Print this page
Saturday, 19 December 2020 13:31

“ቀለም እና ውበት” መድበልን በወፍ በረር

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(5 votes)

 ናጡት ናጡት ይላል መግፋት የለመደ፣
መገፋት አይደል ወይ እኔን የወለደ፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ዕድሜዋ 20 ዓመት እንኳ በቅጡ ያልሞላት አንዲት ወጣት ቅርበታችንን መሰረት በማድረግ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ግጥሞች ታነብልኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የምታነበው በቃሏ ሲሆን ግጥሞቹ ባብዛኛው በራሷ የተጻፉ ነበሩ። ሆኖም የአፍላ ወጣቷን ግጥሞች  በቅጡ ሳላጣጥም ነው አብረን ስንሰራ ከነበረበት መሥሪያ ቤት የለቀቅሁት፡፡
ወጣቷን ከዚያ በኋላ ያገኘኋት በፌስቡክ ነው፡፡ ልጅት በፌስቡክም ትገጥም ገባች፡፡ በዚህ የማህበራዊ ገበታ ላይ ጥቂት ግጥሞቿን አንብቤአለሁ፡፡  አንዱ ግጥሟ “ናጡት” ይላል፡፡  
ናጡት ናጡት ይላል መግፋት የለመደ፣
መገፋት አይደል ወይ እኔን የወለደ፡፡
በዚህ ግጥም ውስጥ ተናጋሪው “ቅቤ” ነው። መገፋት ላይ ላዩን ወተት መናጥ ቢሆንም፣ ውስጡ ግን በደልን፣ ግፍን የሚወክል እምቅ ግጥማዊ ቃል ነው፡፡ ግጥማዊ ቃላት ይላሉ ብርሃኑ ገበየሁ፣ በአማርኛ ስነግጥም መጽሐፋቸው- ግጥማዊ ቃላት ደራሲው ከሌሎች ቃላት መርጦ ለኪናዊ ተግባሩ የሚገለገልባቸውን ቃላት የሚያካትት ነው፡፡
በሔለን ፋንታሁን ግጥሞችም ብርሃኑ ገበየሁ ያሉትን ግጥማዊነት አይቻለሁ፡፡ ገጣሚዋ ሔለን በተለያዩ ጊዜያት የከተበቻቸውን ግጥሞች፣ ”ቀለም እና ውበት” በሚል ርዕስ አሳትማ ለንባብ አብቅታለች፡፡   በ85 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በ99 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
በመጽሐፉ የምስጋና ገጽ ገጣሚዋ፣ “ለካስ ሰው ሞልቶኛል” በማለት አዎንታዊ አመለካከት (Positive thinking) አንጸባርቃለች፡፡ ገጣሚዎች ጨለምተኛ ናቸው የሚለውን መነሻው የማይታወቅ እሳቤም አምክናለች፡፡
”ቀለም እና ውበት” ሃምሳ ሁለት ግጥሞችን ያካተተች መድበል ናት፡፡ ውብ ግጥሞችን ታስነብበናለች - የሁላችንንም ማኅበራዊ እሴቶች የሚዳስሱና የሚያንጸባርቁ፡፡ ወጣትና ጀማሪ ገጣሚ ብትሆንም፣ በንባብ የበለጸገ እውቀት እንዳላት ግጥሞቿ ይመሰክራሉ፡፡ ሔለን በስንኞቿ ተደስታ ታስደስተናለች፣ ተከፍታ ታስከፋናለች፡፡ አማርራ ታማርረናለች፡፡ ስቃ ታስቀናለች… ተመራምራም  ታመራምረናለች፡፡
ግጥሞቿ በቅርጽም መልዕክት ያስተላልፋሉ። ለምሳሌ “ጠብታ”ን እንይላት፡፡
ጠብታ



ከባዶ ፎሌ ተገኝታ፣
አፋጀች አሉ በምኞት
ያም ለኔ፣ ያም ለኔ ሲላት
ርሷ ግን…
ታውቃለች እና ውበቷን
በምኞት ብቻ ማርካቷን




ላለ መገኘት ታመነች
ይህ ገጸ ጽሑፋዊ ፍንገጣ (graphological deviation የሚታይበት ግጥም፣ የማን ታሪክ ነው ካልን የአንዷ በአካባቢያችን የምናውቃትን ማለት ነው- በፊት ለፊት ስናየው፡፡
ባዶ ፎሌ= ተስፋ ቢስነት (ብርጭቆው በግማሽ ውሃ አለው ከማለት በግማሽ ጎድሏል እንደ ማለት)
አፋጀች አሉ በምኞት = የተመኟት ተሻሟት ተፈራረቁባት
ታውቃለች እና ውበቷን= ከሷ ምን እንደሚፈለግ
በምኞት ብቻ ማርካቷን= (በቁሙ)



