Saturday, 02 January 2021 11:11

ሞት ቅጣት ነው እንዴ?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  መደመጥ እንጂ ማዳመጥ ግብሬ አይደለም ብሎ በእብሪት የሚፏልል ከሃዲ፤ የጥፋት ሜዳውን ጨርሶ ገደል ሲገባ ማየት የጥጋብን መጨረሻ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ ጥጋብ ልብ ሲነሳ፣ ጆሮ ለልቦና ዕውነት ማቀበሉን እየተወ፣ ከሃዲዎችን ዳፍንታም እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል። በክህደት የሰከረ አዕምሮ መዘዝ በሚያስከትል ዝባዝንኬ ነገር እየተወጠረ የጥፋት ክንድ ሲበረታ፣ ፈጥኖ የሚመጣው ውድቀት መሆኑንም ዓለም እልፍ አዕላፍ ጊዜ ተመልክቷል፡፡
ውድቀት በውርደት ሲታጀብና ክህደት ሲታከልበት ደግሞ ቅሌት በአደባባይ ገሀድ ይወጣል። የዚህን ዕውነትነት ለማረጋገጥ ከትህነግ ጁንታ ወዲያ ማመሳከሪያ መፈለግ አያሻም።
ጁንታው ገና ከፍጥረቱ የተንጋደደ በመሆኑ ከአጋንንት መንገድ በጊዜ መውጣት ተስኖት በጥፋት ሲባዝን የኖረበት የሴራ ዕድሜ አብቅቶ እንጦሮጦስ ቢወርድም፣ ክህደቱን ይቅር የሚል ሰውና ሰውነት አይኖርም፡፡ በሴራና በዝርፊያ የጠበደለ ጁንታ፣ ከአገር ትከሻ ላይ ሲወርድ፣ አንገት ቀና እያለ የእፎይታ ትንፋሽ ሠማይ ምድሩን ቢያወድም፣ በየማዕዘኑ ያፈሰሰው የንፁሃን ደም ቦይ እየሠራና ለግፍ ማስረጃ የሚሆን ደለል እየተወ የወረደበት ጥፋት የታሪክ ጉድፍ እንደሆነ ይኖራል፡፡ የዘረፈውን ሀብት ዓይነትና መጠን ለማስላት ቁጥር ከትሪሊዮን የዘለለና ለሁሉም ተግባቦት የማይመች አቅም ባይኖረውም ቅሉ አግበስባሽነቱ ሊደበቅ አይችልም፡፡
ታሪክ የከሃዲውን የዘመናት ሴራ በቅጡ ለማንበብ ጊዜ ቢወስድበትም፣ በሚዛኑ በሚያስቀምጠው ጊዜ፣ ዓለምን ጉድ የሚያሰኝ መሠሪ ድርጊቱ እየተጎለጎለ ገና ይወጣል፡፡
አገርና ህዝብ ጠል በሆነ እሳቤውና ድርጊቱ አገር የመራበት አበቅቴም፣ የመጀመሪያው የምድር ጉድ ሊያደርገው እንደሚችል ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ የክህደቱ ዓይነትና መጠን ለምድር መምረሩ ደግሞ ከምንም የባሰ ሆኗል፡፡ ህዝብን እየፈጀና እያስፈጀ፣ ታሪክን እያደበዘዘና እየፋቀ፣ አገር ማፍረስን ግብ አድርጎ ቀንና ሌሊት የሚያሴር ብልሹ ቡድን፣ አገር እመምራት መንበር ላይ ያን ያህል ጊዜ ተጎልቶ መቆየቱ ጉድ ካላሰኘ፣ ጉድ የሚያሰኝ ነገር የለም ወደሚል ይወስዳል፡፡
