Tuesday, 22 December 2020 00:00

የ82 አመቱ የጊኒ መሪ ለ3ኛ የስልጣን ዘመን ቃለ-መሃላ ፈጸሙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የላይቤሪያ መሪ የስልጣን ዘመን ከ6 ወደ 5 አመት ዝቅ ሊል ነው

         ስልጣንን ያላግባብ ተጠቅሞ በዙፋን ላይ እስከ ዕለተ ሞት የመቆየትን ኩሸት በጸጋ አንቀበልም ያሉ ዜጎችን ለከፍተኛ ቁጣ ዳርጎ ለተቃውሞ አደባባይ ባስወጣና በመቶዎች የሚቆጠሩትን ለሞት በዳረገ አወዛጋቢና ተቃውሞ ያልተለየው ምርጫ፣ አሸናፊነታቸውን ያወጁት የጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ፤ ባለፈው ማክሰኞ ለ3ኛ የስልጣን ዘመን ቃለ-መሃላ የፈጸሙ ሲሆን በላይቤሪያ ደግሞ የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን እንዲቀነስ ህዝቡ ወስኗል፡፡
የ82 አመቱ የእድሜ ባለጸጋ የበርካታ አፍሪካ አገራት መሪዎችና ደጋፊዎቿቸው በተገኙበት በፈጸሙት ቃለ መሃላ “አገሬን ከዚህ ቀደሙ በተለየ መልኩ ለማስተዳደር ስላሰብኩ አታስቡ፣ ያለፈውን መጥፎ ጊዜ እርሱት” ሲሉ ለህዝባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የቀድሞው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩትና እ.ኤ.አ በ2021 በተደረገ ምርጫ አሸንፈው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን የያዙ የመጀመሪያው የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር መሪ የነበሩት ኮንዴ፤ በ2015 በድጋሚ ምርጫ አሸንፈው በስልጣን ላይ ቢቆዩም፣ ከወራት በፊት ህገ መንግስቱን አሻሽለው ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር መወሰናቸው አገሪቱን ወደ ብጥብጥ እንዳስገባት ሮይተርስ አስታውሷል፡፡
በላይቤሪያ በአንጻሩ፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የቀድሞው የአለም የእግር ኳስ ኮከብ ጆርጅ ዊሃ ያቀረበውን የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን ቆይታ የሚያሳጥር የህገ መንግስት ማሻሻያ፣ ህዝቡ በአብላጫ ድምጽ እንዳጸደቀው አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አንድ የስልጣን ዘመን ቆይታ ከስድስት አመት ወደ አምስት አመት ዝቅ እንዲል ከቀረበው የህገ መንግስት ማሻሻያ በተጨማሪ፣ ተደራራቢ ዜግነትን በሚከለክለው ረቂቅ ህግና ሌሎች ማሻሻያዎች ላይ ድምጹን መስጠቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2640 times