ች= ከሰመች፣ ውበቷ ጠወለገ
ላለመገኘት ታመነች= ነይ ካላት ባለጊዜ ጋር ሁሉ ሔደች እንደማለት ነው፡፡ ለኔ ይህ ግጥም የአንዲት በወሲብ ንግድ የምትተዳደር እንስት ሕይወትን፣ ከመጀመርያ እስከ ፍጻሜው ያስቃኛል፡፡
አንድም በአንዲት እንደ ኢትዮጵያ ባለች የሀብታም ድሃ (ሀብት እያላት የምትራብ) ሀገርን መስላበታለች፡፡ ከድህነት አዘቅት ትገኛለች ፣ ኃያላን ለሀብትና ስትራቴጂክ ጠቀሜታዋ ሲሉ ይራኮቱባታል፣ ሀብቷን ታውቃለች ግን በዕዳ ክምር ጠፋች እንደ ማለትም ይሆናል፡፡
ግጥሙ በተጨማሪም፣ የማይጨበጥ ምኞትን፣ ተስፋ አልባ ሕይወትን፣ ግለኝነትን… በጥቂት ስንኞች ቀንብቦ የያዘ ነው፡፡
አፍቃሪነትን በመንገደኛነት በመሠለችበት “መንገደኛ ሆንኩልህ” የተሰኘ ግጥሟ እንዲህ ትላለች፡-
ብክንክን ማለትን አለመርጋትን አመላካች ነው ለኔ፡፡
መንገደኛ ሆንኩልህ ረፍት አልባ፣
ቤት ለእንግዳ ላለኝ ሁሉ የማልገባ፡፡
(ስለ መጪው እርግጠኛ አለመሆንንም ጠቋሚ ነው፡፡)
ሕልሜ ሆነ እስከ እርምጃ
ስለ ነገ ሁሌም እንጃ፡፡
(ለፍቅርና ለፍቅረኛ እስከ መጨረሻ መታመንንም ያመለክታል፡፡)
እነጉዳለሁ!
እሔዳለሁ!
ካንተ ውጪ ላለመውደድ
ካንተ ውጪ ላለመልመድ፡፡ (ገጽ 12)
“ዕጣ” የሚለው ግጥም ደግሞ በአገልግል አሠራር  አስታኮ  መልዕክት የተላለፈበት ነው፡፡ ሰው እንዲኖር ሰው ይገደላል፡፡ ሰላም ለማምጣት ሰላማዊ ሰው ይሞታል፡፡ ዲሞክራሲ ለማስፈን ሰው አትናገር አትጋገር ይባላል፡፡ ስለአፈቀርኩሽ ገደልኩሽ አይደል ያለው ሼክስፒር በኦቴሎ፡፡
“እንቆቅልሽ ቅኔ” የወሲብ ተዳዳሪዎችን የሰቆቃ ሕይወት ያንጸባርቃል፡፡ ልበ ልቦናቸው ውስጥ ጠልቀን ገብተን ጎስቋላ ኑሮአቸውን እንድንጎበኝ ያደርገናል፡፡ በዚህ ግጥም ልጅ እናቱን ይጠይቃል፡-
እንቆቅልሽ፣
ምን አውቅልህ?
ዐይኖቿን ተኩላ ገበያ የምትወጣ
ብሎ ይጠይቃል
ድንግጥ ትላለች
ልቧ ይሸበራል÷ ፍርኃት ትወርሳለች
’እንጃ ትለዋለች’
እሱ የጠበቀው “ባቄላ” የሚል መልስ ነው። የእንቆቅልሹ እንቆቅልሽ ግን ዐይኖቿን ተኩላ ሥጋዋን ለመሸጥ ገበያ የወጣችው እናቱ ነች፡፡
በሌላ የሕይወታችን አጽቅ ትልቅ ቦታ የሰጠነው አንሶ ሲገኝ፣ የማይደረስበት የመሠለው በቀላሉ ሲደረስበት፣ ልዩ ያልነው ተራ ሲሆን፣ በቀላሉ ሲገኝ ይታያል፡፡ ለዚህም ይመስላል “ይሁና” ባለችው ግጥም፡-
 እሩቅ መስሎኝ የሸኘሁህ
ላልደርስብህ የሰቀልኩህ
ጎኔ ኑረህ ነው ለካ
ልቤ በናፍቆት ስላቅ የፈካ!!
 “ክፍተት” ግጥም ደግሞ የተቃርኖ ውበት (binary opposition)  የታየበት ግጥም ነው፡፡
አዳምና ሔዋን
እሳት እና ውሃን
ጥቁር እና ነጩ
ሙቀት እና ውርጩ
ለግጥም መድበሏ ምስጋና ይግባውና፤ የሔለንን ግጥሞች ከሞላ ጎደል ለመቃኘት ችያለሁ፡፡ ግን ይህች የቀድሞ ባልደረባዬ፤ አሁን የት እንዳለች አላውቅም፡፡ ግጥሞቿን ግን መኮምኮሜን አቀጥላለሁ፡፡
ሰማይ ነው ይላሉ የጨረቃ ቤቷ
እኔ ግን እላለሁ ልቤ ነው በረቷ
ሞልታ ስታጎድል ታይቶኝ እኔነቷ፡፡
እናንተም ይህን የግጥም መጽሐፍ አንብቡትና በየራሳችሁ መንገድ ተርጉሙት፣ አጣጥሙት፡፡
ቸር እንሰንብት!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1429 times