Monday, 14 December 2020 18:03

አስረስ የኔሰው፤ በኢትዮጵያ የምሁራን ታሪክ ውስጥ

Written by  ፊደል ችሎ
Rate this item
(0 votes)

   “የኢትዮጵያ ልጆች ሆይ፤ ያውሮፓ ሰዎች እስከዚህ የደረሱበትን አስቡ መርምሩ፡፡ የሀገራችሁን ቋንቋ ግዕዝን ተከተሉ የሳይንስን ነገር የሚመራ ለማግኘት ትችላላችሁ”
                    
              ምሁራን፤ በአንድ ሀገር ውስጥ ፖለቲካውን መልክ በመስጠት፣ የሚበጀውን በማመላከት፣ ትውልድና  ሀገርን በማሻገር ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡  የታሪክ፣ የባህልና የኢኮኖሚ መዛነፎች መስመር እንዲይዙ  በማድረግም አስፈላጊነታቸው ወሰን የለውም፡፡ የማህበረሰቡን ችግር ለመለየትና የሚሆነውን መፍትሔ ለማፍለቅም እጅግ ያስፈልጋሉ፡፡
ኢትዮጵያ ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ፣ ከሳይንስ በረከቶች ለመቋደስ በአጠቃላይ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ እንደ መፍትሔ የወሰደችው የምዕራቡን የትምህርት ሥርአት መቀበል ነው፡፡ እናም፤  የኢትዮጵያ የስልጣኔና ማህበረሰብ ታሪክ፣ የፖለቲካና ባህል መስተጋብር እንደ ምዕራቡ አተያይ የሚጠየቅበት መንገድ ብቅ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ፤ ኢትዮጵያ እውነቴ የምትላቸው የማህበረሰብ ይትበሃሎች እንደ ኋላ ቀርነት መቆጠር ጀመሩ፡፡  የኔታ ዘንድ ፊደል መቀፀል፣ የበልሀ ልበልሃ ስርአትና መሰል ሀገር በቀል የኑሮ ስልቶች ባህላዊነት በሚል ተሳበው ወደ ጎን ተጣሉ፡፡ በተጨማሪም ለሚስተዋሉት ተጨባጭ የማህበረሰብ ችግሮች ድህነትና ኋላ ቀርነት፣ መፍትሔያቸው ምእራቡ የደረሰበትን መልመድ እንደሆነ ታመነ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ምሁራን፤ ጃፓንን ወይም የምዕራቡን ዓለም እንደ ምሳሌ አድርገው  ስለ ሀገሪቱ መለወጥ፣ ስለ ዘመናዊ ተቋም ግንባታ እንዲሁም ስለ ባህል ተራማጅነት ብዙ አሉ፡፡  በየዘመኑ ተራማጅ የተባሉት ግለሰቦች ኢትዮጵያን ለማሻሻል አይነተኛ አማራጩ የምዕራቡ የሳይንስ ፍልስፍና እንደሆነ ሞገቱ፡፡  
ከዚህ በተቃራኒ፤ ሊቃውንት በስራቸው፤ የጥንቱን የአክሱምንና ላሊበላ አሻራ መከታ በማድረግ፣ የኢትዮጵያን የማህበረሰብ ታሪክ  የሚተነትኑ አሉ፡፡ ድርሳናትን  የገለጥን እንደሆነ የቤተ-ክህነት ሰዎች፣ የታሪክ ፀሀፍት፣ ፈላስፎች  ትናንት ኢትዮጵያዊያን ያለፉትን በጎ ታሪክ በተመለከተ ብዙ ብለዋል፡፡ ለአብነትም ከየኔታ አስረስ የኔሰው እስከ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ ከዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ እስከ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም፣ ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ  እስከ ዶክተር መአምሬ ድረስ --- ኢትዮጵያኖች በታሪካቸው የስልጣኔ፣ የመሻሻልና የጥንካሬ ዘመን እንደነበራቸው ያወሳሉ፡፡ በተጨማሪም ዛሬ ለሚስተዋሉት ችግሮች መፍትሔያቸው ወደ ኋላ መመለስ እንደሆነ  ይመክራሉ፡፡ የኢትዮጵያዊያንን የልብ ትርታ የሚያውቅ ለውጥ ለማምጣትም ሆነ የተሻለ ማህበረሰባዊ ሥርአት ለመገንባት ወደ ታሪክ መመመለስ እንደሚገባ አበክረው ያስረዳሉ፡፡   
እንደ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ አተያይ፤ “አንድ አገር ሊበለጽግ የሚችለው የራሱ ታሪክ ባለቤት ሲሆን ነው። የራሱ ታሪክ ባለቤት ለመሆን የሚችለው ደግሞ በጊዜ ውስጥ እራሱን በማየት ለመኖሩ ሉዓላዊ የሆነ ትርጓሜ ሲሰጥ ነው” (2013፣ገጽ፣9)፡፡ በዚህ አመክንዮ መሰረት፤ ታሪክ ለመሻሻል፣ ስልጣኔን እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ታሪክ፤ ትናንት ምን እንጎደለ የምንጠይቅበት እንዲሁም ለዛሬ እውቀትና ክህሎት የምንበደርበት ክስተት እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡
አስረስ የኔሰው ኢትዮጵያን ኋላ ቀር አድርገው ለሚረዷት፣ የራሷ ስልጣኔ የላትም ለሚሉቱ---- ሀገሬ እውነት አላት ሲሉ ከሞገቱት ልሂቃን አንዱ ናቸው፡፡ በአንድ ዘመን፤ በተለይ አንዳንድ የምዕራቡን ታሪክ ያጠኑ ኢትዮጵያዊያንና የምዕራቡ ምሁራን፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያቀርቡት ጥናት እጅግ የተሳሳተ እንደሆነ በስራቸው ያወሳሉ። አስረስ የኔሰው በፃፏቸው መፅሐፋት፣ ስለ ኢትዮጵያ የስልጣኔ ከፍታ፣ የቋንቋ ታሪክ እንዲሁም ስለ ነበራት ሃያልነት ብዙ ብለዋል። ስራዎቻቸው ታሪክ እንደገና መመርመር እንዳለበት የሚያመለክቱ ናቸው፡፡  ዛሬ ሰለጠኑ የምንላቸው የአውሮፓ ሀገራት የፊደልና ኪነ-ህንፃ ታሪክ ላይ ሳይደርሱ በፊት  ኢትዮጵያኖች ቀድመው ከፍተኛ ስልጣኔ እንዳሳዩ ይናገራሉ፡፡
አስረስ “ትቤ መኑ አክሱም መኑ አንተ?”፣ “የካም መታሰቢያ” እና ጠቃሚ ምክር በተሰኙ ጥራዞቻቸው፤ የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔ የሚተርኩ እንዲሁም  የታሪክ መረዳታችን በእጅጉ የሚያሰፉ እሳቤዎች ማቅረብ ችለዋል፡፡ እንደ አስረስ አተያይ፤ መለወጥ ወይም መሻሻል ባህልን መተው አይደለም፤ እራስን ማደስ ታሪክን ወይም አባቶች የሰሩትን ሥርአት ማፍረስ አይደለም፡፡ ይልቅስ፤ እራስን ለማሻሻል ወደ ታሪክ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም  ለተጣራ የታሪክ መረዳት ስለሚጠቅም አለፍ ሲልም መንፈሳዊ ብርታት ስለሚሆን፡፡
