Print this page
Saturday, 02 January 2021 10:38

ባልደራስ ጥር ዘጠኝ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ አቅዷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ)፤ ዘር ተኮር ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ፣መሪዎች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በመጪው እሁድ ጥር 9 ቀን   ለማካሄድ ማቀዱን አስታውቋል፡
የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ስለሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ለአዲስ አድማስ ሲያስረዱ ሰላማዊ ሰልፉ አራት ዋነኛ ግቦች አሉት ብለዋል፡፡
ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈፀሙ የቆዩ ዘር ተኮር ግድያዎች ማፈናቀሎችን ኢ-ሰብአዊ ደርጊቶችን የማውገዝ ፣ሱዳን ድንበር ጥሳ መግባቷን የሚቃወምና መንግስት የሃገሪቱን ሉአላዊነት እንዲያስከብር የሚጠይቅ አዲስ አበባ ላይ የኦሮሚያ ክልል የሚያከናውናቸውን የተለያዩ የህንፃ ግንባታዎች መቃወም እንዲሁም፣ የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች በአፋጣኝ ከእስር ተለቀው በምርጫው እንዲወዳደሩ የመጠየቅ አላማ ያለው ሰልፍ መሆኑን ዶ/ር በቃሉ ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል በኦሮሚያ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብ ኮንሶ የዘር ማጥፋት መልክ ያላቸው ግድያዎችና ማፈናቀሎች ሲፈፀሙ መቆየታቸው ያስታወሱት ዶ/ር በቃሉ፤ ይህ መሰሉ ድርጊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ በሰላማዊ ሰልፍ ይጠይቃል ድርጊቱንም ሁሉም ዜጎች እንዲያወግዙት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን ጥር 9 ለማካሄድ ያቀደው ባልደራስ፤ ሰልፉ ከሚካሄድበት፤ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ህጉ በሚያዘው መሰረት ለአዲስ አበባ አስተዳደር ያሳውቃል ብለዋል -ዶ/ር በቃሉ
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባልደራስና መኢአድ በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ በደቡብ ኮንሶ፣ በቤኒሻንጉል መተከል ከሰሞኑ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀሙ ጭፍጨፋዎችን አውግዘው፤ መንግስት ህግ የማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የተፈፀሙ ግድያዎችና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችም በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ እንዲሁም ተጎጂዎች በአፋጣኝ እንዲቋቋሙና ካሳ እንዲከፈላቸው ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡  


Read 12213 times