Tuesday, 15 December 2020 00:00

አሜሪካ በ2019 የጦር መሳሪያ ሽያጭ 1ኛ ደረጃን ይዛለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 አለማቀፍ የጦር መሳሪያ ሽያጭ የአሜሪካ ኩባንያዎች ቀዳሚነትን መያዛቸውንና አገሪቱ በአመቱ በመላው አለም ከተከናወነው የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ 61 በመቶ ያህሉን  መያዟን ስቶክሆልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢንስቲቲዩት የተባለ አለማቀፍ ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
ከአለማችን የአመቱ ባለከፍተኛ ገቢ 25 ታላላቅ የጦር መሳሪያ አምራችና ሻጭ ኩባንያዎች ያገኘውን መረጃ መሰረት አድርጎ ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ ኩባንያዎቹ በአመቱ በድምሩ ከጦር መሳሪያዎች ሽያጭ 361 ቢሊዮን ዶላር አግኝተዋል፡፡
ከ25ቱ ኩባንያዎች መካከል ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገቡት የአሜሪካዎቹ ኩባንያዎች ሎክሄድ ማርቲን፣ ቦይንግ፣ ኖርዝሮፕ ግሩማን፣ ሬቲዮንና ጄኔራል ዳናሚክስ ሲሆኑ፣ ኩባንያዎቹ በአመቱ 166 ቢሊዮን ዶላር ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ማግኘታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ በ2018 ከነበረበት የ8.5 በመቶ እድገት ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በአመቱ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ካስመዘገቡት 25 ኩባንያዎች መካከል የተካተቱት 4 የቻይና ኩባንያዎች በሽያጭ ሁለተኛ ደረጃን ወይም 16 በመቶ ድርሻን ይዘዋል፡፡
ከ25ቱ የአለማችን ታላላቅ የጦር መሳሪያ ኩባንያዎች ተርታ ለመሰለፍ የበቃው የመጀመሪያው የመካከለኛው ምስራቅ አገር ኩባንያ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትሱ ኢጅ ሲሆን፣ ከአመቱ ሽያጭ የ1.3 በመቶ ድርሻ በመያዝ በ22ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ከኩባንያዎቹ መካከል በአመቱ ከፍተኛ አመታዊ ሽያጭ ያስመዘገበው ኩባንያ የፈረንሳዩ ዳሶልት አቪየሽን ግሩፕ ሲሆን፣ ኩባንያው በ2018 ካስመዘገበው ሽያጭ የ105 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡ ተነግሯል።


Read 7205 times