Print this page
Wednesday, 30 December 2020 10:08

በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ በተላለፈው ውሳኔ ዙሪያ ምርጫ ቦርድ ለአዲስ አድማስ የሰጠው ማብራሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 አሟልተዋል የተባሉት ፓርቲዎች ከ35% በላይ ያመጡት ናቸው አወዛጋቢው የህወኃት ጉዳይ ገና በቦርዱ እየታየ ነው

            ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ የፓርቲ መስፈርት አላሟሉም ያላቸውን 26 ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ ሲሰረዝ ፣12 ፓርቲዎች ተጨማሪ ሰነድ እንዲያሟሉ ጠይቋል፡፡ 40 ሀገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎች ደግሞ መስፈርቱን አሟልተው የተገኙና ህጋዊነታቸውን ያረጋገጡ ሆነዋል፡፡ ቦርዱ ባካሄደው ማጣራትና በቀጣይ ሊመለከታቸው ስለሚገኙ ጉዳዮች የኢትዮጵያ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡ ቦርዱ የተለያየ ውሳኔ ያሳለፈባቸው የፖለቲካ ድርጅት ዝርዝር ከቃለ ምልልሱ ጋር ተያይዞ ቀርቧል፡፡
የተሰረዙ ፓርቲዎች ድጋሚ ጉዳያቸው የሚታይበት እድል ይኖር ይሆን? ከተሰረዙ በኋላ ያለው አማራጭ እንደገና መመስረት ነው፡፡ እንደ አዲስ ነው
የመመስረት ሂደት መጀመር የሚችሉት። ያለውን ይዞ መቀጠል አይቻልም፡፡ ስያሜም አዲስ ነው የሚሆነው፡፡ የበፊቱ ከተባለ በሌላ አለመያዙ ተረጋግጦ ነው ሊሰጣቸው የሚችለው፡፡ ቦርዱ የመሰረዝ ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ነው፡፡ በይግባኝ የሚታይ ነገር አይኖርም፡፡ ያው ወደ ፍ/ቤት ነው መሄድ የሚችሉት፡፡ ብዙዎች መነጋገሪያ አድርገውት የነበረው የ“ቅንጅት ለአንድነት ለዲሞክራሲ” ጉዳይስ? እሱም ተሰርዟል፡፡ ዝርዝር ውስጥ ያላስገባነው የፍ/ቤት ጉዳይ ስላለበት ነው፡፡ በፍ/ቤትና በአቃቢ ህግ በኩል የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ ነው ዝርዝር ውስጥ ያላካተትነው እንጂ ተሰርዟል(ቅንጅት የተጭበረበረ ፊርማ በማቅረብ መከሰሱ ይታወቃል) ማሟላት ያለባቸው ጉዳይ አለ ተብለው የተዘረዘሩት ፓርቲዎች እንዲያሟሉ የተጠየቁት ምንድን ነው? የጊዜ ገደብስ
ተሰጥቷቸዋል? እንዲያሟሉ የተነገራቸው በሁለት መልኩ ነው የሚታዩት፡፡ የተወሰኑት ማባራሪያ ነው የተጠየቁት፡፡ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብም እንደተጠየቁት የማብራሪያ አይነት ይለያያል። አምስት ቀን የጊዜ ገደብ የተሰጣቸው አሉ፤ ሰባት ቀን የተሰጣቸው አሉ፡፡ የተሰጣቸው ገደብ ይለያያል፤ አሟልተናል ብለው ሲከራከሩ እኛ ጋር ያለው ዶክመንት ሲታይ የተጓደለ ነገር በመኖሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ነው የተጠየቁት፡፡ አንዳንዶቹ ፊርማ አሟልተው አቅርበው ነበር ግን ለምሳሌ አርብቶ አደር በመሆናቸው ፈራሚዎቹ ቋሚ አድራሻ የሌላቸው ሆኖ ሌሎች የማረጋገጫ ዶክመንት እናመጣለን
ያሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ የተዋፅኦ ችግር ነው የታየባቸው፡፡ ለምሳሌ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድን) ብንመለከት፣
ሀገራዊ ፓርቲ ነን ብሎ ያመጣው ፊርማ የ5 ክልል ስብጥር አያሟላም፡፡ ስለዚህ መኢአድ የተጠየቀው ወደ ክልላዊ ፓርቲነት እንዲወርድ ነው ማለት ነው። መመዝገብ የሚፈልግ ከሆነ ፊርማው ወደ ተሟላለት ክልላዊ ፓርቲ እንዲወርድ ነው የተጠየቀው። ለምሳሌ የአገው ፓርቲ እንደዚያ እንዲያደርግ
ተጠይቆ፣ ወደ ክልላዊ ፓርቲ ወርዷል፡፡ ያመጣው ፊርማ የአማራ ክልል ፓርቲ ብቻ የሚያደርገው ስለሆነ በአማራ ክልል ፓርቲ እንዲሆን ተደርጓል። ሌሎቹ የጸደቀላቸው ግን ቦርዱ ዝቅተኛ ብሎ ያስቀመጠውን መስፈርት በተለያየ ደረጃ አሟልተው በመገኘታቸው ነው፡፡ አሟልተዋል አላሟሉም ተብሎ
የተቀመጠውን የመቶኛ ስሌት በተመለከተ ማብራሪያ ቢሰጡን? ውጤታማ ናቸው የተባሉት ከ35 በመቶ በላይ ያመጡት ናቸው፡፡ አሰራሩም
ከሀገራዊም ከክልላዊ ፓርቲ የመጡ ፊርማዎችን ናሙና ወስደን፣ ረዥም ጊዜ ፈጅተን ያጣራነው፡፡ በምናጣራበት ወቅት ያልተገኙ አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ ውጤት ያመጡት ለዚህ ነው፡፡ ፈርመዋል የተባሉ ሰዎች አሉ የተባለበት ቀበሌ ወይም አስተዳደር ድረስ ለማጣራት ተሞክሯል፡፡ አብዛኛዎቹ የሚጣጣም
