Monday, 14 December 2020 19:21

ግማሽ ግማሽ

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(4 votes)

  ሙሽሮቹን ብዙ ባላውቃቸውም ያለ ወትሮዬ በሰርጉ ለመገኘት ወስንኩ። የሰርግ ካርዱ ለየት ያለ ነው። በማሳሰቢያና በማስጠንቀቂያ የታጀበ። አንድ ልብ አንጠልጣይ መልእክትም አለው። “አያምልጥዎ፤ ሕይወትዎን ሊለውጥልዎ የሚችል ሰርግ ነው!!” የሚል ጽሁፍ ከግርጌ ሰፍሯል።
የጥሪ ሰዓቱ ደሞ ከምሽቱ 4፡30 እስከ ንጋት ይላል። ያልተለመደ ነው። ሙሽሮቹ ሌሊት ለምን መረጡ? ይኼን እያሰላሰልኩ ዓይኔ ሌላው የካርዱ ጽሁፍ ላይ አረፈ። የአለባበስ ዓይነት ይገልፃል። “የአዘቦት ልብስ ብቻ ይፈቀዳል!” ይላል። “ትዳር ያላቸው በፓርቲው መሳተፍ አይፈቀድላቸውም!” የሚለው ማስጠንቀቂያ ግን ከሁሉም የበለጠ ግራሞት ፈጠረብኝ።
እንኳንስ ትዳር ጊዜያዊ ፍቅረኛም የለኝ። ወዲያው ደሞ ያልታወቀ የደስታ ስሜት በደም ስሬ ሲሯሯጥ ተሰማኝ። መቼም ወንደላጤ ብቻ አይጠራም፤ ሴተላጤም ትኖራለች። ይሄ የራሴ ምኞት ነው። እንደ ምኞቴ ከሆነ ታዲያ ጠበሳ በሽበሽ! ነው ማለት ነው። ቀንቶኝ ፍቅረኛ ቢገጥመኝ.. ስል አሰብኩ።
ሰርግ ቤቱ በር ላይ ግርግሩ ለጉድ ነው። ፈጽሞ የሰርግ ቤት ድባብ የለውም። ከሰርግ ይልቅ ለዳንስ የተዘጋጀ ይመስላል።፡ ሁለመናው። ብዙዎቹ ተጠሪዎች ወጣቶች ቢሆኑም ጠና ጠና ያሉም አልጠፉም፡፡ ካርዴን አሳይቼ ልገባ ስል አስተናባሪው፤ “ጋሼ፣ ሎተሪ አይገዙም? አሸናፊ ሊሆኑ ይችላሉ።; አለኝ የተጠና በሚመስል ቅላፄ። “ሠርግ ቤት ሎተሪ?”” አልኩኝ ነገሩ አስገርሞኝ፡፡ “ለእንግዶቻቸው ሲሉ ያደረጉት ነው?”  አለኝ አስተናባሪው።
“ሽልማቱ ምንድን ነውዋጋውስ?” ሁለት ጥያቄዎች አከታትዬ ጠየኩት።
“ጌታዬ! ሽልማቱን እንኳ አላውቅም፤ የሎተሪው ዋጋ ግን 50 ብር ነው"
“እንዴ! የሰርጉን ወጪ በእኔ ብር ሊሸፍኑ?” አልኩኝ፤ በሳቅና ቁጣ መሃል ሆኜ።
“አረ አይደለም ጌታዬ" አለ አስተናባሪው እየተሸኮረመመ።
የ100 ብር ኖት ከገንዘብ ቦርሳዬ አወጣሁና ሰጠሁት።
“ሁለት ትኬት ላድርገው?” አለኝ አስተናባሪው፡፡
"ቀልደኛ!” አልኩት አፍጥጬበት።
ይኼኔ የሎተሪ ትኬቱንና የ50 ብር ኖት ሰጠኝ፡፡
“አብሽር! ከደረሰኝ ግማሽ ግማሽ እንካፈላለን”  አልኩት አፌ አንዳመጣልኝ።
