Print this page
Monday, 04 January 2021 00:00

የወቅቱ የአሸናፊነት ጥያቄ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  ጊዜን እንዴት ነው የምንረዳው? በሚል ጥያቄ እንጀምር፡፡ ይህን ጽሑፍ ማንበብ ከተነሳንበት ጊዜ አንስቶ እንኳን ስናሰላ ሰኮንዶች ወደ ደቂቃ፣ደቂቃዎች ወደ ሰዓት እያደጉ ናቸው፡፡ ደጋግመን እንደምንናገረው ሁሉ ንባባችንን እንደገና ለመጀመር ብንፈልግና መጀመር ብንችልም፣ የምንጀምርበት ጊዜ የቅድሙ ሳይሆን የሚጠብቀን ተለውጦ ነው፡፡ ቀደም ሲል 4፡00 ሰዓት ላይ ጀምረን ቢሆን፣ ሥንመለስ የምናገኘው ጊዜ 4፡10 (አራት ሰዓት ከአስር ደቂቃ) ሊሆን ይችላል፡፡
ሰኔ 20 ቀን 1983 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ፣ በሕወሐት ኢሕአዴግ መሪነት፣ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ስብሰባ እየተካሄደ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የደርግን መንግሥት መሣሪያ አንስተው ይፋለሙ ከነበሩት ውስጥ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኅብረት (ኢዲዩ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦኤንኤልኤፍ) እና ሌሎችም እንዲሳተፉ ተደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ድርሽ እንዳይል ተከለከለ። በአንጻሩ ሕወሐት ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የተመሠረቱና በአውሮፓና በአሜሪካ የነበሩ፣ በጦር ሜዳ ያልታዩ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል። የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህራንና የኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን (ስሙን ከሳትሁ ይቅርታ) በድምፅ እንዲሳተፉ ወንበር ተሰጥቷቸዋል፡፡ በወቅቱ ኤርትራን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው አሥመራ ላይ አስተዳደራቸውን የመሠረቱት የሻቢያው መሪ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂም ተገኝተው ነበር፡፡ ከጉባኤው ተሳታፊዎች አንዱ፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ አገር መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሻቢያ ከሽግግሩ መንግሥት መስራች ኃይሎች አንዱ መሪ መሆን እንዳለበት በመግለፅ ሀሳብ አቀረቡ፡፡ በመሣሪያ ትግል ያገኙትን ስልጣን ማስረከብ  ያልፈለጉትና የሽግግር መንግሥት ምስረታ አካል መሆንን ያልወደዱት አቶ ኢሳያስ፤ “የኤርትራና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነትን ማጥናት ለዩኒቨርስቲ ምሁራን ተውላቸው” በማለት ነበር የቀረበውን ሃሳብ በጥዋት ከገበያ ያስወጡት፡፡
“ይህን ያለፈ ጉዳይ ለተመራማሪዎቹ ተውት” የሚለው የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ (ፕሬዝዳንት) ንግግር ወይም ምክር፤ አሁን ላሉት የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ተደጋግሞ ሊነገራቸው ይገባል፡፡ አቶ ኢሳያስ ተውት ሲሉ ታሪክ ምንም ዋጋ የለውም  ማለታቸው ሳይሆን፤ ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ሊለውጠው አይችልም ማለታቸው እንደሆነም ማስገንዘብ ይገባል፡፡