ባገሩ ሠማይ ሥር በወገኑ መሃል የድካም ውሎውን በእንቅልፍ ተሻግሮ የአገር ጋሻነት ክቡር ሥራውን ማለዳ ሊቀጥል የነበረን ጀግና፣ ነግቶለት ለአዲስ ቀን ሳይበቃ ለአሞራ መዳረግ ከክህደትም በላይ የሆነ አረመኔያዊ ድርጊት ነው፡፡ ከዚሁ የተነሳ ኢትዮጵያውያን እናቶች ውስጣቸው በሃዘን እየተገመሰ ሳግ ይተናነቃቸዋል እንጂ የክህደቱን ክፋት እንዲህ ነው ብለው የሚገልጹበት ቃል አላገኙለትም፡፡
ታሪክ በረጅም ጉዞው ውስጥ ለሰው ልጅ ያላሳየው ክህደት ሲከሰት ቋንቋ የመግለፅ አቅም ቢያጥረው አይገርምም፡፡ ቋንቋ እሾትንና ድርጊትን መግለጫ መማሪያ እስከሆነ ድረስ ከዚህ ቀደም እንኳንስ ሊደረግ ሊታሰብ የማይችል ሰይጣናዊ ክህደት ሲፈጸም፣ የመግለፅ አቅመቢስ ሆነ ማለት አገር የተካደችበትንና የተመታችበትን በትር ልክ አለመረዳት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ ልጆች የአጋንንት ባለሟል ሆነው፣ ክንዷ እንዲዝልና አጥሯ እንዲፈርስ ያደርጋሉ፣ ፃዕዳ ታሪኳ ጥላሸት እየተደፋበት ጥቀርሻ ይለብሳል፣ ክህደት ባሰከረው አራሙቻ ዳዋ የመልበስ አደጋ ይደቀንባታል ተብሎ አይታሰብም ነበር፡፡
ይሁንና አገርና ህዝብ ጠል ከሆነና በሴራ ከተሸበበ ድፍርስ አዕምሮ ሰው-ጠቀም ውጤት መጠበቅ ዘበት ነበር፡፡ የትህነግ ጁንታም  የዚሁ ልክፍተኛ ሆኖ ዕድሜ ልኩን ናውዟል፡፡ ሠላም እርሙ ስለሆነ ቃሉን መስማት አይሻም ነበር። የሞትና የውድመት ዜና የዙሪያ ገባውን አየር ካላሞቀው ህመም የሚበረታበት በሽተኛ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጁንታው ለሠላም የቆሙ ትላልቆች ጫማው ሥር ወድቀው ሲለምኑት ትናንሽ የመሰሉት። “ሠላም ከሌለበት እየመጣችሁ ሠላሜን አትንሱኝ” እያሉ ልክ በሌለው መታበይ የተኮፈሰውም ክህደትን በመተማመን ነበር፡፡ አዎ! ጁንታውማ አገራችንን አፍርሶ፣ አገራቸውን ወዳላፈረሱ የመሰደድ ዘግናኝ ውርደት ደግሶልን ነበር፡፡ ሆኖም እብሪት ወደ ትቢያነት ሲቀየር የነገሮች ፍጥነት አስገራሚ ሆኗል፡፡
ሌላው ደግሞ ሞት ለነዚህ እኩያን ተመጣጣኝ ቅጣት ይሆናል ብሎ ማመን ፍርደ ገምድልነት መሆኑ ነው፡፡ ዕድሜ ልካቸውን ሴራና ክህደት ያነወዛቸው፣ ሃሣባቸው ያረጠና ውሏቸው የጀዘበ አጁዛዎች፣ በሞት ቢቀጡ ምንም  እንዳልሆኑ  ይቆጠራል እንጂ ብይን ነው ሊባል አይችልም፡፡
የምር እንነጋገር ከተባለ፣ ሁሉም የሚሞተውን ሞት፣ አገር ለገደሉ ከሃዲዎች ቅጣት ነው ቢባል ፌዝ ይሆናል፡፡ የላይ ቤቱን የሲኦል ቅጣት ታሳቢ በማድረግ ከሆነ፣ ምድር ላይ ላጠፉትና ምድርን ላጠፋት ቅጣት የሚሆን ብይን ነው የአገር እሾት፡፡
ለማንኛውም እንደ ጁንታው ክህደት፤ ግፍ የተስተናገደባት ምድር፣ እሳተ ገሞራ አለመትፋቷና የህዝብ ቁጣ ረመጥ ሆኖ ጁንታውን በማቃጠል ብቻ ማብቃቱ፣ ትዕግሥት የተወራረሰበት አገር መሆኑን ያሳያል፡፡

Read 3034 times