ወይ የሰርግ ሎተሪ? ብቻ ብሄራዊ ሎተሪ እንዳይሰማችሁ! እያልኩ መቀመጫ በዐይኔ ማማተር  ጀመርኩ። በተንጣለለው ሰፊ ግቢ የተደኮነው ዘመናዊ  ድንኳን ጢም ብሏል። የእንግሊዘኛ  ሙዚቃ ይደለቃል።  ከርቀት  የፈገግታ ብርሃን የምትረጭ ወጣት፣ ዓይኔን ያዘችውና ከእግሬ ጋር ተመሳጥረው እሷው ጋ ወሰዱኝ። የውበት አማልክት ተጨንቀው ተጠበው እንደሰሯት ማንም ሊጠራጠር አይችልም፤ ውበት ፈሶባታል። ከእሷው ትይዩ ተቀመጥኩና አጠገቤ የተቀመጠውን ዋይት ሆርስ ቀድቼ ተጎነጨሁ። ዓይን ዓይንዋን ስመለከት እቆይና እሷ ወደኔ ስትዞር ዓይኔን እሰብራለሁ። እቆይና ደሞ  በከፊል የሚታዩት ፈርጠም ያሉ ጡቶቿ ላይ አፈጣለሁ። አንዴ ከዓይኖቿ ጋር፣ ሌላ ጊዜ ቀይ ቀለም በጥንቃቄ ከተቀባው ስስ ከንፈሯ ጋር እየተፋጠጥኩኝ ሳለሁ፣ ዓይኖቼ  አንድ መልካም ወጣት ላይ አረፉ። ደጋግማ ስትቃኘው መናደድ ጀመርኩኝ። ሰው እያውካካ መጠጡን ይጨልጣል። ዳንስና ጭፈራው ሲጀመር ለአፍታ ሌሎች ወጣቶች ማየት ጀመርኩ። ዞር ስል አጅሬ ከልጅቷ ጋር ወሬ ጀምሯል፡፡ በንዴት ጦፍኩኝ! ቅናት አበገነኝ። ይለይልህ ብለው ተያይዘው ተነሱ፤ ለዳንስ።
ይኼኔ እኔም ውስኪዬን መደጋገም ቀጠልኩ። በጉሮሮዬ ውስጥ ስለት የተላከ እስኪመስለኝ ድረስ ተጋትኩት። ልጅቷን የማጣት ያህል ግን አላሰቃየኝም።
እኔ ከብርጭቆዬ ጋር ተወዳጅቼ ሳለሁ፣ አንዲት ጥጥ የመሰለ ሽበት ጭንቅላታቸውን የሸፈነው አሮጊት ሲጋራቸውን እያቦለሉ፤ “ወጣት! ተነስ እንጂ ፓርቲ እኮ ነው!” አሉኝ፤ በቆሙበት እየተወዛዘዙ።
ዓይኔ ነው ወይስ ሰክሬአለሁ! “ስማ! ዳንስ ላስተምርህ ተነስ!” አሉኝ፤ አሮጊቷ ያለቀችውን የሲጋራ ቁራጭ መሬት ጥለው በእግራቸው እየረገጡ። ክንዴን ይዘው በግድ ወደ ዳንሱ ወለል ወሰዱኝ። ሁሉም ጥንድ ጥንድ ሆኗል። ዞር ስል ያቺ ውብ ወጣትና ጣውንቴ፣ በዳንስ እየተወዛወዙ በኔ ይስቃሉ። ንዴቴ ናረ! የሰው ዕድል መንጠቁ ሳያንሰው ማሾፉ ልቤን አሳረረው። የእጁን እንዲያገኝ በልቤ ተመኘሁ። ጠረጴዛው ላይ የተጎለተውን ውስኪ እስኪበቃኝ ተጋትኩት። ቅናቴን አጠብኩበት ብል ይሻላል።
“ስማ! ስማ!” አንድ ወፍራም ድምጽ ከእንቅልፍ ዓለም ይሁን ከስካር ዓለም አባነነኝ። ሽበታሟ አሮጊት ናቸው። መቼ ነው ደሞ ከጎኔ የተቀመጡት?
“ስትገባ ሎተሪ አልገዛህም?” አሮጊቷ ተጣድፈው ነው የጠየቁኝ።
“ገዝቻለሁ!”
“እጣው እየወጣ እኮ ነው! እስቲ አምጣው እንየው!” እንደ ምንም ፈልጌ ከአንዱ ኪሴ ውስጥ አገኘሁት።
“እዚህ ፊት ለፊትህ የነበረችው ቆንጆ ስትፈነጥዝ ነበር!”
