Saturday, 12 December 2020 00:00

ከ38 ቢሊዮን በላይ የሳይበር ጥቃት በ14 ቀናት…..

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

“የአሁኑን ጥቃት ከወትሮው የሚለየው እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሙከራዎች ከአንድ አካባቢ የተደረጉ መሆናቸው ነው”
                        
              የመንግሰት መ/ቤቶች፣ የብሮድካስት ሚዲያዎች፣ የፋይናንስ ተቋማትና ኢትዮ ቴሌኮም   በ14 ቀናት ውስጥ በህዝብና በሀገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ከ39.8 ቢሊዮን በላይ የሳይበር ጥቃቶች ሙከራ እንደተደረገባቸው ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም ሁሉም ሙከራዎች ግን የታለመላቸውን ግብ ሳይመቱ መክሸፋቸውን አመልክቷል፡፡
ሙከራዎቹ ያነጣጠሩት በመንግሰት ትላልቅ ተቋማት፣ በብሮድካስት ሚዲያዎች በፋይናንስ ተቋማትና በቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ መሆኑን የጠቆሙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ፤ በእነዚህ ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ የመረጃ መረብ ጥቃት ሙከራ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 6 ሰዓት ከ37 ደቂቃ ላይ በትግራይ ክልል የቴሌኮም አገልግሎት መቋረጡን የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬህይወት፤ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ በመቀሌና ሽሬ የሚገኙት ዋና ጣቢያዎች ያላቸው አማራጭ የመገናኛ መስመሮች በሙሉ በመቋረጣቸውና ከዋናው የኃይል ማመንጫ የነበረው የኃይል አቅርቦት  እንዲቋረጥ በመደረጉ ነው ብለዋል።
በትግራይ ውስጥ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በተፈፀመበት ዕለት ከድርጅቱ ሰራተኞች ውጪ የሆኑ አካላት በሰሜን ሪጅን ውስጥ ወደሚገኙት ጣቢያዎች በመግባት፣ አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን የገለፁት ስራ አስፈፃሚዋ፤ ይህንንም ከደህንነት ካሜራዎች ባገኘው መረጃ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
በቴሌኮም ላይ የሚፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶች የተለመዱ መሆናቸውን የገለፁ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ  ባለሙያ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ እንዲህ  የሳይበር ጥቃቶች ብዙውን ጊዜ የተለመዱ መሆናቸውንና  የአሁኑን ለየት  የሚያደርገው በቁጥር ከተለመደው በእጅጉ መላቁ፣ አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የተሞከሩት ከአንድ አካባቢ መሆኑና የተደረጉት ሙከራዎች ከከዚህ ቀደሞቹ ጠንከር ያሉ መሆናቸው እንዲሁም አንዳንዶቹም ስለ መሳሪያዎቹ በሚያውቁ ባለሙያዎች መፈፀማቸው ነው፡፡ ጥቃቶች በተራ ግለሰብ ከሚደረጉ  ሙከራዎች  እስከ ተደራጁና ከአገር ውስጥ በውጪ አገር ባሉ ትላልቅ ተቋማት የሚፈፀሙ መሆኑንና ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል በአገርና በህዝብ  ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ እግጅ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጥቃቶች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉበት ጥቃቶች በቁጥር አነስተኛ ናቸው ቢባልም የሚያደርሱት ጉዳት ግን በአገር ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም እኚሁ ባለሙያ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ፤ ከደህንነት ካሜራው የተገኙትን ምስሎች ይፋ ያደረገ ሲሆን መረጃዎቹን ጉዳዩን  እየመረመረ ላለው  የፌደራል ፖሊስ ምርመራ ክፍል ምርመራው እንደተጠናቀቀም ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥበት አስታውቀዋል፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም ዕውቅና ውጪ በመቀሌ አካባቢ በህገወጥ መንገድ ወደ ቴሌ ሲስተሙም ለመግባት ሙከራ መደረጉ ተደርሶበታል ያሉት  ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ከፍተኛ መጠነን ያላቸው የመረጃ መረብ ጥቃቶች ለማድረስ ሙከራ መደረጉንም ገልፀዋል፡፡  


Read 8366 times