Saturday, 02 January 2021 14:38

ለሰፊ ትከሻ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

 ሁላችንም ትርፍ ስራዎች አሉን፡፡ ሞያ የምንላቸው፡፡ ገቢ የምናገኝባቸው። የምንኮራባቸው፡፡ ግን ዋና ስራዎቻችን አይደሉም፡፡ ዋናው ስራችን ታርጋ መለጠፍ ነው፡፡ ብዙ ታርጋዎች አሉን፡፡ ግን እነሱም አንዳንዴ ያልቁብናል፡፡
በተለይ እንደ ደረጄ አይነቱ ሰው ላይ የምንለጥፈው ሁሉ አልይዝ እያለ፣ እየወደቀ አስቸግሮናል፡፡ ታርጋ ያስፈልገዋል፡፡ ግን የለጠፍንበት ሁሉ ተመልሶ ወደ እኛው ይመጣል፣ እንደ ተመላሽ ፖስታ፡፡ አድራሻ እንዳላገኘ መልዕክት፡፡ “Return to the sender address unknown” የሚለውን የኤልቨስ ሙዚቃ እያዜመ ወደኛ ይመለሳል።
ቁርጥ የሆነው ነገር ደረጄ መፈረጅ እንዳለበት ነው፡፡ መፈረጅ ያለበት ደግሞ ስለጠላነው ነው፡፡ በእኛ ቡድን ውስጥ በሙሉ ድምፅ የተጠላ ሰው፣ እንደ ደረጄ ኖሮ አያውቅም፡፡ የጠላነው ደግሞ አንድ ላይ ነው፡፡ ከመቼ ጀምሮ መጥላት እንደጀመርን አምስታችንም የተለያየ ምክኒያት ነው የምናቀርበው። የምንስማማው የጥላቻችን መራርነት ላይ ብቻ ነው፡፡ እና ፍረጃ በአስቸኳይ መለጠፍ አስፈላጊ መሆኑ ላይ። አምስት ሆነን ስድስተኛውን ደረጄን ነው መፈረጅ የፈለግነው፡፡ በዘላቂነት ጀርባው ላይ የሚጣበቅ ስም ግን ልናወጣለት አልቻልንም፡፡ ደረጄ ደግሞ ለስም አይመችም፡፡ ከራሱ ስም ባሻገር፣ ከጥንት ጀምሮ ልናወጣለት የሞከርናቸው ቅፅል ስሞች፣ ራሳቸው በራሳቸው ጊዜ እኛኑ መልሰው ትን እያሉን፣ እያቃሩን ስንቸገር ኖረናል፡፡ ቅፅል ስም እንኳን አይቀጠልልንም፤ ይቅርና ፍረጃ፡፡
መፈረጅ ከቻልንና ፍረጃው ደግሞ ጀርባው ላይ ሳይወድቅ እንደ ታርጋ ሆኖ መቀመጥ ከሆነለት…. ከዛ በኋላ… ከፍረጃው ውስጥ ፍርዱን የታርጋው ተሸካሚ ይቀበላል። በታርጋው አማካኝነት ቅጣቱን ያገኛል፡፡ ታርጋው በሄደበት ከጀርባ የሚያየው ሁሉ እንዲጠላው ይሆናል፡፡ እኛ እንደጠላነው አለምም ይጠላዋል፡፡ ከዛ በራሱ ሰዐት ወደ መሬት እያጠረ ይሰጥምና ይሰወራል። የጥላቻችን ምክኒያት አንድ ቢሆን፣ ተባብረን ስም ማውጣት ራሱ ያንን ያህል ባልከበደን ነበር፡፡ ግን ምክኒያቶቻችን የተለያዩ ናቸው፡፡ አምስታችንንም  እንደየ ስም አልፋ ቤታችን በቅደም ተከተል ባስቀምጥ… እኔ “ቢ” ነኝ፡፡ በንግድ ስራ ነው የምተዳደረው፡፡ ደረጄ “ዲ” ነው፡፡  እኔ በደንቆሮነቱ ነው የምጠላው፡፡ ግን ደንቆሮ መሆኑን ለማሳመን በቂ ማስረጃ ሳላገኝ ጥላቻዬን ብቻ ያለ ምክኒያት ይዤ አለሁኝ፡፡
