Saturday, 19 December 2020 09:14

በመተከል የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መንግስት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


             በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ በአማራና  በአገው ተወላጆች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን መንግስት እንዲያስቆምና የህዝቡን ዘላቂ ደህንነት እንዲያረጋግጥ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥሪ አቀረቡ።
በመተከል በየጊዜው “ቀዮች” በሚል እየተለዩ ጥቃት የሚፈጸምባቸው አማራና አገዎች በአካባቢው የመኖር ዋስትና ማጣታቸውንና ስልታዊ የዘር ማጥራት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የትህነግን የአፍራሽነትና የጥላቻ አጀንዳ  ለማስቀጠል በቅንጅት የተሰለፉ ሃይሎች ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የሰብአዊ ቀውስ ማዕከል አድርገውታል ያለው የአብን መግለጫ፤ መንግስት ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታበትን መንገድ በአስቸኳይ ሊያበጅ ይገባል ብሏል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መስተዳደር የዘር ጥቃቱን ለማስቆም ፍላጎት እንደሌለው ተረጋግጧል ያለው አብን፤ የፌደራል መንግስትና የአማራ ክልል በጋራ ህዝብን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቋም ሊወስዱ ይገባል ብሏል።
እነዚህ ጥቃቶች አላማም ህዝብን ማህበራዊ እረፍት መንሳት፣ እንዲሁም በመተከል ያለው የአማራና አገው ህዝብ የማንነት ጥያቄን ለማዳፈን ነው ያለው አብን፤  በዚህ ጥቃትም የክልሉ የመንግስት አካላት ጭምር እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁሞ የፌደራል መንግስትም ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን  አክሎ ገልጿል። በተመሳሳይ ኢዜማ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ መንግስት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ትኩረት ሰጥቶ እንዲያስቆም ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጥምረት መስራችና አመራር አቶ ያሬድ ሃይለማርም በበኩላቸው፤ በቤኒሻንጉልና በሌሎች አካባቢዎች፣ በአማራ ተወላጆች ላይ ማባሪያ በሌለው መልኩ እየተፈጸመ ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ገዳዮች ብቻ ሳይሆኑ ጥቃቱን ማስቆም ያልቻለው መንግስት ጭምር ተጠያቂ ነው ብለዋል።
ዘር ተኮር ጥቃቶችን የሚያስቆም መንግስታዊ አካል አለመኖሩ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው ያሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ያሬድ በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከልና በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ውስጥ በአማራ ተወላጆች ላይ  እየተፈፀመ ያለው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ መንግስት በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች የህግ የበላይነትን ማስከበር የተሳነው መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት አመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች ግንባር ቀደም ተጠቂዎች የአማራ ብሔር ተወላጆች መሆናቸውንና በመንግስት በኩል ድርጊቱን ለማስቆም የተደረገው ጥረትም አነስተኛ መሆኑን የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አስገንዝበዋል።
በማይካድራ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ በሻሸመኔ፣ በአርሲና በተለያዩ አካባቢዎች በዘር ላይ አነጣጥረው እየተፈጸሙ ያሉ ጭፍጨፋዎችና የዘር ማጥራት ወንጀሎች በገለልተኛ ወገን ሊጣሩ እንደሚገባ ያሳሰቡት  አቶ ያሬድ  መንግስት በማንኛውም ሁኔታ የዜጎችን ጥቃት እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፤ በመተከል በአማራና አገው ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያና መፈናቀል ከትዕግስቱ በላይ መሆኑንና የፌደራል መንግስትም ሆነ የክልሉ መንግስት ድርጊቱን የማያስቆም ከሆነ፣ የክልሉ መንግስት ገብቶ ህግ ለማስከበር እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
የአማራ ክልል መንግስት ያወጣውን መግለጫ ተከትሎም፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የብልጽግና ፓርቲ በሰጠው ምላሽ፤  ህግ የማስከበር ስራ እየተሰራ መሆኑን፣ ከዚህ ባለፈ በክልሉ ጣልቃ እንግባ የሚለው ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ልዩ ሃይል ሚሊሻ፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው የተሰማሩ ታጣቂዎችን በማደን ላይ መሆናቸወንም የክልሉ መንግስት አክሎ ገልጿል።
በኦሮሚያ፤ በወለጋ ተመሳሳይ ጥቃቶች በኦነግ ሸኔ የሚፈፀሙ መሆናቸውን የጠቆመው የኦሮሚያ ክልላዊ  መንግስት በበኩሉ በታጣቂው ሃይል ላይ ተከታታይ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አስታውቋል።
የክልሉ መግለጫ፤ 780 የታጣቂ ቡድን አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱን ጠቁሟል። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ሰሞኑን ተወላጆች እና በ6 የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ግድያ መፈጸሙን አስታውቋል።
የክልሉ መንግስት ግድያዎችንና ጥቃቶችን እየፈጸመ ነው ባለው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ ተከታታይ እርምጃዎች እየተወሰደ መሆኑንና ቡድኑ ጥቃት መፈጸም የማይችልበት ደረጃ እስኪደርስ መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተገለጸው።

Read 8867 times