Saturday, 02 January 2021 10:59

“የንጉስ እራት” መርሃ ግብር 1ቢ. ብር ይጠበቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

     በጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በሚመራው “ገበታ ለሀገር” መርሃ ግብር ፕሮጀክት ውስጥ ከተካተቱት አንዷ ለሆነችው ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ጎርጎራ ልማት የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ “የንጉስ እራት” የተሰኘ መርሃ ግብር በጎንደር ከተማ ይካሄዳል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት በዚህ መርሃ ግብር 1 ቢ.ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የክልሉ ባለሃብቶች፣ ዲያስፖራዎችና በዚህ ልማት ላይ አሻራዬን ማሳረፍ አለብኝ የሚል ሁሉ እንደሚታደምበት ተናግረዋል።
ከጥምቀት በዓል በኋላ ባሉት ቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በአንዱ ቀን የሚካሄደው “የንጉስ እራት” መርሃ ግብር፣ ብዙ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን በውስጧ ሸጉጣ ወደ ኋላ የቀረችውን ጎርጎራን በእጅጉ ይለውጣል ለተባለው ፕሮጀክት ይውላል ተብሏል።
“የጎርጎራ መልማት የጎንደር መልማት ነው፤ በዚህ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ጎርጎራ ስትለማ ከስራ ዕድል ፈጠራ ጀምሮ በርካታ እድሎችን ለጎንደር ከተማም ይዞ እንደሚመጣ በማመን የእራት ፕሮግራሙ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በተያያዘ ዜና፤ ከዚህ ቀደም ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ገንዘብ ለመስጠት ቃል የገቡ የንግድ ተቋማት ሰሞኑን ገንዘቡን ገቢ ያደረጉ ሲሆን ተቋማቱም ሚድሮክ ኢትዮጵያ 40.ሚ ብር፣ አዳማ ቆርቆሮና ምስማር ፋብሪካ 10ሚ.ብር፣ ላየንስ ግሩፕ 5.ሚ ብር፣ በላይነህ ክንዴ 10ሚ.ብር፣ የኦሮሚያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን 5.ሚ ብር፣ የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን 10 ሚ. ብር ኬርቻንሺ  ትሬዲንግ 10 ሚ.ብር፣ ባለዛፍ አልኮል 5.ሚ.ብር፣ ኢትዮ ጋባና ትሬዲንግ 5.ሚ፣ ጭላሎ ምግብ ማምረቻ ኮምፕሌክስ 5.ሚ.ብር ገቢ ማድረጋቸው ታውቋል።

Read 12437 times