ከመሃከላችን “ፐ” የሚባለው ደረጄን መጥላት የጀመረው “Middle name” በስሙና በአባቱ ስም መሃል ከጨመረበት ጊዜ ጀምሮ ነው ባይ ነው፡፡ የደረጄ ሙሉ ስም ከድሮ ጀምሮ አብሮ አደጋችን ሆኖ ሲያድግ፣ “ደረጄ ባምላኩ” ተብሎ ነበር። አንድ አመት ከመንፈቅ ቀደም ብሎ “Dereje W. Bamelaku” ብሎ የስሙን ትንሳኤ ካወጀ በኋላ “ፐ” ጠመደው፡፡
“ፈረንጅ ልሁን ነው ወይንስ የገዢው መደብ ሰው ነኝ ለማለት ነው… በአባቱ እና በራሱ ስም መሃል አዲስ መጠሪያ መክተት ያስፈለገው"… በጣም ዘረኛ ሰው መሆኑን ካወቅሁ በኋላ ነው የጠላሁት… ደግሞ ድሮውኑ ባውቅ ችግር አልነበረውም… ዘረኝነቱ ፋርነቱንም ያመለክታል፡፡ … Middle name’ሜን ጨምረህ ካልጠራህ አቤት አልልህም ሲለኝ… Middle finger አሳየሁት…” በማለት የጥላቻውን ምክኒያት “ፐ” ለማጉላት ሞክሯል፡፡ ግን እሱን ለጥላቻ ያነሳሳው ምክኒያት በሌሎቹ የግሩፑ አባላት ዘንድ ያንን ያህልም ተቀባይነት አላገኘለትም።
“እሱ እንኳን ይሁን…” ይላል “ኤፍ” የተባለው ጓደኛችን፡፡ “እሱ እንኳን ይሁን ችግር የለውም፡፡ ምናልባት የጨመረው አዲሱ ተቀጥያ እውነተኛው የአባቱ ስም ሊሆን ይችላል፡፡ ጋሽ ባምላኩ እውነተኛው አሳዳጊ አባቱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በጥልቀት በገሩን ሳናውቅ ድምዳሜ ማድረግ  እኔ በበኩሌ ይከብደኛል፡፡ … ይልቅስ እኔ የእሱ ባህሪ  እያስጠላኝ የመጣው የማስተርስ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ ነው፡፡ … አካሄዱም አነጋገሩም… አሳሳቁም የውሸት ሆነ፡፡ ደረቱን በትዕቢት መንፋት ጀመረ፡፡ ድሮ እንደ ደጋን ጎብጦ ትምህርቱን ሲማር እኛን እየቀፈለ እንዳልነበር… አሁን ጥጋቡ አላስቀምጥ አለን፡፡ ስንት ክረምት የእኔን ምግብ እየበላ አሳልፏል፡፡
ለብሶ የሚመጣውን ቡቱቶ የእኛ ቤት እቃዎች ተጠይፈው በየስርቻው ገብተው ከጠፉበት እስካሁን መቼ ተገኙና ነው እሱ በእኔ ላይ ደረቱን የሚነፋው"… ገና ነገና ዘመኑ የእኔ ነው ብሎ ጠባይ መቀየር ደስ አይልም፡፡ ሹመት ቢያገኝ ለራሱ ባያገኝ ለራሱ… ለእኔ አምስት ሳንቲም የሚደርስ ነር የለም፡፡ እዛው ራሱን ችሎ የሚኖር እኛም ራሳችንን መሸከም አቅቶን የማናውቅ ሰዎች ነን፡፡ ታዲያ ምንድነው መሬት አይንካኝ ማለት"… “ብሎ “ኤፍ” ይቀጥላል። የእሱ ምክኒያት፡- ለራሱ የሰጠውን ዋጋ ለሌሎቻችን አልሰጠንም የሚል ይመስላል። ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ምንም ምክኒያትም ላይኖረው ይችላል፡፡
