Friday, 01 January 2021 00:00

"የብሔር ልዩነታችን ላይ መሰረት ባደረገ ፖለቲካዊ የአስተዳደር ስርዓት የዜጎችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ማረጋገጥ አይቻልም"

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በሀገራችን ኢትዮጵያ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለ አሰቃቂ ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ ለዘመናት ከኖሩበት ስፍራ መፈናቀል እንዲሁም ያፈሩትን ሃብትና ጥሪት በአንድ ጀንበር አጥተው ለተረጅነት መዳረግ በየጊዜው የሚያጋጥም የተለመደ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡ ይህንን በዜጎች እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ መፈናቀልና ሃብትና ንብረታቸውን ማጣት እንዲቆም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ደግመው ደጋግመው ቢያወግዙም በተቃራኒው ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ዕምነት፤ ባህል፣ ስነልቦና፣ ጋብቻ፤ ስራ፤ ጉርብትና ሌሎችም መስተጋብሮች ላንለያይ አስተሳስረውን ጠንካራ የአብሮነት ባህል የነበረን ህዝቦች ነን፡፡ ይህ የአብሮነት መስተጋብር በብዙ አጋጣሚዎች ፈተና ላይ የወደቀ ቢሆንም እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ አብረን እንድንጓዝ አድርጎናል፡፡ መሰረታዊ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ በማክበር የሁላችንም መኖሪያ የሆነችውን ሀገር አንድነት በማስጠበቅ፤ በመንግስት አስተዳደር ስርዓት ውስጥ ብዝኃነታችንን የሚያስተናግዱ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና ለጋራ ጥቅም በማዋል፤ እስከ ዛሬ የነበሩንን ጠንካራ ልምዶች ይበልጥ በማጠናከር፣ ከድክመቶቻችን ና ስህተቶቻችን በመማር ብሎም በማሻሻል፣ በአብሮነት ሁሉም አሸናፊና ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት መዘርጋት ይቻላል ብለን እናምናለን። በእኛም ሀገር ይሁን በሌሎች ሀገራት ላይ ለሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ የቆየ አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን፣ በሀገራችን እየተከሰቱ ለምንመለከታቸው ከፍተኛ የንጹሃን ህይወት መቀጠፍ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት የመብት ጥሰቶች ዋነኛው መንስዔ፣ የሀሰት ትርክት የወለደው ብሔር ተኮር የጥላቻ ፖለቲካ መሆኑ ጥርጥር የሌለው አሳዛኝ ሐቅ ነው፡፡ አሁንም መንግስትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት፣ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት፣ ሀገራዊ ፍቅርና ቁርጠኝነት የአለም አቀፍ ሕግጋትን መሰረት ባደረገ መልኩ፤ ያለንበትን 21ኛውን ክ/ዘመን በሚመጥን በሰከነ
ስሜት በቅንነት በመነጋገር፤ መሬት ላይ ያለውን ብዙኃኑን ምስኪን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመስል የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት እስካልወሰኑ ድረስ በሁሉም የሀገራችን ወሰን ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች በዘላቂነት ማስከበር ከቶውንም አይቻልም። ሰብዓዊ መብቶች ባልተከበሩበት፤ የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት፣ ሰላም ባልሰፈነበት ሁኔታ፤ የሀገርን ዕድገትና ለውጥ ዕውን ለማድረግ ማሰብ እጅግ አዳጋች ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ እየተስተዋለ ያለው የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ ልዩነትን መሰረት ያደረገ የብሔር ፖለቲካ፣ የጨቋኝ ተጨቋኝና
የመጤ ሰፋሪ ትርክት ምንአልባትም ከእስካሁኑም ወደከፋ የግጭት አረንቋ ቢከተን ነው እንጂ የዜጎችን ሰው
በመሆናቸው ብቻ እና በዜግነታቸው ማግኘት ያለባቸውን መብቶች ማስከበር ፈጽሞ አይቻልም፡፡
ችግሩን በፈጠርንበት አስተሳሰብ፣ ችግሩን በፈጠሩት የፖለቲካና የታሪክ ስሁት ትርክቶችን ሳናስተካከል መፍትሔ
