Saturday, 02 January 2021 10:17

በሱዳንና በኢትዮጵያ መካክል ላለው ውጥረት እርቀ ሰላምን እንደሚያስቀድም መንግስት አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የሱዳን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው ጥቃት መፈፀማቸውን ያረጋገጠው መንግስት፤ ችግሩን በእርቀ ሰላምና በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የሱዳን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት ገበሬዎች ላይ ጥቃት ፈፅመው፣ ሃብት ንብረት መዝረፋቸውን የጠቆመው የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በቅድሚያ ሰላማዊ የግጭት መፍቻዎችን ብቻ ተጠቅማ ችግሩን ለመፍታት ትሰራለች ብሏል፡፡
በቅርቡ ም/ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ወደ ሱዳን ባቀኑበት ወቅትም የተፈጠረው ውጥረት በሚረግብበትና ሰላማዊ አማራጮች በሚቀድሙበት ጉዳይ  ላይ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ አስታውቀዋል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣናት በበኩላቸው፤ “የቀድሞ መሬታችንን አስመልሰናል፤ አሁን ድንበር ማካለል አለብን” የሚል አቋም መያዛቸውን ታዋቂው የሱዳን ጋዜጣ ትሪቡን ጨምሮ በርካቶች የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ያመለከቱ ሲሆን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከሱዳን ባለ ስልጣናት በኩል በአፋጣኝ የድንበር ማካለል ስራ እንዲሰራ ጥያቄ መቅረቡን አመልክቷል፡፡
በቀድሚያ የድንበር ማካለል ጉዳይ እንዲጠናቀቅና ቀጥሎም በሱዳን ግዛት ላይ ያሉ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን ጉዳይ ጨምሮ ማንኛውንም ነገር መወያየት እንችላለን የሚል ሃሳብ መወያያት እንችላለን የሚል ሃሳብ የሱዳን መንግስት እያራመደ መሆኑን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ያመለከተው፡፡
 ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ የሱዳን ወታደራዊ ሃይሎች ከባድ መሳሪያ በመጠቀም የተደራጀ ጥቃቶችን መፈፀማቸውን በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን  በዚህም የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶች መዘረፋቸውን፣ ካምፖች መውደማቸውንና እንዲሁም የእርሻ ምርት እንዳይሰበሰብ እንቅፋት መሆኑን መንግስት አስታውቋል፡፡
በሱዳን በኩል የሚደረገው ውጥረት አባባሽ ሁኔታ እንዲቀየርና ችግሩ በእርቀ ሰላምና ውይይት እንዲፈታየኢትዮጵያ መንግስት አቋም መያዙን ያስታወቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሱዳን የጦር ሃይልም ከጠብ ጫሪ ድርጊቶች እንዲቆጠብ አሳስቧል፡፡
ከዚሁ የሱዳን ወረራ ጋር በተያያዙ የሱዳን ጦር ምክትል ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀነራል ካሊድ አብዲን አል ሻሚ፤ “ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሚሊሻ ከተቀማነው 80 በመቶ ያህል ግዛታችንን አስመልሰናል” ሲሉ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡  


Read 12020 times