Print this page
Saturday, 02 January 2021 10:24

በዘንድሮ ጥምቀት ጐንደር ከግማሽ ሚ. በላይ ቱሪስቶችን ትጠብቃለች

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 ኮቪድ 19 እና የፀጥታ ሁኔታ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎባቸዋል
                  
             በዘንድሮ የጥምቀት በዓል በጎንደር  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የከተማዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘው ተናገሩ፡፡
በዓሉ ኮቪድ-19 በተሰራጨበት ወቅት እንደመከበሩና መንግስት ህግን ለማስከበር እየወሰደው ባለው እርምጃ ምክንያት፣ የፀጥታውና የጤናው ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነ አቶ ቻላቸው አስረድተዋል፡፡
የጥምቀት በዓል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር ባወጡት የበዓል አከባበር ፕሮቶኮል መሰረት የሚከናወን ሲሆን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እየተከላከሉ በዓሉን በጥንቃቄ ለማክበር ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር  በቅንጅት እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ለበዓል አከባበሩ አንድ አብይ ኮሚቴና 8  ንዑሳን ኮሚቴዎች የተዋቀሩ ሲሆን፣ ኮሚቴዎቹ ከቤተ-ክህነት፣ከጤናው፣ከባህልና ቱሪዝም፣ ከፀጥታ አካላትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ነውም ተብሏል፡፡
ሀላፊው የፀጥታውን ጉዳይ በተመለከተ ሲያበራሩ፤ ጎንደር በህወሃት የጥፋት ሀይል ትኩረት የተደረገባት ከተማ የነበረች ቢሆንም ባለው ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር ጉዳት ሳይደርስ መከላከል መቻሉንና በተላላኪነት እዚሁ ከተማ ሆነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን በቁጥጥር ስር በማዋል መቻሉን ተናግረዋል።
ለጥምቀት ህዝቡ ከተለያየ የአገሪቱ ክፍል በመምጣት በሰላም አክብሮ እንዲመለስ፣ ለፀጥታና ደህንነት ሁኔታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ በመሆኑ ምንም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
የኮቪድን ጉዳይ በተመለከተም በከተማ አስተዳደሩና በባለ ድርሻ አካላት ድጋፍ የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘርና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በተለይ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ግቢ እንዲገቡ ለተፈቀደላቸው መዘጋጀቱንና ጠንካራ ወጣት አስተባባሪዎችን በመመደብ በዓሉን በሥርዓትና ያለ ስጋት ማክበር እንዲቻል ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ቻላቸው ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ በኮሮና ምክንያት የውጭ ቱሪስቶች ብዙ ባይጠበቁም፣ ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ከ500 እስከ 600 ሺ ታዳሚ እንደሚመጣ ታሳቢ በማድረግ ለእንግዶቹ የሚመጥን ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ በመሆኑ ሁሉም ጎንደር ላይ መጥቶ ደማቁን የጥምቀት በዓል በሰላምና በደስታ እንዲያከብረው ጥሪ አቅርበዋል አቶ ቻላቸው ዳኘው፡፡  


Read 11905 times