መረጃ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ ቦርዱም ይሄን ለማጣራት ጊዜ ወስዷል፡፡ በማጣራቱ ወቅት ቀበሌ ላይ ወይም በሚኖሩበት አስተዳደር ላይ ፋይላቸው ያልተገኘ ሰዎች ሳይቀር ነው ፓርቲዎቹ እንዳሉ ተቆጥረው፣ አብዛኛዎቹ ከ35 በመቶ በላይ ውጤት ማምጣት የቻሉት፡፡ መኢአድ ወደ ክልላዊ ፓርቲ እንዲወርድ ሲጠየቅ ፊርማ ያሰባሰበው ከየትኛው ክልል በመሆኑ ነው?ወደ የትኛው የክልል ፓርቲነት ነው ሊለወጥ የሚችለው? ካሟሉት ክልል ሊሆን ይችላል፡፡ ያንን የሚመርጡት እነሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን ሀገራዊ ፓርቲ መሆን የሚያስችላቸውን መስፈርት አላሟሉም፡፡ ሀገራዊ ፓርቲ ነን
ብለው ነገር ግን መስፈርቱን ካላሟሉለት መካከል፡- የኦሮሚያ ብሄራዊ ፓርቲ፣የአገው ብሔራዊ ሸንጎና መኢአድ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ወደ ክልላዊ ፓርቲ ወርደው ራሳቸውን የሚያደራጁ ከሆነ፣ በአምስት ቀን ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ተነግሯቸዋል። የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ክልላዊ ፓርቲ
ለመሆን መስፈርቱን አሟልተው ካለፉት ፓርቲዎች አንዱ ሆኗል፡፡ አወዛጋቢ የሆነው “የህወሃት” ጉዳይስ? ገና በቦርዱ እየታየ ነው፡፡ በአመፅ ድርጊት፣ የሃይል እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ የሚሉትን ጉዳዮች ቦርዱ መርምሮ፣ ህጎች አገናዝቦ በህወኃት ጉዳይ የሚሰጠው ውሳኔ ይኖራል፡፡ ገና በመታየት ላይ ነው፡፡ እንደጨረስን ውሳኔውን የምናሳውቅ ይሆናል፡፡ ከተዘረዘሩት ውጪ አዲስ እየተደራጁ ያሉ ፓርቲዎች ይኖሩ ይሆን? አዎ በርካታ ናቸው፡፡ 25 ገደማ ፓርቲዎች “ክልላዊ ነን” “ሀገራዊ ነን” እያሉ እንደ አዲስ እየተደራጁ ነው፡፡ ጊዜያዊ የትብብር ፍቃድ ወስደው እየተደራጁ ያሉ አሉ፡፡ እውነቱን
ለመናገር የፓርቲዎች ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም ያለው፡፡ ቦርዱ በማጣራት ወቅት የገጠሙት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? የመስራች አባላትን ያቀረቡ ፓርቲዎች መካከል ናሙና በመውሰድ በሁሉም ክልሎች እና በሁሉም ወረዳዎች የመስራች አባላትን ማጣራት ስራ አከናውኗል። ስራው
ተከናወነው በቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አማካኝነት ሲሆን በዚህም መሰረት በሁሉም ወረዳ ላይ የቦርዱ ባለሞያዎች በግንባር በመገኘት የነዋሪነት ማረጋገጫ ለመስጠት ስልጣኑ ካላቸው የአስተዳደር አካላት ጋር በመነጋገር የመስራች አባላት እውነተኛነትና የመረጃዎችን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል። በዚህ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች፡-
 መረጃዎች በትክክል ተሟልተው አለመምጣታቸው (የማይታወቅ ወረዳ፣ ትክክለኛ ያልሆነ የወረዳ፣ ቀበሌ… ወዘተ ስም)
 ከታችኛው እርከን አስተዳደር የመረጃ አያያዝ ችግር የተነሳ ለማጣራት ረጅም ጊዜ መውሰዱ (መታወቂያ ቁጥር፣ የቤት ቁጥር……. መረጃዎች አለመሟላት)
 በፓርቲዎች በኩል የተጓደሉ መረጃዎች ሲኖሩ፣ በአጭር ጊዜ አሟልቶ ያለማቅረብ ችግርች
 በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ በቦርዱ በኩል የሰራኞች ማጣራቱን ፍጥነት ማጠናቀቅ አለመቻል….. በዚህም የ ተነሳ የ ማጣራት ሂደቱ ረጅም ጊዜ ከመውሰዱም በተጨማሪ በሂደቱ የተገኘው የማጣራት ውጤት ቦርዱ በፈለገው መንገድ ሊሆን አልቻለም። እንደ አዲስ አበባ ባሉ የአስተዳደር አካላት፣
የመስራች ፊርማን ለማጣራት ባልቻሉበት ሁኔታ ፓርቲዎች እንዳቀረቡት ትክክለኛ ፊርማ እንዲቆጠር ተደርጓል። የመስራች ፊርማ ናሙና ማረጋገጫ ከ35
በመቶ በታች በመሆኑ የተሰረዙ ፓርቲዎች ዝርዝር የሚከተለው ነው፡-
1. የአማራ ሕልውና ለኢትዮጵያ አንድነት- 24%
2. የኦሮሞ አንድነትና ዴሞክራሲ የፌደራል የሰላም ለውጥ ፓርቲ - 25%
3. የኦሮሞ አቦ ነጻነት ግንባር - 10%
4. የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር - 4%
5. የተባበሩት ኦሮሞ ነፃነት ግንባር - 33 %
6. የኦሮሞ ነፃነት ዴሞክራሲዊ ግንባር - 24% ያገኘ እና በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ባለማካሄድ
