Print this page
Saturday, 19 December 2020 13:29

“መላዕኩና ልጂት”

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(8 votes)

“ሊኖር ያሻል - ጤና። ህይወት እስካለ - መኖር እስከቀጠለ” ትላለች አክስት አስካለች። እንደማትሰማት ብታውቅም ቅሉ።
እንደ ድንገት ከውዥንብር ባህር ተዘፈቀች። ብቻዋን ስታወራ... የባጥ የቆጡን ስትለፈልፍ ትውላለች። ቁርጥራጭ እንቅልፍ ..ንጭንጭ... ብስጭት... ቅዠት መልህቁን ጥሏል - እልቧ ላይ። ተሸግና የሄደችበት ያ ጎዳና፤ አሁን በእብደት ክርታዝ ተጠቅልላ ትድህበት ሆነ። እንዳይዋት የወደዷት፣ ጠይም የደስ ደሷ ስቧቸው እግሯ ሥር እንደ ነፍሳት ይወድቁ የነበሩ አዳሞች አሁን አይታዩም። ምፀት በአራቱም ማዕዘናት እዚህች እንስት አናት ላይ ይርከፈከፋል። ከሁሉም አቅጣጫ እዝነት ይጎርፋል። ምናልባት የአንጀት። ምናልባትም ያንገት - እዝነት።
“እምፅ”
ብዙዎች ያዝናሉ። አንዳንዶች ደሞ አያዝኑም። ጥሩ ስራ ነበራት። ትነግድ ነበር። በአንዲት የተረገመች ዕለት ግን ( አሉባልተኞች እንደሚሉት) እረፍት አስፈለጋት። በስራ የደከመ አካልዋን ማሳረፍ ሻተች። ሰራተኛ ቀጥራ ትንሽ ማረፍ ፈለገች።
ማታ ማታ ብዙ ህልም ታልማለች። ብዙ ነገር ይመጣባታል። አክስቷ ጠዋት የመኝታ ቤቷን መስኮት ስትከፍት፣ ተግተልትለው የሚገቡ የፀሃይ ጨረሮች ቤቷ ግርግዳ ላይ ሲያርፉ...የተሰቀለው የመላዕክ ምስል እንደ ወስፌ ይወጋሉ - ይህንንም ትመለከታለች። በነሲብ እጇን አንስታ ወደ ደረቷ ትልካለች። ልቧ በጣሙን ይመታ ነበር። ጭንቀት ነበረባት። ምን እንደሚያስጨንቃት ግን አታውቀውም። ማንም ሊያውቅ አይችልም። እዉን ጭንቀት ነበረባት? የምትናፍቀው የለም። እናት አባቷ ቅርቧ ናቸው። ተመላልሰው ይጠይቋታል እንጂ በእርግጥ አብረዋት አይኖሩም። አክስቷ አጠገቧ አለች። ልረፍ ብላ ቤት ስትዉል ግን እንዲሁ ይዞርባት ጀመረ። ቀን የማታ ህልሟን ታስባለች። ስራውን ጭራሽ ተወችው። ጭራሹን ስራ እንዳላትም ዘነጋች። መሽቶ ማለሙን ትፈልጋለች።
* * *
እንደ ጥጥ ነጭ ገፅ አለው። ከንፈሩን አንገቷ ውስጥ ያርመሰምሳል። አንዳንዴ ሰፌድ በሚያክሉ ፀኣዳ እጆቹ ፊቷን ይዳብሳል፤ ሲለው ደሞ ፀጉሯን... ወለሉ በትላልቅ ክንፎች ተሞልቷል። ንጣታቸው ገላጭ ያጣ ... ትልቅ ሰይፍ ከአልጋዋ ስር ተንጋሎ ይታያል። አንዳንዴ እሳት ታቅፎ ይመጣል። መብራቱን አጥፍተው ጥሩ ምሽት ያሳልፉበታል፤ አገልግሎት ላይ ውሏልና... ሁሌም ክፍሏ የማይጠፋ የዕጣን ማጨሻ ዕቃ ውስጥ ያስቀምጠዋል።
“እወድሻለሁ” አላት።