ሁላችንም የየራሳችን ጥላቻ ይበልጥብናል። እንደ ብጉር እናዳትፈርጥ ጠጠንቅቀን የምናሻሻት የጥላቻ እባጭ አለችን። ለጥላቻችን መንስኤ የሆኑት የእርስ በራሳችን ምክኒያቶች ግን አያሳምኑንም። የተስማማንበት ነገር ጥላቻው ላይ ብቻ ነው፡፡
“Z” ደግሞ የሚጠላው የደረጄን ሚስት ነው፡፡ የደረጄ ሚስት (እሱ እንደሚለው) ያላደረገችው ነገር የለም፡፡ መጀመሪያ ሚስቱን ከደረጄ ነጥሎ ነበር የሚጠላው፣ በሂደት ግን የሚስትየው ተፅዕኖ ባልየው ላይም እየተንፀባረቀ መምጣቱን አስተዋለ። “ተው የድሮ ወዳጅነታችን ይሻለናል… ሚስት ይመጣል ሚስት ይሄዳል:: ደግሞም ሚስትህ ናት እንጂ እናትህ አይደለችም፡፡ … እንደዚህማ እንድትለውጥህ አትፍቀድላት”  የሚል ለዘብተኛ ምክር ለመለገስ ሞክሮ ነበር፡፡
ደረጄ ምክሩን ተቀብያለሁ ማለቱን የቡድኑ አባላት በአጠቃላይ ሰምተዋል። “Z” ግን አልሰማም ባይ ነው፡፡ “ጭራሽ ለዓመት በዓል ቤቱ ብሄድ የለሁም ብሎ መለሰኝ… በዛ ላይ የእናቴ ሙት አመት የሚውልበትን ቀን ጠብቆ የራሱን ልጅ የአምስት አመት ልደት ለማክበር ደገሰ። ደግሞም ይቅርታ እንኳን አላለኝም። … አሁን አሁንማ ከመጀመሪያውም የችግሩ ምንጭ ሚስቱ እንዳልነበረች ግልፅ እየሆነልኝ መጥቷል። እንዲያውም ሚስቱ ክፉ እንድትመስል የቀረፀብኝ እሱ በእኔና እሷ መሃል እንደ ሽብልቅ ገብቶ ነበር፡፡ ወሬ እያመላለሰ እንደነበር ተረድቻለሁኝ” ብሎ የጥላቻውን ንዳድ የሙቀት ደረጃ፣ ለእኛ ለማስገንዘብ ይሟሟታል፡፡ እኛም በቴርሞሜትራችን የእርስ በራሳችንን የጥላቻ መጠን እንለካካለን። ሙቀቱ ሁላችንም ላይ ተመሳሳይ ነው፡፡ በደረጄ ምክኒያት በጥላቻ ንዳድ ታመናል፡፡ ንዳዱን የቀሰቀሱብን ምክኒያቶች ግን ለየቅል ናቸው፡፡ ወደ አንድ ህብረት መጥተው የትግል ግንባር ለመፍጠር አስማሚ ፍረጃ በመካከላችን ለመትከል የተሳነንም በዚህ ምክኒያት ነው፡፡
