Saturday, 12 December 2020 00:00

ፎርብስ የአመቱን የአለማችን ሃያላን ሴቶች ይፋ አድርጓል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  አንጌላ መርኬል ለ10ኛ ጊዜ 1ኛ ደረጃን ይዘዋል


            በተለያዩ የሙያ መስኮች ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉና ተሰሚነት ያተረፉ የአለማችን ሴቶችን በየአመቱ እየመረጠ ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሔት ከሰሞኑ የ2020 የአለማችን 100 ሃያላን ሴቶችን ዝርዝር ያወጣ ሲሆን፣ ላለፉት 9 አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበሩት የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል ዘንድሮም ክብራቸውን የሚነጥቃቸው አላገኙም፡፡
የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ፋላፊ ክርስቲያን ላጋርድ እንዳምናው ሁሉ ዘንድሮም የሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፤ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት፣ ጥቁር አሜሪካዊትና እስያ አሜሪካዊት ምክትል ፕሬዚዳንት ሊሆኑ የሳምንታት ጊዜ ብቻ የቀራቸው ካማላ ሃሪስ፤ የአመቱ ሶስተኛዋ የአለማችን ሃያል ሴት ተብለዋል፡፡
ኡርሱላ ቫን ደር ላይን አራተኛዋ፣ የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ተባባሪ ሊቀ መንበር ሚሊንዳ ጌትስ አምስተኛዋ፣ ሜሪካ ባራ ስድስተኛዋ፣ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ሰባተኛዋ፣ አና ፓትሪሺያ ቦቲን ስምንተኛዋ፣ አቤጊየል ጆንሰን ዘጠነኛዋ፣ ጌል ቦድሬክስ አስረኛዋ የአመቱ የአለማችን ሃያል ሴት ተብለው በፎርብስ መጽሔት ተመርጠዋል፡፡
ፎርብስ ለ17 ጊዜ ያወጣው የአለማችን 100 ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የ30 አገራት ሴቶች የተካተቱ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አስሩ የአገራት መሪዎች፣ ሰላሳ ስምንቱ የኩባንያ ስራ አስፈጻሚዎችና አመራሮች፣ አምስቱ ደግሞ በመዝናኛው መስክ የተሰማሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 1018 times