Saturday, 02 January 2021 10:26

የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት የ123 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን አረጋግጫለሁ - ኢሠመኮ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    አፋጣኝ የግፍና የጭካኔ ወንጀል መከላከል ስትራቴጂ እንዲነድፍ ተጠይቋል
                    
           የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ስለተፈጸሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ያከናወነውን ምርመራ ትናንት ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ ለ3 ቀናት በቆየው የፀጥታ መደፍረስ የ123 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 500 በሚሆኑት ላይ ደግሞ የአካ ል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ለወራት ሲያካሂድ የቆየውን ምርመራ በ64 ገጾች ሰንዶ ያቀረበ ሲሆን መንግስት  አጥፊዎችን በሚፈለገው ልክ ወደ ህግ አላቀረበም፤ ድርጊቱን የሚመጥን የህግ እርምጃዎችም አልተወሰደም ብሏል።
አርቲስት ሃጫሉ ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በድንገት መገደሉን ተከትሎ፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ለ3 ተከታታይ ቀናት ባጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ በሰዎች ላይ ጉዳት ከመድረሱ በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፣ በንግድ ድርጅቶችና የመንግስት ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ተፈጽሟል ብሏል።
በ40 የተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተከሰቱ የፀጥታ መደፍረስ 76 በሁከቱ የተሳተፉ ግለሰቦች የፀጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ መገደላቸውን፣ 35ቱ ደግሞ በሁከቱ ተሳታፊ ግለሰቦች እጅ መገደላቸውን ነው ሪፖርቱ ያመለከተው።  12 ያህል ግለሰቦች ደግሞ በፀጥታ መደፍረሱ ወቅት በተከሰተ ፍንዳታ፣ ቃጠሎና መሰል አደጋዎች ህይወታቸው ማለፉን መሞታቸውን ነው ሪፖርቱ ያመለከተው።
በጥፋቱ የተሳተፉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች  ከቦታ ቦታ በቡድን እየተንቀሳቀሱ በጩቤ ፣ ድንጋይ ፣ እሳት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ፣ በዶማ፣ በገጀራና መጥረቢያ ፍፁሞ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ጥቃቱን መፈጸማቸው ተገልጿል።
ጥቃቱ ያነጣጠረው በከፊል በብሄርና በሃይማኖታቸው የተመረጡ ሰዎች ከየቤታቸው ለይቶ በማሳደድና በማጥቃት፣ በከፊል ብሄርና ሃይማኖት  ሳይለይ  ሰላማዊ  ነዋሪዎችን ወይም ሲቪል ሰዎችን ሆነ ብሎ በማጥቃት የተፈፀመ የወንጀል ድርጊት መሆኑን እንዲሁም በወቅቱ በማህበራዊ ሚዲያና በተወሰኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይተላለፉ የነበሩ መልእክቶችና በመወንጀል ድርጊቱ ይሳተፉ የነበሩ ሰዎችና ቡድኖች ያሰሟቸው ከነበሩ መፈክሮች አንፃር ድርጊቱና ውጤቱ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ (Crime against humanity) የግፍና ጭካኔ ወንጀል መሆኑን የሚያሳይ ነው -ብሏል ኮሚሽኑ።
ድርጊቱ ሲፈፀም በአካባቢው የነበሩ የፀጥታ ሃይሎች ትእዛዝ አልደረሰንም በሚል ድርጊቱን በጊዜ ለመከላከል ዳተኝነት ማሳየታቸውን በሪፖርቱ የጠቆመው ኢሰመኮ፤ በዚህም የጉዳቱ መጠን ሊጨምር ችሏል ብሏል። መንግስት ግልፅ በሆነ መንገድ በሁከቱ የተሳተፉ አካላትን በሙሉ ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ የተጎዱትን መልሶ እንዲያቋቁም የጠየቀው ኢሰመኮ፤ መሰል የግፍና ጭካኔ ተግባራት እንዳይደገሙ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተሟላ የግፍና የጭካኔ ወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ነድፎ በአፋጣኝ በስራ ላይ እንዲያውል አሳስቧል።

Read 11552 times