አምስተኛዋ የጥላቻ ቡድናችን አባል “A” ናት፡፡ ምናልባት የእሷ የጥላቻ አይነት መላ ቅጡ የጠፋበት በመሆኑ ሊሆን ይችላል፤ ስኬታማ የሆነ የፍረጃ ታርጋ ለባላንጣችን ማግኘት ያልቻልነው፡፡ “A” አንደኛ ደረጃ በፆታዋ ሴት ናት፡፡ ወደ ጓደኛሞቹ ቡድን የመጣችው ዘግየት ብላ ሲሆን አምጥቶ ያስተዋወቃት ደግሞ ደረጄ ራሱ ነበር። ደረጄ ይዞ ሲያመጣት እንደ ፍቅረኛው ነገር ነበረች፡፡ በኋላ በዛው ቡድን ውስጥ ታቅፈው ታቅፈው እንዳሉ ተደባብረው ተለያዩ፡፡  በጓደኝነት እንቀጥል ተባብለው ተስማምተው፣ እሱ በመቀጠል አሁን አግብቶ አብሯት በመኖር ላይ ያለችው ሚስቱ ላይ ደረሰ። ያኔ ግን “ኤ” አዲስ የፍቅር ጓደኛ እንደያዘ አላወቀችም ነበር፡፡ በፎንቃ ደረጃ የማይቀር ፍቅር ሳይዛት አልቀረም ማለት ነው፡፡ በጓደኝነት እንቀጥል ያላት ቀን የተስማማችው፣ በጓደኝነት ሲቀጥሉ እንዳይርቅ መቆጣጠር ቀላል ነው ብላ አስባ ሊሆን ይችላል፡፡ ለማግባት መወሰኑን የነገራት ዕለት “A” የደረጄ ጠላት ሆነች፡፡
ግን ጠላትነቷ ቁርጥ ያለ አቋም የያዘ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንድ ፍረጃ በአባላቱ ፀድቆ በእሱ ጀርባ ላይ ለማተም ሲወሰን ነጠል ብላ የምታቅማማ እሷው ነች። ውሳኔያቸውን ከተለያየ አንጻር በመተንተን ቁርጠኛ አቋም እንዳይዙ ግራ ታጋባቸዋለች።
ከ“ኤ” በስተቀር ሌሎቹ አንድ መጥፎ ነገር ደረጄ ቢያጋጥመው የአንጀታቸው ንቃቃት በቅቤ የሚርስላቸው ናቸው። “ኤ” ግን በጥላቻ ሰንደቋ ላይ ሙሉ እምነት ቢኖራትም የምትጠላው ሰውዬ ግን እንዲሞትባት አትፈልግም። እንዲሞት የማትፈልገው ለመጥላት ራሱ የሚጠላው ነገር በህይወት መኖር ስላለበት ነው ብላ የተለያዩ የሞራል አስተምህሮቶችን አስደግፋ ታብራራለች።
ማብራሪያዋን ግን የተቀሩት የቡድኑ አባላት በሙሉ ልብ አይቀበሏትም። የማይቀበሉበትም ምክኒያቱ ግልፅ ነው፣ ቢያንስ ለእነርሱ፡፡ የምትጠላውን ሰውዬ የምትወደውም በመሆኑ ምክኒያት ነው፡፡ የምትወደው ሰውዬ እንዲኖር  የምትጠላውም እሱነቱ አብሮ መዝለቅ መቻል አለበት፡፡ ግን ይሄ ማለት እንዲጎዳ አትፈልግም ማለት አይደለም። በደንብ አድርጎ እንዲጎዳና ከጉዳቱ እንዲማር ትፈልጋለች፡፡ ሲማር ደግሞ በወሰደው ትምህርት ምክኒያት ተፀፅቶ ወደ ቀድሞው የእርሷ እቅፍ ዞሮ ሲገባ ታልማለች፡፡
“ኤ” እና “ዜድ” አንዳንድ ጊዜ ይስማማሉ። በተለይ የሁለቱም ዋና ጠላት የደረጄ ሚስት መሆኗ ግልፅ ብሎ በታያቸው ጊዜያት ይስማማሉ። ደረጄ ላይ የፍረጃ ታርጋ ከመለጠፍ የተለጠፈችበትን ሚስት አውልቆ መጣል የተሻለ ውጤት ያመጣል ብለው ይዶልታሉ፡፡