“ለምን አትወስደኝም - አንተ ጋር” ከት ብላ ትስቃለች። ያ ጎራዳ አፍንጫዋን ከአፏ ጋር በእጇ ይዛ። አፋራም ሳቅዋን ታሳያለች። ግን ከት ብላ...  ፒጃማዋን እየገለጠ ገላዋን መዳሰስ ይጀምራል።
“ጊዜው ገና ነው!” ገላዋን እየዳሰሰ “ምዑዝ ምዑዝ" ይላታል። ምን እንዳለ አይገባትም። አንዳንዴ የሚናገረዉ ፈፅሞ አይገባትም።
* * *
ገሚሱ አውቆ አበድ ናት ይላል። ጥቂቶች እርኩስ መንፈስ ነው ይላሉ። አንዳንድ አወቅን ባዮች፣ ዘመናዊ ቀለም በጥብጠን ጠጣን የሚሉ ጨላጦች ደሞ የአዕምሮ ችግር እንደገጠማት ይናግራሉ። ልክ ናቸው ተባለ።
“እዪው ከዚያ ሰማይ ላይ የተሰቀለውን መላዕክ፤ ፀዳል ገፁን ተመልከችማ! ደመናን ተንተርሶ የሚኖር ነው። ሊወስደኝ ይመጣል። አግብቶኝ ሊኖር። ማታ እኮ ማለልኝ። እንደ እሱ ነጭ ወርቅ የመሰሉ መንታ ልጆች እወልድለታለሁ። ማህፀኔ በነጭ ወርቅ ይጥለቀለቃል... እግዜር ከሰማይ ትልቅ ቤት ሰርቶ ይሰጠናል። ባይሰጠንም ደመና ላይ ጎጆ እንቀልሳለን። ፍቅር ካለ ሁሉም ሙሉ ነው። ያለ ፍቅር ግን ሙሉ ይጎድላል። ፍቅር አለን። እግዜር ባለ አራት ክፍል ቤት ከሰጠን እሰየው። መርቆ ከሽኘንም ደግ! አለዚያ ፍቅር ይበቃናል። የፍቅር አለም ውስጥ እግዜር ቢቀር አይጎድልም... እዪው... ሊያገባኝ ነው - የሚመጣው። በእርግጥም ያገባኛል።"
“ኧረ ተዪዪዪ! የምን መላዕክ ነው” አክስቷ አስካለች... ቆጣ ትላለች።
“ቀንተሽ ነው - ማርያምን ! አስካለች ሙች ይወደኛል። ሲመሽ ሲመሽ ነው የሚመጣው። አንቺ መተኛትሽን ሲያውቅ ነገር... አሁን መሬት ደርሶ ይዞኝ ሲሄድ ታያለሽ።”
አክስቷ ቤት ነው - የምትኖረው። አማኑኤል ሆስፒታል ተመላላሽ ታካሚ ናት። የምትውጠው መድሃኒት አደንዝዞ ከባድ እንቅልፍ ይለቅባታል።
“ቀረብኝ እኮ” ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች።
“ኧረ ተዪ!”
እውነቱን ያውቃል ልቧ። ከዚያ ሰማይ ላይ ክንፉን ዘርግቶ የሚወርድ መላዕክ፣ ሊያገባት የቋመጠ ፀዳል መላዕክ ፣ በፍቅሯ የተነደፈ፣ ሁለንተናዋን ሽቶ ልቡን ሊሰጣት የተዘጋጀ መላዕክ... ምናልባት የእብደት ደጎል ይሆናል - የጀቦናት። የቅዠት ለምድ ለብሶ የሚመጣ... ለፍቅር ያደባ መላዕክ... ቀን የሚቆጥር... በእርግጥም ልክ ነች። ምናልባት የእውነት ዓለም ሲመጥቅ፣ የቅዠት ምድር ላይ ሊያርፍ ይችላል። እነሱ እኮ በአንድ ገበታ ይበሉ ይሆናል። ጥንዶች፣ አንድ አካል አንድ አምሳል ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባት ያልደረስንበት፣ ልንደርስበትም የማንችል ሆኖ ነገርየው፣ ውዥንብሩን ሸምነን ይሆናል።
“ጊዜው አልደረሰም ሲል ምን ማለቱ ነው?” ታስባለች!
