Saturday, 12 December 2020 00:00

መቀሌ በሰላማዊ እንቅስቃሴ ጅማሮ ላይ ናት ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  - የመጀመሪያው 12 ሺህ ኩንታል የእርዳታ ስንዴ ደርሷል
            - የተቋረጠው መብራት ትናንትና አገልግሎት ይጀምራል ተብሎ ነበር
            - “ከጊዜያዊ የክልሉ አስተዳደር ጋር የማረጋጋት ስራ እየሰራን ነው” (ትዴፓ)
                  
             መቀሌ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኑን የፈንቅል እና የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሃላፊዎች ገለጹ።  ለትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበ ሲሆን ከ16 ሚሊየን ብር በላይ የወጣበት የእርዳታ ስንዴና መድኃኒት ወደ ትግራይ እየተጓጓዘ ሲሆን ከነገ ጀምሮ መከፋፈል ይጀምራል ተብሏል። የመጀመሪያው ዙር 12 ሺህ ኩንታል የእርዳታ ስንዴ መቀሌ መግባቱም ተገልጿል።
መንግስት ከጥቅምት 24 ምሽት ጀምሮ የህወሃትን አጥፊ ቡድን ለህግ ለማቅረብ የጀመረውን እርምጃ ተከትሎ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የዘለቀችው መቀሌ  በአሁኑ ሰዓት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰች ነው ተብሏል። ህዝቡ ወደ ውጪ መውጣት ጀምሯል፤  ካፌዎች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ሲሉ የፈንቅል ንቅናቄ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስሃቅ ወልዳይ በመቀሌ የሚገኝ አባላቸውን ጠቅሰው ነግረውናል።  አቶ ይሰሃቅ አክለውም  በቀጣይም ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ፣ የስልክና የባንክ አገልግሎት ይጀመራል መባሉን ተከትሎ ህዝቡ በደስታና በተስፋ መሞላቱን ገልጸዋል። ህዝቡ ከመከላከያ ሰራዊቱና ከጊዜያዊ የክልሉ አስተዳደር ጋር በመሆን የህወሃት የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን፣ የህወሃትን አላማ ለማሳካት ሲላላኩ የነበሩ ባንዳዎችንና ሌሎች የጥፋት ሴራዎችን እያጋለጠ እንደሚገኝ  ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
ፈንቅል በቀጣይ በጦርነቱ ምክንያት ለችግር የተጋለጡትንና አስቸኳይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የክልሉን ነዋሪዎች ለመደገፍ የእርዳታ ድርጅቶችን አጋር በማድረግ እንደሚሰራ እና ከተማዋን የማረጋጋት ስራ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
የትዴፓ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “ህወሃት አጥፍቶ ለመጥፋት የተነሳ የጥፋትና የጭካኔ ቡድን ነው ያሉ ሲሆን ጁንታው ቡድን ሁሉንም መሰረተ ልማቶች በማፈራረስና በማውደም የትግራይ ህዝብ በጨለማና በችግር እንዲኖር አድርጎት ቆይቷል ብለዋል። ህውሃት ህዝቡን ለ27 ዓመት ያፈነውና የተጨቆነው ሳያንስ አሁን በቅርቡም “ልትወረር ነው ልትወጋ ነው፤ ልታልቅ ነው” የሚል የባሰ ስጋትና ጭንቀት ውስጥ አስገብቶት የቆየ በመሆኑ አሁን በመከላከያ ሰራዊት መረጋጋት እያገኘ መሆኑን መቀሌ የሚገኙ አባሎቻችን ገልፀውልናል ብለዋል።  እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ መብራት በመጥፋቱ ወፍጮ የሚባል ነገር አልነበረም፣ አሁንም መብራት፣ የባንክ አገልግሎት ስራ አልጀመረም፣ መድሃኒትም የለም። ሕዝቡ እነዚህን አገልግሎቶች ሳያገኝ በመቆየቱ በችግር ውስጥ በመሆኑ መንግስት እነዚህን መሰረተ ልማቶች በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ስራ እንዳስጀመረ ሁሉ በመቀሌም በፍጥነት ያስጀምራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
ሰሞኑን መቀሌ የደረሰውን የእርዳታ ስንዴም በተመለከተ የተሰራውን ስራ አድንቀው በሴፍትኔት ለሚኖረው አብዛኛው የትግራይ ህዝብም ሆነ ተሯሩጦና ያገኘውን ሰርቶ የእለት ጉርሱን ለሚያገኘው ሁሉ ከፍተኛ ችግር ሆኖ በመቆየቱ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፤ ፓርቲያቸው ከጊዜያዊው የክልሉ አስተዳደር ጋር በመተባበር የማረጋጋትና እርዳታ የሚያገኝበትን መንገድ በመፈለግ በኩል ከፍተኛ ስራ ይሰራል ብለዋል።

Read 8029 times