚገኘውና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው የካንሰር ህክምና ማሽን ሰሞኑን ተመርቆ ስራ ጀመረ። “ሊየር ኦክስለሬተር” የተሰኘውና ጨረር በማመንጨት ካንሰርን የሚገድለው ይኸው ማሽን ባለፈው ሳምንት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ማዕከል ተመርቆ ነው ስራ የጀመረው።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የካንሰር ህክምና እንዲስፋፋ ከፍተኛ  ስራ በማከናወን፣ በመትጋት የሚታወቁት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰው  ወልደሃና፣ አራቱ ቀደምት የካንሰር ሀኪሞች እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሃላፊ፣ ዶ/ር ዳዊት ወንድምአገኝና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።
የማሽን የገጠማ ስራ (ኢንስታሌሽን) እና ተጨማሪ ስራዎችን ያከናወነው መቀመጫውን በእስራኤል ያደረገውና በኢትዮጵያም ቢሮ የከፈተው “ኤልስሜድ ኸልዝ ኬር” የተሰኘ የህክምና መሳሪያ አስመጪና የገጠማ ስራ ድርጅት ሲሆን ድርጅቱ በጨረታ ውስጥ ያልተካተቱ ተጨማሪ የገጠማ ስራና ግብአቶችን አሟልቶ የማሽኑን ክፍል በመስራት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከካንሰር ህክምና ክፍሉ ሃላፊዎች ከፍተኛ ምስጋና ተችሮታል።
ማሽኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣውን የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር ወረፋ መጠበቅ መቶ በመቶ ያድነዋል ባይባልም ቅሉ የተሻለ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የካንሰር ህክምና ማዕከሉ ሃላፊ ገልጸው፤ መንግስት ተጨማሪ ማሽኖችን  እንዲያስገባ ጠይቀዋል።
 ቀደም ሲል በማዕከሉ 20 እና 30 ሰዎች ይታዩ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን አሁን በቀን እስከ 150 ሰዎች እየታከሙ እንደሆነ የጠቆሙት የማዕከሉ ሃላፊ፤ ይህም የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እያሻቀበ ለመምጣቱ ማረጋገጫ ነው ብለዋል። የዓለም የጤና ድርጅት ለ1 ሚሊዮን ሕዝብ አንድ የካንሰር ህክምና ማሽን የሚል ህግ ቢያወጣም፤ እኛ አገር ግን ከ104 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚጠቀመው ከዚህ በፊት በነበሩት “ከባል 60”የተሰኙ ማሽኖች እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት ማሽኖቹ ተበላሽተው ከአገልግሎት ውጭ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ካንሰርን ለማከም ከሚውሉ ከ70 በላይ መድኃኒቶች ውስጥ በአንድ ጊዜ የሚገኙት ከ30 እንደማይበልጡ፣ የህክምና መሳሪያዎችን በማስመጣት ሂደት ላይም በጉምሩክ በኩል በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉና በአፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሻ ተነግሯል፡፡

Read 3456 times