Wednesday, 23 December 2020 00:00

አመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች የታሰሩበት ነው - ሲፒጄ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት እድሜ ብቻ በቀረው የፈረንጆች አመት (2020) በአለም ዙሪያ በድምሩ ከ274 በላይ ጋዜጠኞች በስራ ገበታቸው ላይ ሳሉ ለእስር መዳረጋቸውንና አመቱ በታሪክ ከፍተኛው የጋዜጠኞች እስር የተፈጸመበት መሆኑን አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ ሰሞኑን አስታውቋል፡፡
እስካለፈው ታህሳስ 1 ቀን በነበሩት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በአሜሪካ፣ አፍሪካ፣ አውሮፓ፣ የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ አገራት ቢያንስ 274 ያህል ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸውንና በአብዛኞቹ የአለም አገራት ለጋዜጠኞች እስር መበራከት በሰበብነት የሚጠቀሱት ተቃውሞዎችና ፖለቲካዊ ውጥረቶች መሆናቸውን ተቋሙ ባለፈው ሰኞ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ ገልጧል፡፡
ባለፈው አመት በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ከአለማችን አገራት ቀዳሚዋ የነበረችውና ባለፉት 12 ወራት ስለ ኮሮና ዘግባችኋል ብላ የያዘቻቸውን ጨምሮ 47 ጋዜጠኞችን ያሰረችው ቻይና፣ ዘንድሮም በጋዜጠኞች ላይ የከፋ ጥቃት በማድረስ ቀዳሚዋ የአለማችን አገር መሆኗን ሪፖርቱ ያሳየ ሲሆን፣ ቱርክ፣ ግብጽና ሳዑዲ አረቢያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በአመቱ በተለያዩ የአለማችን አገራት በጋዜጠኞች ላይ እስር፣ የወንጀል ክስ፣ ድብደባና የመብት ጥሰቶችን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶችና በደሎች መፈጸማቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በአሁኑ ወቅት በመላው አለም በእስር ላይ ከሚገኙ ጋዜጠኞች መካከል ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከሽብርተኝነትና ከህገወጥ ቡድኖች ጋር በተያያዘ ክስ የቀረበባቸው እንደሆኑም አክሎ ገልጧል፡፡
የፈረንጆች አመት 2020 አሜሪካ በታሪኳ አድርጋው የማታውቀውን የ120 ጋዜጠኞች እስር የፈጸመችበት ነው ያለው ሪፖርቱ፣ በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል በጋዜጠኞች እስር ከፍተኛ መጨመር ታይቶባቸዋል ሲል ሪፖርቱ የጠቀሳቸው ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያና ቤላሩስ ናቸው ብሏል፡፡

Read 5606 times