Saturday, 19 December 2020 09:41

መቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹን አስመርቋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 በትግራይ ክልል ዋና ከተማ  መቀሌ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል። ከአላማጣ እስከ መቀሌ ድረስ ባለው መስመር የስልክ፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎት መጀመሩም ታውቋል። የኢንተርኔት አገልግሎት ግን አሁንም እንደተቋረጠ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
 የመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት  ኃይለ ገብርኤል አብርሃ ከተማዋ ከቀናት በፊት ከነበረችበት  ሁኔታ በእጅጉ በተለየ ሁኔታ ሠላምና መረጋጋት  እንደሚታይባት ይገልፃል፡፡ ነዋሪውም ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚችልባቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ስራ  መጀመራቸውን የጠቆመው ኃይለ ገብርኤል፤ የባንክ አገልግሎት ግን አሁንም እንደተቋረጠ መሆኑንና ይህም በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩን በመግለፅ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥበት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡
ሌላው የመቀሌ ነዋሪ ትርሀስ ሊላይ በበኩሏ  “ከቀናት በፊት ተስፋችን ሁሉ ተሟጦ ከነህፃናት ልጆቼ መሞቴ የማይቀር መሆኑን አምኜ ነበር ፤የሁለትና የአምስት አመት ህፃናት ልጆቼን ምን ውስጥ እንደምከታቸው ተጨንቄ ነበር፡፡ ፈጣሪ ረድቶን ለዛሬዋ ቀን አብቅቶናል”፡፡ ያንን የመድፍ ድምፅና ተኩስ እንኳን ህፃናት ልጆቼ እኔም ዳግም እንድሰማ አልመኝም፡፡ አሁን ተመስገን ከተማችን ሰላም ሆናለች ሁሉ ነገር ተረጋግቷል። መብራትና ስልክ መጀመሩ ይበልጥ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከተማው ውስጥ ሮንድ እየዞሩ የከተማዋን ፀጥታ እየተቆጣጠሩ ነው”፡፡  ችግራችን የባንክ አለመከፈት ነው፤ መንግስት ባንኮች አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩበትን ሁኔታ ቢያመቻችልን ጥሩ ነው፤ ቅድሚያ መስጠት ለሚገባቸው ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ለችግራችን መፍትሄ ቢሰጠን ነው ጥያቄችን ብላለች።
በከተማዋ በጀበና ቡና ማፍላት ስራ የምትተዳደረው ሃዳስም አሁን በከተማዋ የሚታየው ሰላምና መረጋጋት በእጅጉ እንዳስደሰታት ገልጻ፤ ያሳለፍናቸው ሁለት ወራት ገደማ ለጠላትም አልመኛቸውም ብላለች ትርሀስ፡፡ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የ2013 ዓ.ም ተመራቂ ተመሪዎቹን ከትናንት በስቲያ ያስመረቀ ሲሆን ተማሪዎቹ እንኳንስ ለምርቃታችን ቀን እንበቃለን ብለን ልናስብ ቀርቶ በሕይወት ተርፈን ከቤተሰቦቻችን ጋር እንገናኛለን የሚል እምነት አልነበረንም፤ መመረቃችን ብቻ ሳይሆን በዚህ ፍጥነት አገሪቷ ተረጋግታ ሰላማዊ የምርቃት ቀናችን እና ክብር መብቃታችን ማመን አልቻልንም” ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተውናል፡፡
 በመቀሌ ከተማ ልዩ ስሙ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በህወሃት አመራሮች  ተቀብሮ የነበረ ከ200ሺ ሊትር በላይ የተደበቀ ነዳጅ በቁፋሮ መገኘቱን የመከላከያ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ በ13 የነዳጅ ታንከር የተቀበረው ይኸው 200 ሺ ሊትር ነዳጅ በቁፋሮ  እንዲወጣ መደረጉም ታውቋል፡፡ በሌላ ስፍራም በተመሳሳይ መንገድ የተቀበረና ገና በነዳጅ ያልተሞላ ዘጠኝ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ታንከር ተገኝቷል ተብሏል፡፡

Read 12597 times