Saturday, 09 January 2021 11:02

አራት የህወኃት ከፍተኛ አመራሮች ሲገደሉ ዘጠኝ በቁጥጥር ስር ውለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

     ከህወኃት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የቡድኑን ቃል አቀባይ ሴኩቱሬ ጌታቸውን ጨምሮ አራቱ ሲገደሉ፣ ዘጠኝ ያህሉ እጅ መስጠታቸውን መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ፡፡
የሰሜን ዕዝን በ45 ደቂቃ ውስጥ መብረቃዊ ጥቃት በመፈፀም ከጥቅም ውጭ አድርገነዋል ብለው የገለጹት የህወኃት ቡድን ቃል አቀባይ  አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው ፣የቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅና የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዘርአይ አስገዶምና የድምጻዊ ወያኔ ሃላፊ የነበሩት አቶ አበበ አስገዶም እንዲሁም የትግራይ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ዳንኤል አሰፋ የመከላለከያ ሰራዊት  ታህሳስ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በወሰደው እርምጃ ከሹፌርቻቸውና ከጠባቂዋቻቸው ጋር መደምሰሳቸው ተገልጿል፡፡
ባለስልጣናቱ እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲሰጡ የቀረበላቸውን ጥያቄ አንቀበልም  በማለታቸው የሃይል እርምጃ እንደተወሰደባቸው ታውቋል፡፡
የክልሉ የቀድሞ የም/ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣የቀድሞ የትግራይ ክልል ከተማ ልማት ቢሮ ሃላፊና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ የነበሩት ዶ/ር ሰለሞን ኪዳነ የማረት (ማህበር ረድኤት ትግራይ) ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፤ የክልሉ ንግድ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ገብረመድህን ተወልደ፣ የክልሉ የመንገድ ትራንፖርት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ደስታ፣ በሱዳን  የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳዳር አባዲ ዘሙ፣ የመለስ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንትና የኢፈርት ቦርድ ሃላፊ የነበሩት አቶ ቴዎድሮስ ሃጎስ፣ የክልሉ የንብረት ግዢ ስራ ሂደት ሃላፊ የነበሩት አቶ ብርሃነ አደም መሀመድንና የክልሉ ም/ቤት ህግ አማካሪ የነበሩት ወ/ሮ ምህረት ተክላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቁሟል።
ቀደም ሲል የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የትራንስፖርት ሚኒስተር ዴኤታ የነበሩት ወ/ሮ ሙሉ ገ/እግዚአብሄር፣የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ አዲስ አለም ባሌማን ጨምሮ በርካታ የህወኃት አባላት የጦር መኮንኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸው አይዘነጋም።
የመከላከያ ሰራዊቱ ቀሪ የህወኃት አመራሮችና ግብረ አበሮቻቸውን አድኖ ለመያዝ የሚያደርገውን አሰሳ አጠናክሮ  መቀጠሉንና የህግ ተፈላጊዎቹ ራሳቸውን በመቀየር በየአቢያተ ክርስቲያናቱና የእምነት ተቋማት ውስጥ ተሸሽገው እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡  

Read 1247 times