Tuesday, 08 December 2020 13:55

ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው)

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  በብዕር ስሙ “ገሞራው” በመባል የሚታወቀው ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ ፣ ሐምሌ 1935 ዓ.ም በደብረ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ፣ አዲስ አበባ ተወለደ። አባቱ መሪ ጌታ ገብረ ዮሐንስ ተሰማ፣ እናቱ ወ/ሮ አመለወርቅ ሀብተወልድ ይባላሉ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። ከዚያም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ የቋንቋ ጥናትና የስነ ልሳን ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቀ። ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ በመጀመሪያ ተግባረዕድ ትምህርት ቤት፣ ቀጥሎም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት (ኮተቤ) በመምህርነት አገልግሏል።
በ1968 ዓ.ም ባገኘው የነፃ ትምህርት ዕድል ወደ ቻይና ሄዶ በቋንቋና በፊሎዞፊ መስክ ሁለተኛ ዲግሪውን የተቀበለ ሲሆን፤ ወደዚያ የተጓዘበትን ትምህርት ከአጠናቀቀ በኋላ በቻይና ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ላይ ምርምር አደረገ። የቻይና ስነ-ጽሑፍ ነፃነት የሌለው ሆኖ ስለታየው በመንግሥቱና በሥርዓቱ ላይ የፅሑፍ ትችትና ነቀፋ ሰነዘረ። በዚህ ምክንያት ከቻይና ወደ ስዊድን ሄደ። ከዚህ በኋላ ስደተኛ ሆኖ ቀረ።
ኃይሉ፣ እ.ኤ.አ ከ1980 እስከ 2010 በኖርዌይና ስዊድን ሀገሮች በስደት ሲኖር በትርፍ ጊዜው በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ከ30 በላይ ጽሑፎችን አስር መጻሕፍትን ለኅትመት አብቅቷል። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. በረከተ መርገም፡- የግጥም መጽሐፍ ነው። የጻፈውና በንባብ ያስደመጠው ቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት በ1959 ዓ.ም ሲሆን፣ ታትሞ ለንባብ የበቃው ግን በ1966 (ብርናንና ሰላም ማተሚያ ቤት)ነው። በድጋሚ እ.ኤ.አ. የካቲት 1980 ስዊድን አገር ታትሟል።
2. ፍንደቃ፡- በ1968 ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ዘጉባዔ ማሚያ ቤት ታተመ።
3. ዜሮ ፊት አውራሪ፡- እ.ኤ.አ. ጥር 1980፣
4. ዛር ነው በሽታዋ:- እ.ኤ.አ. መጋቢት 1981፣
5. በናቴኮ ሴት ነኝ፡- እ.ኤ.አ. የካቲት 1982፣
6. ወይዘሪት ወይዘሮ፡- እ.ኤ.አ ግንቦት 1983.
7. እናትክን በሉልኝ፡- እ.ኤ.አ  ሕዳር 1984.
8. ቆርጠሃት ጣልልኝ፡- እ.ኤ.አ ሰኔ 1985፣
9. የመንጎሌ ጥሪ፡- እ.ኤ.አ. ጥቅምት 1985፣
10. የሽግግር ደባ፡- እ.ኤ.አ. የካቲት 1986፣
(ከተራ ቁጥር 2-10 የተጠቀሱት መጻሕፍት የታተሙት፣ በNina Printing press, Kungsangsvagen  25፣ S-753 23 Uppsala Sweden ማተሚያ ቤት ነው።)
ኃይሉ (ገሞራው)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታው፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ በብዕሩ በማጋጋል የታወቀ ነበር። በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ የእስር ቤት ሰለባ ከመሆኑም በላይ ከዩኒቨርሲቲው እስከ መባረር ደርሶ ነበር። በሕዝቡ፣ በተለይም በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አድናቆት፣ እውቅናና ሽልማት ያገኘበት “በረከተ መርገም” የተባለው ግጥም ነው። በ1960ዎቹ ውስጥ የነበሩት የመንግስት ፀጥታ ሠራተኞችና ፖሊሶች “ባለ መርዛሙ ብዕር” ብለው ይጠሩት እንደነበር ይታወቃል። ከ“መርዛሙ ብዕር” የቀለም ጠብታ ለአብነት እነሆ፡-
“በመንቃት ላይ ባሉ ፍጡራን መካከል፤
ሕይወት የምንለው እንደ ጥሬ እህል፤
በኑሮ ምጣድ ላይ ቢቆላ ቢማሰል፣
የበሰለው ያራል ጥሬው እስኪበስል።
በሰበብ አስባቡ ራስን ለመጥቀም፤
ንብረት ለማደርጀት እያጋነኑ ስም፤
በህግ አመካኝቶ እየተወጡ ቂም፤
ደግሞም ለመፈንጠዝ በማዕዘን ዓለም፤
ጭቆና ባርነት፣ አድልዖና አመጽ፣ እንዲስፋፋ በጣም።
እንዲሆን ከሆነ አስበው መርምረው፣ ስልጣንን የሰሩት፣
ደግሞም አስተዳደር፣ ሕግም ሆነ መንግሥት፤
እነዚያ ጀጁዎች የዋሆቹ ፍጥረት፣
ፕሌቶ አርስቶትል ሁላቸው ሊቃውንት፣
ይህን ግብዝ ሐሳብ፣ ከግብ ሳያደርሱት
በሥራ ላይ ሳይውል ገና ሲወጥኑት፣
ይሻላቸው ነበር፣ አፎቿን ከፋፍታ ብትውጣቸው መሬት”
ኃይሉ፣ ከሚወዳት ሀገሩ ርቆ፣ ብሶቱን ሲሰማለት ከነበረው ወገኑ ተለይቶ፣ ለ35 ዓመታት በቻይና፣ በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት፣ በኖርዌይና በስዊድን እየተዘዋወረ ሲኖር፣ በርከት ያሉ ጽሑፎችን በግእዝ፣ በአማርኛ፣ በኖርዊጂያንና በስዊድንኛ ቋንቋዎች አበርክቷል።
ይህ ታዋቂ ገጣሚ በሀገራችን የተፈራረቁ የመንግስት ስርዓቶችን አንዱንም ደግፎ አያውቅም። ይልቁንም ባለበት ሀገር ሆኖ በተባ ብዕሩ ሲሄሳቸውና ሲነቅፋቸው ኖሯል።
ኃይሉ (ገሞራው) ባደረበት ፅኑ ሕመም ምክንያት በተወለደ 72 ዓመቱ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። በኑዛዜው መሰረት አስክሬኑ ከኖረበት ስዊድን፣ ወደሚወዳት ሀገሩ መጥቶ፣ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ዐረፈ።
(በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከታተመው “ማህደረ ደራስያን" አዲስ መፅሐፍ የተወሰደ)



Read 3910 times