ጠይም ገጿ ላይ የሚያበሩ ትልቅ ዓይኖች አሉ። እንደ ቤተ መቅደስ ጠዋፍ ይንተገተጋሉ። ከግንባሯ ሰፍታ ውርድ እየጠበበች ትሄዳለች... ጎራዳ አፍንጫዋን አንዳንዴ እንደ መንፋት እያደረገች በዓይኗ ሥር ታየዋለች። ይሄም ጦሽ አድርጎ ያስቃታል። ሳቅ አትችልም። በፊት በፊት ለሁሉም ነገር ሳቅ ይቀናት ነበር። ስትለከፍ ትስቃለች። ስትወደድ ትስቃለች። ስትታቀፍ ሳቅ ያመልጣታል። ስትሰደብ እንኳ ጦሽ ብላ የምትስቅ ነበረች። አሁን አሁን ደብዝዘው ...ሳቅዋን የተካ ንዴት ነው። አንዳንዴም ያ - የቅዠት ፍቅር። ታዲያ በቅዠቷ ያን የድሮ ሳቋን ታያለች። ጉንጯ ማህል ላይ ጥቋቁር ነቁጥ ጉብታዎች አሉ። `የቃል ኪዳኑ ማህተም ናቸው` ትላለች... `እናንተ እንደምታስሩት ቀለበት ያለ ነው`
ሰንበት ሰንበት ይመጣሉ - ቄስ ባህታ። በችኮላ የሚያንቸለችሉት ፀሎት አለ። ውሃ በጆክ ተሞልቶ ይሰጣቸዋል። ግዕዝን በምላሳቸው ያካልቡታል... አስካለች ባይገባትም እጇን ዘርግታ ትቆማለች። አንዳንዴም ከሚያገለግሉበት ደብር ፀበል እያመጡ የግዷን ያጠምቋታል።
“እኚህ ሰውዬ ጂኒያም ናቸው። መልዓኬ እንዲፀየፈኝ ከሰይጣን የተላኩ ናቸው። ሊያቆሽሹኝ ነው የመጡት። አስውጪልኝ ! አስወጪልኝ..."
“ኧረ እንዲህ አይባልም...”
“ተያት አስካለች! ወድዳ እኮ አይደለም። የያዘ ይዟት ነው”
በደንብ እረጭተዋት ይሄዳሉ። አብዛኛው ፀበል ፊቷን ሲያላጋ ነው የሚያልቀው። ከዲንጋይ ጋር እንደሚጋጭ ፏፏቴ አይነት ድምፅ ያወጣል... እየሳሳ የሚያደበይ አይነት...ግንባሯ እንደ አለት ያለ ነው። ጅስሟ ቅዝቅዝ ይላል. . .ፍርሃት ልቧ ላይ ዳሱን ተክሎ እንደ ሆነ ዓይነት ልዩ ፍጡር ያፃማታል።
“አንቱ ሰውየ ይተዉ እኮ ነው የምለው...ኡኡኡኡኡ...” ቤቱን በጩኸት ትንጠዋለች ...
“ቀረብኝ ማለት ነው” ከዓይኗ እንደ ምንጭ የሚፈልቁ ፈጅ ፍሳሾች ጉንጯን እየላጡ ወደ አንገትዋ ይወርዳሉ. . .ጉሮሮዋ በሳግ ተወጥሮ፣ እንደምንም...  “ይወደኛል እኮ” ትላለች። ማመን የምትፈልገው ይሄን ነው። ስለዚህም ሁሌ ትናገረዋለች። እንደዚያ ነው የአኗኗር ቀመሯ። ማመን የፈለጉትን በሚናገሩና በሚሰሙ ተከባ ያደገች ናት።
የመውደድ ጉድኝት ትሻለች። የምታየው ያን ገፁን...በዓይኗ ህሊና የምትስለው እሱን እሱን ብቻ ነው። ካለ’ሱ ማንንም አታውቅም። ካለ’ሱ ማንም አይወዳትም። አልፋና ኦሜጋዋ እሱ ነው ። መጠበቁ ሰቀቀን ነው። እንደ አተም ልቧን ስነጣጥቆ ከአንጀቷ የሚቀብረው ቦምብ አለ - መቅረቱ። ሳምንታት አለፉ... ወራትን አምጠው ቢወልዱም ዝር አላለም። በሰመመኗ የተሸመነው ፍቅር ብዙ ጊዜ ሆነው ከመጣ። ካየችው ቆየች...
“ዛሬም ቀረብኝ” ጠዋት ተነስታ ታላዝናለች።
እንቅልፏ ጥልቅ ነው። ቁርጥራጭ ጥልቅ። መፈራገጥ... መጮህ... አልፎ አልፎ እንጂ እንደ ምዉት ትንፋሿ እንኳ አይሰማም። ልብ ምቷ ቀሰስተኛ ነው።
1:30
መድሃኒቷን የምትወስድበት ነው - ጊዜው። ጥቂት እንደ ፈዘዘች ከባድ እንቅልፍ ይጥላታል። ለመተኛት ወደ አልጋዋ ስትሄድ፣  ሁሌም በተስፋ ነው። «ይመጣል» ይሉት ተስፋ! ከተስፋም የቅዠት ተስፋ... ህልም መሰል ተስፋ...