ማምጣትም ከባድ ነው፡፡ በሀገራችን በየትኛውም ዘመን እንደ ህዝብ ተለይቶ የደላው ወይ ሌላውን የጨቆነ የለም፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመንግስትና የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች በተደጋጋሚ አስረግጠው የተናገሩት ዕውነታ ቢሆንም፣ በተቃራኒው በተዛባ የታሪክ አረዳድ ሆን ብለውም ይሁን በስህተት የፖለቲካ አጀንዳ ባደረጉ አካላት ምክንያት የተነሳ ምንም የማያውቁ ንጹሀን ወገኖቻችን ደም እንደ ጎርፍ እየፈሰሰ ንብረታቸው እየወደመ ይገኛል፡፡ ይህም የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ በመጣል ወደ ከፍተኛ ግጭት፤ ሞት፤ መፈናቀልና ስደት፤ ብሎም ለውጭ ኃይሎች ወረራና ጥቃት ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ከአባይ ግድብ ጋር በተገናኘም ሆነ በቀጠናችን ካለ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ይህ የማይሆንበት ሁኔታ ይኖራል ብለን አንገምትም፡፡ ስለሆነም በቅርቡ በእርስ በርስ ግጭት ሕዝባቸውን ለስደትና ሞት ከዳረጉ ሀገራት በመማር ከምን ጊዜውም በላይ ሀገራዊና ሕዝባዊ አንድነታችንን ማጠናከር የሚገባን ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ መንግስት፣ ሕግና ስርዓት እያለ እንኳ በተገቢው መልኩ ማስቀረት ያልቻለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በጦርነትና በስደት መካከል ደግሞ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችልና ለውርደት እንደሚዳርገን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ይህ ፖለቲካው የወለደው የዜጎች ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ አይነቱን እየቀያየረ አንድ ጊዜ ሀይማኖትን ሌላም ጊዜ ብሔርን ወይንም አመለካከትንና አቋምን ሰበብ በማድረግ ይብዛም ይነስም ያልደረሰበትና ያልነካው
የሕብረተሰብ ክፍል የለም ማለት ይቻላል። የችግሩ ምንጭም የቅርብ ሳይሆን አስርት አመታትን የቆየና አሁን እየባሰ የመጣ ነው፡፡ በሀገራችን ይህ ሁሉ ቢሆንም እንደ ሕዝብ የሚገድልና እንደ ሕዝብ የሚያፈናቅል አላየንም፡፡ ለዚህም ጥቃት በሚደርስባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ተጠቂዎችን ለማዳን፤ ለማሸሽና ለመደበቅ ያደረጉት ወገናዊና ሞራላዊ መልካም ስራ ማስረጃ ነው፡፡
የፖለቲካው በቅንነት በመተማመንና በአንድ ሀገራዊ ስሜት አለመመራት ሁሉንም የሀገሪቱ ዜጎች በየትኛውም ስፍራ በእኩል ዓይን በማየት ለሰብዓዊና የዜግነት መብቶቻቸውን በሚያከብርና በሚያስከብር መልኩ ባለመመራቱ የተነሳ ችግሩን ከማቅለል ይልቅ በማወሳሰብ፡-
- እጅግ ብዙ ንፁሐን ወገኖቻችን ሕፃናትን፡ ነፍሰጡሮችን፡ አቅመ ደካሞችን ጨምሮ ያለ አግባብ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ሆኗል፤
- የሀገሪቱን የቀድሞ ኤታ ማዦር ሹም ጨምሮ የክልል ከፍተኛ አመራሮችን አጥተናል፤
-  ኢማሞችንና ቀሳውስትን ጨምሮ የቤተ እምነት አገልጋዮችን ውድ ሕይወት አጥተናል፤
- በዩንቨርሲቲዎቻችን ለትምህርት የሄዱ ብዙ ወጣቶችን ትርጉም በሌለው ምክንያት ተቀጥፈውብናል፤
- ለትምህር የሄዱ ሴት ተማሪዎችና የጤና ረዳት ሰራተኞች ታግተው ለስቃይ ተዳርገዋል፤
- በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ለምሳሌ እንደ ትራንስፖርት፤ መንገድ መዘጋት፤ ምግብ፤ ባንክ፤ ቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት፣ መድሀኒት ወዘተ አቅርቦት በተደጋጋሚ ረዘም ላሉ ጊዜያት በመቆራረጥ
ሰላማዊ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር እንዲዳረጉ ሆኗል፡፡
- ግምቱ ከፍተኛ የሆነ የሀገርና የህዝብ ንብረትና ሀብት እንዲወድም ሆኗል፤
- ከዚህ ሁሉ በላይ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት፣ ችግራችን የደረሰበትን የአሳሳቢነት ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ለዚህ ጥቃት ዋንኛ መንስኤ ከሀገርና ከሰው ይልቅ ብሔርን ያስቀደመ የማንነት ፖለቲካ ውጤት ሆኖ  እናገኘዋለን፡፡ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ዳግም እንደማይፈጠርስ ምን ማስተማመኛ አለን? ከብሄር፤ ከኃይማኖትና ከፖለቲካ ነጻ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ከውስጡ የወጡ የራሱ ወገኖች ያጠቁት የብሔር ፖለቲካው ውጤት ነው፡፡ ይህም በቶሎ በታላቅ መስዋዕትነት በቁጥጥር ባይውል ኖሮ፣  የሀገራችንን ሉዓላዊነት የሚገዳደርና ከዚህ የከፋ ቀውስ የሚያስከትል እንደነበረ መረዳት አያዳግትም፡፡ ችግሩ ላይ ብቻ ሳይሆን የችግሩ መንስዔ ላይ አተኩረን ለመስራትና ለማስተካከል ከዚህ በላይ ምን ምክንያትና ምቹ ጊዜ እየጠበቅን ነው? ምንስ እስኪፈጠር ነው ለውሳኔ የምንዘገየው? በየቀኑ ክቡር የሰው ነፍስ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተቀጠፈ እያለ የሞተው ወይም ገዳይ ከኛ ነው ከነሱ ነው እያሉ የፖለቲካ ቁማር ከመጫወት ሁላችንንም እንደ ሀገር ከሰውነት ከፍታ ያወረደንን የጥላቻ ፖለቲካ በመመካከርና በማሻሻል የተሻለ ስርዓትን ለትውልድ እናቆይ፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
ጋዜጣዊ መግለጫ
ታህሳስ 22/2013


Read 1177 times