Print this page
Saturday, 02 January 2021 10:48

ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ከእለታት አንድ ቀን የሀገራችን ገጣሚ  እንዲህ ብሎ ገጥሞ ነበር።
ሚሚዬንም ጠየኳት፡-
ሁልጊዜ አረንጓዴ ለምለም ፍቅር አለ  
ትወጃለሽ ሚሚ ይህን የመሰለ?
ወይስ ያዝ ለቀቅ
ጭልጥ አንዴ መጥቶ
አፍ ጠራርጎ መሄድ ያገኙትን በልቶ
ሚሚዬ እንዲህ አለች፡-
ሳስቃ መለሰች
“የምን እኝኝ ነው እድሜ ልክ ከአንድ
ቋሚ ፍቅር  ይቅር ለብ ለብ እናርገው
ፍቅሯ ለብ ለብ
ትምህርቷ ለብ ለብ
እውቀቷ ለብ ለብ
ነገር ዓለሟ ግልብ
እንዴት ይበስል ይሆን እሳት ያልገባው ልብ?
*   *   *
ሁሉንም ነገር ለብ ለብ አድርገን አንችለውም፤ ጠለቅና ጠበቅ ማለት አለብን። ቢያንስ ታሪክና ባህል ያለን ህዝቦች ነን። ማንም ወራሪ ይወረን ዘንድ እድል የለውም።  ድህነት የኛው ነው። ጠላት ድህነትን ወሮ ምን ያገኛል።
ከሰሞኑ ተስፋዬ ገሰሰን ያህል ታላቅ ሰው አጥተናል። በኛ ስሜት ባንዲራችን ዝቅ ብሎ ብንሸኘው በወደድን፤ የሀገር ባንዲራ ነውና! ስለምናውቃቸው ሰዎች ልብ ለልብ እንወያይ፣ ልብ ለልብ እንተያይ፣ ልብ ለልብ እንተዋወቅ፡፡ መጀመሪያ ግን እንወቅ፡፡ ለፍቅርና ለእውቀት ቅድሚያ ያልሰጠ፣. ህይወትን ማሸነፊያውን መንገድ አያውቅም።
ደራሲ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ በአፄ ምንይልክ መጽሐፋቸው፤ አንድ ጎራዴ ያሟቀለና የመሸበት ደበንአንሳ ያሟቀለ እከካም ወታደር፣ በባላገሩ ልጅ ተሰሪ ገብቶ፣ የዚያን ባላገር ውብ ልጅ አየ። ከዚያም #ይህቺ እህትህ ስንት አመቷ ነው?# ሲል ጠየቀው፡፡ ባላገሩም እድሜዋን ተናገረ። ያም ቅማላም ወታደር ሚስቱን ይዞበት አደረ። ባላገሩም ፡-
“በሀገር እኖር ብዬ”
ልጅ አሳድግ ብዬ
ከብት እነዳ ብዬ
ከሰው እኖር ብዬ
ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴን ብዬ -- አለ ይባላል።
ይህ አይነቱ ሁኔታ ዛሬ ባለመኖሩ ፈጣሪን ማመስገን ይገባናል።  በጥንቱ መግለጫ፤ በጫጫታ የፈረሰች ሀገር ብትኖር  የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢያሪኮ ብቻ ናት ተብሎ ነበር። አብዮታዊ ኢትዮጵያ እንጂ የምትፈርስ ኢያሪኮ የለንም። ተብሎም ነበር።
እኛ ደግሞ #በጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ልብላው ልብላው ነው። ከአህያ ቆዳ የተሰራ ግድግዳ  ጅብ የጮኸ እለት ይፈርሳል; ብለናል። በሃይል አንመን፤ እያንዳንዱ ጠመንጃ ያዥ ተረኛ ነብሰ ገዳይ መሆኑን አንርሳ፤ የሚያኖረን ፍቅርና አንድነት እንጂ ፀብ አይደለም።
የመንገዶች መብዛት ጥሩ እግረኛን አያመጣም። ወሳኙ ሰው ላይ መስራት ነው። ለዚህ ደግሞ መልካምና ደግ መንግስት ያሻናል። መልካምና ደግ መንግስት ደግሞ የታታሪና ለመብቱ የሚታገል ህዝብ ውጤት ነው። ሲዛነፍ የሚያቃናው፣ ሲቃና የሚያጠናክረው ሕዝብ ያስፈልገዋል። ተቆጣጣሪ የሌለው መንግስት ነጻ የሆነ መንግስት ብቻ ሳይሆን፣ ማን አለብኝ የሚል መንግስት ሊሆን ስለሚችል ወደ አምባገነንነት ሊያደላ ይችላል።
ስለዚህም ልጆቻችንን አስተምረንና አጠንክረን መንግስትን የሚቆጣጠሩ ኃይሎች ማድረግ አለብን። እንዲህ ያሉ ልጆች ያሏት ሀገር፣ የታደለችና የታጠረች የማትደፈር ሀገር ትሆናለች።

Read 13494 times
Administrator

Latest from Administrator