ቤቷ በዕጣን ጭስ ታውዷል። አልጋ ላይ ተንጋላለች። በህብረ ቀለም የነደደ አልጋ ልብስ እላይዋ ተኮፍሷል። ክንፎቹን እያራገበ ቆሟል - የጠበቀችው። በፊት በፊት ክንፎቹን ነቃቅሎ፣ እንደ ጨርቅ መሬት ጥሏቸው ተቻኩሎ ብርድ ልብሷ ውስጥ ይገባል። ከንፈሩን አንገቷ ውስጥ እያርመሰመሰ፣ በሰመመን ጥልቅ ንቃት እንደ ደመና ከፍ አድርጓ ይሰቅላት ነበር። እያያት ብዘ ቆመ። እየጠበቃት... መልሶ ወደ አልጋዋ ይቀርባል... ደሞ መልሶ ይሸሻታል... ውሳኔው ልክ እንዳልሆነ ቂላቂል ሰው ዓይነት...የሚፈራው አካል እንዳስጠነቀቀው ዓይነት...
ፈገግ ብላ አየችው። ተነስታ እጁን እየጎተተች... ወደ አልጋው እያስጠጋች... አልጋው ጠርዝ ላይ ቁጭ ብሎ እንደ ህፃን አይኑን ያቁለጨልጫል... የለበሰችውን ባለ ሙሉ ቀሚስ ፊቱ አወለቀች። የጡቶቿ ጫፎች ነቁጥ ፀሊም ጉብታ አላቸው። እጉንጯ ላይ እንዳሉ ... ቃል ኪዳን እንደምትላቸው አይነት ናቸው። ትልቅ ሰይፍ መሬት ላይ ተጥሏል። አንዳንዴ ፀሊም ጉም መሰል ነገር ከአናቱ ላይ ይተናል። ይኼኔ እነዚያ ብርሃን የሚረጩ ዓይኖቹ፣ እንደ ሸማኔ መቂናጥ ወዲያ ወዲህ ይሉና ደም ይለብሳሉ።
እላይዋ ላይ ብዙ እንደቆየ የዘር ፍሳሹን ውስጧ አስርጎ ሲካለብ ተነሳ። ክንፎቹን ከወዳደቁበት አንስቶ ጎን ጎኑ ተከላቸው። ሰይፉን በግራ እጁ አንስቶ ያዘ።
“አትሂድ” አለች።
ዝም! ግር በሚያሰኝ ዓይን ያያታል። ትስቃለች። አፏን ይዛ ደጋግማ ትስቃለች።
“እወድህ አይደል. . .አትሂድብኝ”
ዝም!
5:48
ያለ ሰዓቷ ነቃች። ከሌላው ጊዜ በተለይ ዓዲስ ስሜት ውስጧ ይርመሰመስ ነበር። ፊቷ ፈገግ እንዳለ ነው። እርቃን ገላዋን ነበረች። ኩርማን የብርድ ልብሷ አካል መሬት ወድቋል። ተነስታ መስኮትዋን ከፈተች። ግማሽ ጨረቃ ብራማ መልኳን አዳምቃ፣ ኩል ከመሰለው ሰማይ ላይ ተሰቅላለች። ከእግዜር መስክ ላይ የተዘሩ ከዋክብት እንደ እንቁ ያበራሉ።አሻግራ ትመለከታለች። እርቃን መሆንዋን ልብ ያለች አትመስልም። ብትልም እንዲህ መሆን አስፈልጓት ነበር።
[ ድ ህ ራ ይ ]
ቀስ በቀስ ጤናዋ እየተሻሻለ መጣ። የምትቀባጥረው፣ ደጋግማ ስሙን የምትጠራው መላዕክ እንደ ተረሳ የሰው አካል፣ እንደ ማይፈለግ ግዑዝ ሆነ። ከጥቂት ዝምታ፣ ከጥቂት ድብርት ውጪ ጤናዋ እየተመለሰ ሄደ። ሲከታተሏት የነበሩ ሃኪሞች ስራቸው ውጤት ማስገኘቱን አመኑ። ቄስ ባህታ ’የፀበል ሃይል እስከዚህ ነው’ እያሉ የእግዜርን ተዓምር ለአገኙት ሰው ሁሉ አበሰሩ። በዚህ መኻል ሆድዋ እየገፋ መምጣቱን ማንም ልብ አላለም።
________________________
¹ ሽቶ የተቀባ አካል: ጥዑም ጠረን የሚያውድ

Read 2420 times