አስረስ፤ በዚህኛው ዘመን ጭምር እውነት የምንላቸውን የፖለቲካ መረዳት፣ የስልጣኔ ትርጉም፣ የባህል አተያይና የታሪክ አተረጓጎም መለስ ብለን እንድንጠይቅ የሚረዳ እሳቤ ማቅረብ ችለዋል፡፡ አንዳንድ የምዕራብ ምሁራን፤ የኢትዮጵያ የስልጣኔ ታሪክ ከአረብ የመጣ እንደሆነ ይተርካሉ፡፡  እንደ አስረስ የታሪክ መረዳት ግን ኢትዮጵያ የስልጣኔ ባለቤት ናት፡፡ እንደ አክሱም የመሳሰሉ ቅርሶች ኢትዮጵያኖች የስልጣኔ እድገት ያሳዩባቸው እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም፤ በመፅሐፎቻቸው ስለ ግዕዝ ምስጢርነትና አስፈላጊነቱ ይተርካሉ፡፡ እንደ ምክርም እንዲህ ይሉናል፡- “የኢትዮጵያ ልጆች ሆይ፤ ያውሮፓ ሰዎች እስከዚህ የደረሱበትን አስቡ መርምሩ፡፡ የሀገራችሁን ቋንቋ ግዕዝን ተከተሉ የሳይንስን ነገር የሚመራ ለማግኘት ትችላላችሁ” (ጠቃሚ ምክር፣ገጽ፣43)፡፡
እንደ አስረስ አተይይ፤ በኢትዮጵያ የተማሩ ሰዎች በተለይ የምዕራቡን ትምህርት የተማሩ ስለ ምዕራቡ ታሪክ፣ ፍልስፍና እና ስልጣኔ ብዙ ያውቃሉ፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ ግን ውስንነት አለባቸው ይላሉ። የኢትዮጵያን የማህበረሰብ ታሪክ እንደ ምዕራቦች አተይይ ለመተንተን እንደሚሞክሩ መታዘባቸውን ይተርካሉ፡፡ ስልጣኔ የታሪክ እርሾን ይፈልጋል፡፡ አክሱምን የሚያውቅ፣ የቅኔ ምስጢራችን የሚፈታ፣ የኑሮ ዘዴያችን የሚገባው እንዲሁም ለችግራችን መፍትሔ የሚሆን ስልጣኔ እውን ለማድረግ ትናንት ሰበአ ትካት የሰሩትን ማጤን እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
አስረስ እንደ አንድ የተማረ ሰው ታሪክን እንደገና ለማጥናት ተነስተዋል፤ ኢትዮጵያ የስልጣኔ ታሪክ አላት ሲሉ ሞግተዋል። ትውልዱ የጠራ የታሪክ መረዳት እንዲኖረው በእጅጉ ለፍተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኪነ-ህንፃና መሰል ስልጣኔዎች ኢትዮጵያኖች  እውቀታቸውን ያዋጣቡት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡  
ጠቅለል ስናደርገው፤ አስረስ ስለ ታሪክ፣ ስለ ሀገራችን፣ ስለ ስልጣኔ በአጠቃላይ ትናንት አባቶቻችን ስለ ሰሩት የጋራ ስኬት እንዲሁም ነገ ኢትዮጵያዊ የሆነ ስልጣኔ እውን የሚሆንበትን መንገድ ለማሳየት ጥረዋል፡፡ አንዳንድ እውነት ብለን የተቀበልናቸውን የታሪክ አንደምታዎችና የስነ-ቃል ጥናቶች የበዛ ስህተት እንዳለባቸው ለማሳየት ጥረዋል፡፡ አስረስ፤ መማርን ታሪክን በወጉ ከማጥናት ጋር ያያይዙታል፡፡ የመማር ጥቅሙም አንድ አገር ያለፈችውን የታሪክ ሁነቶች ከመመርመር ይጀምራል ይላሉ፤ ያላትን ሀብት ለማወቅ፣ የጎደላትን ለማጥናት እንዲሁም የሚበጃትን ሥርአት ለማቆም መማር በእጅጉ እንደሚጠቅም ያስረዳሉ፡፡  

Read 10661 times