Saturday, 19 December 2020 09:14

የሳሪስ 170 ነጋዴዎች ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን ገለጹ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 “አልጋዬን ሸጬ ነው ለመንግስት ግብር የከፈልኩት”
    
             በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6  ንግድ ባንክ  ጀርባ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ያሉ 170 ያህል ነጋዴዎች፣ ጩኸታችንን የሚሰማን አጣን ሲሉ አማረሩ። እነዚህ የሰላም ገበያ ባለ አክስዮኖች ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በህገ-ወጥ ነጋዴዎች ምክንያት መፈናፈኛ አጥተን መስራት አልቻልንም ብለዋል።
እንደ ነጋዴዎቹ ገለጻ፤ አካባቢው፤ የቆሻሻ ማከማቻና ማንም ዞር ብሎ የማያየው ፅዩፍ ቦታ በነበረበት ጊዜ፤ ሥፍራውን ጠርገው አጽድተው ንግድ የጀመሩ ሲሆን ቀስ በቀስ ስራቸውን እያስፋፉና እየተደራጁ በመምጣት ሰላም የገበያ አክስዮንን መመስረታቸውን ይናገራሉ። በመንግስት እውቅናም አግኝተው አሁን ያለውን ግራና ቀኝ የሚገኝ ሱቃቸውን በላሜራ ሰርተው፣ ግበር እየከፈሉ፣ ልጆቻቸውን እያስተማሩና መንግስት የሚፈልግባቸውን የልማት ጥሪ እየመለሱ መዝለቃቸውን ያስረዳሉ።
ይሁን እንጂ በሱቆቻቸው መሃል ባለው መንገድ ላይ የሰፈሩት ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ሙሉ በሙሉ አካባቢውን በመውረር፣ ከጨዋታ ውጭ እንዳደረጓቸው፣ በየቀኑ ሱቅ ቢከፍቱም ምንም ሳይሸጡ ውለው ወደ ቤት ባዶ እጃቸውን እንደሚገቡ፣ በዚህም መንግስት የሱቁን ሁኔታ አይቶ የሚከምረውን ግብር መክፈል እንዳልቻሉና ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁንም የሳሪስ ነጋዴዎቹ ጠቁመዋል።
ህገ-ወጥ ነጋዴዎቹ እኛን ገበያ ከማሳጣት ባለፈ መተላለፊያ መንገዱን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት እሳት አደጋም ሆነ ሌላ ነገር ቢከሰት፣ አምቡላንስም ሆነ ሌላ መኪና በዚያ ቦታ ማለፍ እንዳይችል ደንቃራ ሆነዋል ብለዋል። በየቀኑ ጥለውት የሚሄዱትም ቆሻሻ የጤና ጠንቅ ሆኖብናል፤ ችግራችንን ለመንግስት አቤት ብንልም መፍትሄ አላገኘንም ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል።” “መንግስት ትዝ የምንለው ግብር ሲደርስ ብቻ ነው” ይላሉ ነጋዴዎቹ በቅሬታ።
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት፣ ለተለያዩ ልማቶች መዋጮ ሲጠየቁ ሳያቅማሙ ያላቸውን በማዋጣት የሚሰሩበትን ቦታ ዛፍ በመትከልና ኮብልስቶን በማንጠፍ የተቻላቸውን ሁሉ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጠቆሙት ነጋዴዎቹ፤ በቅርቡ መንግስት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የጀመረውን የህግ ማስከበር  ዘመቻ  ለመደገፍ አክስዮን ማህበራቸው 100 ሺህ ብር ማዋጣቱንም አክለው ገልጸዋል።
ሆኖም በህገ-ወጥ ነጋዴዎች እንቅስቃሴ ሳቢያ ገበያው ላይ ተፎካካሪ ሆነው ነግደው መግባት እንዳልቻሉ የሚገልፁት ሴት ነጋዴዎቹ፤ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ አዋጪ ወደ ሆነውና ግብር መክፈል ወደማይጠይቀው ህገ-ወጥ ንግድ ለመግባት እንገደዳለን ብለዋል።
አንድ እናትም ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃል፤ “ዘንድሮ ግብር የከፈልኩት ጎኔን የማሳርፍበትን አልጋዬን ሸጬ ነው” ብለዋል በምሬት።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ምክትል ስራ አስኪያጅና የንግድ ጽ/ቤት ሃላፊ ሜሮን መንግስቱን በጉዳዩ ዙሪያ ጠይቀናቸው ሲመልሱ፣ ነጋዴዎቹ ያነሱት ችግር ትክክል መሆኑን ጠቅሰው የመሀል መንገድ ላይ የሰፈሩት ኢ-መደበኛ ነጋዴዎች ቲን-ነምበር አውጥተው ወደ መደበኛ ንግድ ለመግባት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
እነዚህን ኢ-መደበኛ ነጋዴዎች ከቦታው አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወርም ከክፍለ ከተማ ጋር በመሆን በመተባበር እየተሰራ ነው ያሉት ሃላፊዋ፤ ለዚህም አምስት ቦታዎች ተለይተው በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ጠቅሰው ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ ጥቂት እንዲታገሱ ጠይቀዋል።
ቦታው ሞቅ ያለ ንግድ የሚጧጧፍበትና በርካታ ነጋዴዎች የሚተራመሱበት በመሆኑ ወረዳው ብቻውን የሚያስተካክለው አይደለም። ለችግሩ የተሟላ ምላሽ ለመስጠት ግን ከክፍለ ከተማው ጋር በንቃት እየሰራን ነው ብለዋል። ሃላፊዋ ሜሮን መንግስቱ።

Read 1001 times