Monday, 21 December 2020 00:00

ለድሃ አገራት የታሰበው የኮሮና ክትባት 2 አመት ሊፈጅ ይችላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለድሃ አገራት በወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለማዳረስ ተብሎ የተቋቋመው አለማቀፉ የኮሮና ጥምረት ለአገራቱ ክትባቱን በአፋጣኝ የማድረስ ዕቅዱ ከፍተኛ ስጋት እንደተጋረጠበትና ጥምረቱ ክትባቱን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሚኖሩባቸው አገራት እስከ ፈረንጆች አመት 2024 ላያደርስ እንደሚችል መነገሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት የጀመረውና ኮቫክስ የተባለው ዋነኛ ፕሮግራም እስከ መጪው የፈረንጆች አመት 2021 መጨረሻ ድረስ በ91 ድሃና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአለማችን አገራት ለሚገኙ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች 2 ቢሊዮን ያህል ክትባቶችን ለማድረስ አቅዶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ያም ሆኖ ግን ፕሮግራሙ በገንዘብ እጥረትና በሌሎች እንቅፋቶች ሳቢያ ግቡን ላይመታ የሚችልበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን የሚያሳዩ መረጃዎች መውጣታቸውን አመልክቷል፡፡
ኮቫክስ በመጪው አመት ክትባቶችን ለድሃ አገራት ለማዳረስ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት 7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው የጠቆመው ዘገባው፣ እስካሁን ድረስ ማሰባሰብ የቻለው ግን 2.1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ብቻ መሆኑንና ለጋሾች በአፋጣኝ እርብርብ ማድረግ ካልጀመሩ ዕቅዱ ሳይሳካ እንደሚቀር መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ መረጃ፣ ባለፈው ሃሙስ አዛውንቶችንና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት መስጠት የጀመረችው ብሪታኒያ፣ በሳምንቱ 140 ሺህ ያህል ሰዎችን መከተብ መቻሏን ዘ ጋርዲያን የዘገበ ሲሆን ቢቢሲ በበኩሉ፤ ከሰሞኑ ለፋይዘር ክትባት እውቅና የሰጠቺው አሜሪካ ባለፈው ማክሰኞ ሞደርና የተባለው ሌላ ክትባት 94 በመቶ አስተማማኝ መሆኑን በማረጋገጧ፣ ለክትባቱ እውቅና መስጠቷንና ይህም ክትባቱን ለሰዎች ለመስጠት በር ከፋች መሆኑን አስነብቧል፡፡

Read 2917 times