Saturday, 12 December 2020 00:00

ለሚካኤል ቤተ ስላሴ ዝክረ መታሰቢያ ተካሄደ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ ለሰዓሊና ቀራፂ ሚካኤል ቤተስላሴ ዝክረ መታሰቢያ ተካሄደ፡፡ በፔፐር ማሽ papier mâché   በሚሠራቸው ቅርፆች በመላው ዓለም የታወቀው ኢትዮጵያዊ ሰዓሊና ቀራፂ ከ30 ዓመቱ ጀምሮ  ቅርፃቅርፅ ላይ በመሥራት ቆይቷል፡፡  በ69 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት እስኪለይ በፓሪስ ከተማ ውስጥ ይኖር ነበር።
የኦዳ መደመር አፍሪካ የሥነጥበባት ስፍራ፤ የነፃ አርት ቪሌጅ፤ የናስ ስቱድዮ ሰዓሊያን ሌሎች እንግዶች በተሳተፉበት ዝክረ መታሰቢያ ሚካኤል ቤተ- ስላሴ በመንፈሱ ጥንካሬ ፤ በእውነተኛነቱ፤ በሰብዓዊነቱ፤ ለስነጥበብና ለስነጥበባውያን በነበረው ወገንተኝነት  ታውሷል፡፡ በዝክረ መታሰቢያው የተገኙ ታዋቂ ሰዓሊያን እንደተናገሩት ሚካኤል ቤተስላሴ ለኢትዮጵያ ስነጥበብ ያበረከተውን የማይተካ ሚና በማክበር  በአገር ውስጥ ያሉ የስዕል ስራዎቹ ተሰባስው ለእይታ መቅረብ እንዳለባቸውም ተገልጿል፡፡
ሚካኤልን  በማሰብ በኦዳ መደመር አፍሪካ የስነጥበባት ስፍራ በአፈር ሰዓሊው ዳዊት ሙሉነህ ግዙፍ የማስታወሻ ስዕል የተሰራ ሲሆን፤   በስነጥበባት ስፍራው በፔፐር ማሽ የሚሰራውን ስነጥበብ ለማጎልበት እና በይበልጥ ለማስተዋወቅ  አንድ ኮርነር ለመፍጠር ሰዓሊዎቹ ምክክር አድረገዋል፡፡ በዝክረ መታሰቢያው ላይ የኦዳ መደመር አፍሪካ የስነጥበባት ስፍራ መስራች ረዳት ፕሮፌሰርና ሰዓሊ ጎሳ ገብረስላሴ‹‹ሚካኤል ለእኛ የተመኘው ስኬታማ ሆነን በመላው ዓለም እንድንታወቅ ነው፡፡ ንፅህና ያለው እምነትን የምንገልፅበት፤ ከራሳችን ጋር የምንተዋወቅበት በመንፈስም በቁስ አካልም ከፍ ያለደረጃ እንድንደርስ ነበር የሚመክረው፡፡ በ24 ሰዓታት ውስጥ ለ48 ሰዓታት የሚያስብ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርኮችን እየከፈተ ነው፡፡ ይሄን መስራት ያለባችሁ ሰዓሊዎች ናቸው፡፡›› ብሎ መናገሩን ገልፀዋል፡፡
ሚካኤል ቤቴ-ስላሴ በግዙፍ  የፔፐር ማሽ ቅርፆቹ ፤ በደማቅ ቀለሞች የተጌጡ ክብ ወይም ረዣዥም ፊቶች፤ ሙሉ ልክ ያላቸው ቅርፃ ቅርጾች በትልልቅ ኤግዚቢሽኖቹ በማሳየት በዓለም ዙርያ አድናቂዎችን አፍርቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሰጣቸው አስተያየቶችም  በልዩ ስነጥበብ ለቀረፀው ባህል በኢትዮጵያ  ታሪክና አፈታሪኮች መነሳሳቱን ገልጿል፡፡
በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ላለፉት 40 ዓመታት ሲኖር የነበረው ሚካኤል ቤተስላሴ በስራ ዘመኑ በ18 የተለያዩ አገራት በመዘዋወር ከ80 በላይ ኤግዚብሽኖችን አሳይቷል፡፡በፈረንሳይ የተለያዩ ከተሞች ከ25 በላይ ኤግዚብሽኖች ያቀረበ ሲሆን በአምስተርዳም ፣ በአንቨርስ ፣ ባርሴሎና ፣ በርሊን ፣ ኮሎኝ ፣ ጄኔቫ ፣ ሎንዶን ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ፣ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሚገኙ ታዋቂ ሙዚየሞችም ውስጥ ሥራዎቹን አሳይቷል፡፡በበርካታ ታዋቂ መጽሔቶች የሽፋን ገፅ ላይ  በመሥራትም ይታወቃል። የሚካኤል ቤተ ስላሴ የቅርጫ ቅርፅ ስራዎች በመላው ዓለም በታዋቂ ሙዚዬሞች እና ጋለሪዎች የተሰበሰቡ ሲሆን በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የስሚዝሶኒያን ናሽናል ሙዚዬም ኦፍ አፍሪካን አርትም ስራዎች ለቋሚ እይታ ቀርበዋል፡፡ዲፕሎማት ፣ በመንግሥት ሚኒስትርነትና በሚስዮናዊነት ለሰሩት አጎቱ ለብርሃን-ማርቆስ ዋልዳ-ጻዴቅ (1892-1943) ሕይወትና ሥራ መታሰቢያ የሆነን መጽሐፍ በፈረንሳይኛ  በማዘጋጀት በ 2009 አሳትሟል፡፡


Read 28822 times