የአሮጊቷን እጅ ሳላውቅ እንቅ አድርጌ “ማን? ምን አግኝታ?” አልኳቸው በጉጉት።
“ሎተሪ! ሎተሪ! አንደኛው ዕጣ!; አሉ።
አሮጊቷ የሎተሪ ትኬቱን አንስተው ቁጥሩን በጥንቃቄ መመልከት ያዙ። ከመድረኩ የአሸናፊ ቁጥር ሲጠራ ይሰማኛል።
“ብራቮ! ብራቮ!” አሉና ከተቀመጡበት ተስፈንጥረው ተነሱ፤ አሮጊቷ። እላዬ ላይ ተጠምጥመው ደጋግመው ሳሙኝ።
“እየተጠራህ ነው … ብራቮ! ብራቮ!” አሉኝና ትኬቱን ሰጡኝ። በበርካታ ዓይኖች ታጅቤ ወደ መድረኩ አመራሁ። መድረኩ ላይ ቆንጆዋ ልጅ ተቀምጣለች። ከጎኗ ሌላ ባዶ ወንበር አለ። ዓይን ዓይኗን ሳይ፣የኤሌክትሪክ ገመድ ጠለፈኝና ተንደርድሬ ማይክራፎን የያዘው ሰው ጋ ደረስኩ።
"አይዞህ እንኳን ደስ አለህ!" አለኝና ከቆንጆዋ አጠገብ ካለው ባዶ መቀመጫ እንድቀመጥ በምልክት አሳየኝ።
“ክቡራን እንግዶቻችን፤ የሎተሪ አሸናፊዎቹ ታውቀዋል። ሙሽሮቹ ወደ መድረኩ ይመጡና ሽልማቱን ለአሸናፊዎች ይሰጡልናል።" አለ ማይክራፎኑን የያዘው ሰውዬ፡፡
የአዘቦት ልብስ የለበሱ አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጅ ተያይዘው ወደ መድረኩ ወጡ። ሙሽሮቹ ናቸው። ሙሽራው ማይክራፎኑን ተቀብሎ ንግግር ጀመረ…
“የዚህ ምሽት የሎተሪ አሸናፊዎች፤ በዓይነቱ ለየት ያለና ህይወታቸውን የሚለውጥ ሽልማት በማግኘታቸው እኛ ሙሽሮች ደስታችን ወደርየለሽ ነው።" አለና ዞር ብሎ ሁለታችንንም በፈገግታ አየት አደረገን።
“የሁለቱም ሽልማት ተመሳሳይ ነው። ምክንያቱም ሁለቱም የአንደኛው ዕጣ አሸናፊ ናቸው።" አለውና ሙሽራው የኔን ስም ጠራ። ይኸኔ በድንጋጤ ከተቀመጥኩበት ዘልዬ ተነሳሁ።
“አይፈረድብህም! ሽልማቱ ሌላም ያደርጋል!” ብሎ ቀልድ ቢጤ ሲሰነዝር ድንኳኑ በሳቅ ተሞላ።
“የሎተሪ እጣህ ውብ ሚስት አስገኝቶልሃል!" አለ።
ንግግሩ ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም። የማላውቀው ስሜት ወረረኝ። ተወናበድኩ።
ሰውየው አንድ ሌላ ስም ጠራ፤ የሴት። ከአጠገቤ የነበረችው ቆንጆ ወጣት ተነስታ ቆመች፡፡
“በሎተሪ የኑሮ አጋርሽን - ባልሽን አግኝተሻል!"  አላት፤ ሙሽራው ወደኔ  በሁለት እጆቹ እያመለከታት። በቆመችበት ለአፍታ አቀርቅራ ቀረች። ድንኳኑ ውስጥ ዝምታ ነገሰ። ወዲያው ግን ነገሮች መልካቸውን ለዋወጡ። ወጣቷ ሁለት እጆቿን ዘርግታ ወደኔ እየተንሳፈፈች በመምጣት “ሙሽራዬ” የሚለው ዘፈን ተከተለ። እኔም እጆቼን ዘርግቼ ተቀበልኳት።
ንጋት ላይ ዕጣ ፈንታዬን ፣ ሚስቴን ይዤ ወደ ቤት ለመሄድ ተነሳሁ። ከሰርጉ ቤት ስንወጣ በሩ ላይ “ጋሼ፣ ጋሼ” ሲል ጠራኝ አስተናባሪው። ዞር ስል እየተሸኮረመመ፤ “ግማሽ ግማሽ እንካፈላለን አላሉኝም!” አለኝ። እጢዬ ዱብ አለ። አይኔ ፈጥጦ በቆምኩበት ቀረሁ፡፡

Read 1977 times