“ግን እኔ ምን የጎደለኝ ነገር አለ¿” ትላለች አንዳንድ ጊዜ ለቡድኑም ጆሮ መተነጣጠረ መጠይቅ፡፡ “…እኔ ላይ የማይገኝ ብርቅ ነገር ሚስቱ ላይ ከተገኘ ጥሩ ነው፡፡ ያዝልቅላቸው። … ለእኔ ሲገባልኝ የነበረውን ቃል እሷ ላይ ካከበረው ጥሩ ነው፡፡ ግን አይመስለኝም።… ስለ ሚስቱ ሳጣራ ነበር፡፡ … ብቻ በአጭሩ ጥሩ ሴት ላይ አልወደቀም። ትንሽ ሹመት ስላገኘ ነው የተጠጋችው… አትቆይም፡፡ አጣርቻለሁኝ፤ እንደዛ አይነት ሴት ናት፡፡
ስለዚህ በራሱ ግዜ ሲነቃ ከስህተቱ ይማር። ግን እሱ በየስርቻው እየወደቀ ተጎድቶ ሲመጣ፣ እኔ እጄን ከፍቼ የምቀበለው ከመሰለው ተሳስቷል፡፡ የሄደው ሲመለስ የተመለሰበት ባለበት ተቸክሎ አይጠብቅም፤ ይንቀሳቀሳል…” ትላለች “ኤ”። ይሄንን እያለች ወደ ስድስት አመት ገደማ እንዳለፋት እንኳን ልብ ያለች አትመስልም፡፡
የሃሜት ቡድናችን ስራ ማልጎምጎም ሆኖ ይቀራል፡፡ ደረጄ ለማደግ የሚወስዳቸው አማራጮች እየበዙ በመጡ ቁጥር የሚበሽቅ አባል፣ ጥላቻውን ባልተያያዘ ምክኒያት አጅሎ ይረጫል። ግን ምንም ማድረግ አይችልም። ለደረጄ ሰፊ ትከሻ የሚመጥን ታርጋ መፈብረክ አልተቻለም፡፡፡ በጠባብ ትከሻ እና ፣ በቀላሉ እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ የሚበታተን ሰብዕና ላይ በቀላሉ የሚለጠፍ ታርጋ ለደረጄ ጀርባ አልመጠነውም፡፡ አንዱም ተጣብቆ አይቀመጥም፡፡ ወይንም ተጣብቆ ከተቀመጠ ደግሞ ከተለጠፈበት ሰው ግዙፍነት አንጻር ሲተያይ እንደ ዝንብ ማረፉ እናኳን የማይታይ የቁሻሻ ብናኝ ይሆናል፡፡
ከጊዜ ሂደት በኋላ በቁመቱም በግዙፍነቱም የቡድኑ አባላት ሊደርሱበት የማይችል መጠነኛ ተራራ ሆነ፡፡ አይናቸው እያየ፡፡ እዛው በጓዳቸው ሆነው ሲያልጎመጉሙ እሱ ግን ወደ ፊት ተጓዘ፡፡ ተራራ ከሆነ በኋላ በመዐረግም፣ በርቀትም ሊደራረሱ ስለማይችሉ፡- “እሱን እኮ ድሮ አውቀዋለሁኝ፡፡
እናቱ የስጋ ደዌ በሽተኛ ነበረች። ሚስቱ ሴተኛ አዳሪ ናት፡፡ ወላጅ አባቱን አያውቀውም፡፡ እናቱ ሰራተኛ ሆና ከምትሰራበት ቤት ነው እሱን ያረገዘችው” በሚሉ እዛው በትንንሽ ጓዳዎቻቸው ውስጥ በሚፈበርኳቸው ታርጋዎች  ለመፅናናት ጣሩ፡፡
“ውሸታም” በሚል የመልስ ምት  የሰነዘሩት ሁሉ ተመልሶ መምጣት እስኪጀምር እና ተቀባይነት በእርስ በራሳቸውም መሃል እየጠፋ መጣ
ግን የቡድኑ አባላት ምናልባት ከ “ኤ” በስተቀር ዋነኛውን ጽኑ አቋማቸውን አልቀየሩም፡፡ ለደረጄ ያላቸውን ንፁህ ጥላቻ፡፡


Read 2110 times