በሀገራችን የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችን ምሥረታ በሁለት ዘመን ላይ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያዎቹ በንጉሡ መንግሥት መውደቂያ፣ በደርግ መንግሥት መቋቋሚያና የሥልጣን ማደላደያ  ዘመን ላይ የተመሠረቱት ናቸው፡፡ እነዚህም ተበድሏል ተገፍቷል የሚሉት ሕዝብ፤ ፍትሕና ርትእ የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ተነጥሎ የራሱን ነፃ አገር ሲመሠርት ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ሁለተኛዎቹ በዘመነ ሕወሐት ኢህዴግ የተመሰረቱ ሲሆኑ እንደ መጀመሪያዎቹ በቀጥታ የመገንጠል ጥያቄ ባያነሱም፣ የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 39ን እንደ ጋሻ የሚጠቀሙ እንዲሁም ዜጎቿን በእኩልነት የምታስተዳድር ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚታገሉት የኅበረ ብሔራዊ ደርጅቶቸ ምስረታ በዚህ ዘመን ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡
የዶክተር ዐቢይ መንግሥት ከመጣ ወዲህ እንኳ ሁኔታዎች ተለውጠዋል፡፡ ዛሬ ሕወሐት በክልሉ መንግሥት የሥልጣን ወንበር ላይ የለም፡፡ በቄለም ወለጋና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው “ኦነግ ሸኔ”፤ የሕዝብን ሰላም እያወከ፣ ሰዎችን በወጡበት እያስቀረና ንብረት እያወደመ ይገኛል፡፡ በቤኒሻንጉል በተለይም በመተከል የጉምዝ ታጣቂዎች ናቸው የሚባሉ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን እየገደሉ ናቸው፡፡ ይህ መታወክ አልበቃ ያለ ይመስል በተጎራባቾቹ አፋርና ሱማሌ መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና በረጅም ጊዜም የግድቡ አስተዳደር አልፎም ኢትዮጵያ በእለት የውኃ ሀብቷ የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብቷ ላይ፣አሳሪና አስገዳጅ ውል ለማስገባት የፈለገችው ግብፅ፤ ሱዳንን ፊታውራሪ አድርጋ በማሰለፍ፣ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቶ “ከተወሰደብን መሬት ሰማኒያ በመቶውን መመለስ ችለናል” በማለት ጦሩ መግለጫ እየሰጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ያቀረበችውንም ጥያቄ ወደ ጎን እየገፋ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትን በየአቅጣጫው በመወጠር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚፈልጉ ወገኖች ቀኑ እንደደረሰ እየታያቸው መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ እኔ ኢትዮጵያ  እንድትፈርስ የምፈልግ ሰው አይደለሁም። የፈለገውን ጊዜ ያህል ወስዳ የውስጥ ችግሯን መፍታት እንዳለባት አምናለሁ። የማንም የበላይነት፤ የማንም የበታችነት የማይታይባት ኢትዮጵያን መፍጠር የሁሉም ምኞት እንደሆነም እረዳለሁ፡፡
ይህ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ህልውናና አንድነት መጠበቅ አለበት፡፡ የዚህ ተግባር ሸከም በዋናነት በመንግሥት ትከሻ ላይ ቢወድቅም፣ መንግሥት ተሸክሞ መንገዳገድና መውደቅ- የለበትም፡፡ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎችም ጉዳዩን የመንግሥት ብቻ አድርገው መመልከት የለባቸውም፡፡ አገርን ከአደጋ  ለማዳንና ለመታደግ  ሁሉም የአቅሙን እንዲያበረክት መንገዱ ሁሉ ክፍት መሆን አለበት፡፡
መንግስትም ሆነ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሃይሎች በተለወጠ ዘመን ላይ እንዳሉ መገንዘብ አለባቸው፡፡ ትናንት የሚከተሉት መስመር ዛሬ መጥፊያ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ፕሮግራም ለመለወጥ ባያስገድዳቸው እንኳ የስትራቴጂ ለውጥ ማድረግ ግድ እንደሚሆንባቸው ሊያምኑ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ወቅት በአሸናፊነት እንድትሻገር ማድረግ የሚችል አሰራር፣ ለዚህ የሚተባበር የፖለቲካ ኃይልና ሕዝብ ያስፈልጋታል፡፡ ሕዝብ ደግሞ ድርሻውን በአግባቡ መወጣት የሚችለው የሚያምነው የሚቀበለው አመራር ሲኖረው መሆኑን ማወቅ ግድ ነው፡፡Read 1851 times