7. የኦሮሚያ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ - 14% ያገኘ እና በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ባለማካሄድ
8. የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲዊ ፓርቲ - 23%
9. ዱቤና ደገኒ ብሔረሰብ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ - 5%
10. የአገው ዴሞክራሲ ፓርቲ - የመስራች 19%
11. የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት - 18%
12. የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ 28 %
13. የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ - 18%
14. የኦሮሚያ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ - 19%
15. ኅብረት ለዲሞክራሲና ለነፃነት - 17%
16. የሱማሌ አርበኞች ፓርቲ - 17%
17. የአፋር አብዮታዊ ፓርቲ - የመስራች 9%
18. የሱማሌ ክልላዊ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት- 3%
19. ምክክር ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ - 32%
20. የወኽምረ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ - 3 3%
    ከመስራች አባላት ናሙና ትክክለኛነት ማጣራት ውጪ በሆነ መስፈርት የተሰረዙ
21. የኢትጵያ ሰላማዊ የዴሞክራሲያዊ ፓርቲ - የመስራች አባላት ብዛትና ስብጥር ባለማሟላት እና በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ባለማካሄድ
22. አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ - የመስራች አባላት ብዛትና ስብጥር ባለማሟላት እና በጠቅላላ ጉባኤ ምልአተ ጉባኤ ባለማሟላት
23. የኢትዮጵያ ኅብረ ሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ - የመስራች አባላት ብዛትና ስብጥር ባለማሟላት
24. ነፀብራቅ አማራ ድርጅት - በቅጹ ላይ በግልጽ ቢቀመጥም 2 ሺ 691 የፓርቲውን መስራች አባላት የአያት ስም አሟልቶ ባለማቅረብ
25. የፊንፊኔ ሕዝቦች አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ - የመስራች አባላት ብዛት እና ከቦርዱ በተሰጠው አስተያየት መሰረት በሰነዶች ላይ ማስተካከያ ባለማድረግ
26. ሐረሪ ሪቫይቫል ንቅናቄ - በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ባለማካሄድ በተለያዩ ምክንቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም አሟልተው እንዲቀርቡ የተወሰነ እና የማጣራት ሂደታቸው ያልተጠናቀቀ
1. ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
2. ሐረሪ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
3. አፋር ነፃ አውጭ ግንባር ፓርቲ
4. የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
5. የአፋር ሕዝብ ፓርቲ
6. የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ
7. የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት
ድርጅት (መኢአድ)
8. ጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
9. የወለኔ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
10. መላው ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ
11. የሲዳማ ብሔራዊ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ
12. ኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)
የማጣራት ሂደታቸው የተጠናቀቀ ፓርቲዎች ዝርዝር
1. የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ- 51%
2. ቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ -57%
3. የሲዳማ አርነት ንቅናቄ -78%
4. የጌዲዮ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት -93%
5. የጋምቤላ ህዝቦች ፍትህ ሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ -91%
6. የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት- 48%
7. የምዕራብ ሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ - 97%
8. የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ - 69%
9. የአገው ብሔራዊ ሸንጎ 45%
10. ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ -61%
11. የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ -94%
12. የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲ አንድነት ግንባር-49%
13. የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ- 37%
14. የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ -48%
15. ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ -48%
16. ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ -72%
17. የትግራይ ዴሞክራሲየዊ ፓርቲ -79%
18. የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ -43%
19. የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ
ለሰላምና ለዴሞክራሲ ድርጅት -48%
20. የአፋር ህዝቦች ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ
 ፓርቲ -53%
21. አዲስ ትውልድ ፓርቲ -64%
22. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ -38%
23. የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ -99%
24. የቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ -100 %
25. የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ -38 %
26. የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ -96%
27. ብልጽግና ፓርቲ -78%
28. የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ -39%
29. የኦሮሞ ነጻነት ግንባር -47%
30. የሲዳማ ሃድቾ ህዝብ ዴሞክራሲዊ ድርጅት -71%
31. የአማራ ዴሞክራሲዊ ሃይል ንቅናቄ -45%
32. የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ -93%
33. እናት ፓርቲ -47%
34. ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ -64%
35. ቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (በአዲሱ አዋጅ ቀድሞ የተመዘገበ)
36. ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ ሉአላዊነት (ከማጣራቱ ቀድመው የፊርማ መስፈርት ያጠናቀቁ)
37. የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አነስተኛ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ፓርቲ)
38. የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አነስተኛ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ፓርቲ)
39. የዶንጋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አነስተኛ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ፓርቲ)
40. የፌደራላዊ ዴሞክራሲዊ መድረክ (ግንባር በመሆኑ ፊርማ ማቅረብ የማገባው) የማጣራት ሂደታቸው የተጠናቀቀ ነገር ግን
የቴክኒክ መስፈርቶች የቀሯቸው ፓርቲዎች
1. ህዳሴ ፓርቲ
2. ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ
3. የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት
4. የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
5. የሲዳማ አንድት ፓርቲ
6. አሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
7. ብሔራዊ ባቶ ዓባይ ትግራይ
ቦርዱ የወሰነ መሆኑን ለዜጎች፣ ለሚዲያ ማህበረሰብ አባላት

Read 5052 times