Saturday, 09 January 2021 11:38

የ700 ዓመት ዕድሜ ያላት ደብረሲና ማርያም ገዳም እንዴት ተመሰረተች?

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

  ከጎንደር ከተማ በስተምዕራብ 61 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ጣና ሀይቅ ዳር ትገኛለች የ701 ዓመቷ ደብረ ሲና ማርያም ገዳም። ብዙዎች ሊያዩት ሊጎበኙት ይሻሉ፤ ይጎበኙታልም። በጎርጎራ ከተማ ውስጥ የምትገኘው ይህቺ ጥንታዊት ገዳም በ1312ኛው ክፍለ ዘመን በንጉስ አምደ ፅዮን መንግስት ወቅት ኤስድሮስ በተሰኘ የ    ንጉስ አምደፂዮን የጦር መሪ መመስረቷም ሰሞኑን ለስራ ወደ ጐርጐራ ባቀናሁበት ጊዜ ተነግሮኛል።
እንደ ገዳሙ አባቶች ገለፃ፤ የደብረሲና ማርያም አመሰራረት አስደማሚና ተዓምራዊ ጭምርም ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። ገዳሟ አሁን የምትገኝበት የሀይቁ ዳር አካባቢ በደን የተጠቀጠቀና የሽፍቶች መኖሪያ ነበር። ሽፍቶቹም ባሻ ጐርጐጎር፣ ባሻ አትርፍ፣ ባሻ ስማንና ባሻ ጐራድ ይባሉ እንደነበር ይነገራል።
እነዚህ ሽፍቶች የአካባቢውን ነዋሪ አላስወጣ አላስገባ በማለት፣ በመዝረፍና በመግደል በእጅጉ በማማረራቸው ህዝቡ ለንጉስ አምደ ፂዮን አቤቱታ ማቅረቡን ይናገራሉ።  እንደ ዲያቆን ቀለመወርቅ መልካሙ ገለጻ፤ (የገዳሟ ወጣት አገልጋይ ነው) ንጉስ አምደ ጺዮን የህዝቡን አቤቱታና እሮሮ ካዳመጡ በኋላ ሽፍቶቹን ለመዋጋት ኤስድሮስ በተባለ የጦር መሪያቸው አማካኝነት ጦር ያዘምታሉ።
የጦር መሪው ኤስድሮስ ከሱ ቀድመው የነበሩ ጦር መሪዎች ጦርነት ለመግጠም ሲዘምቱ ታቦተ ፂዮንን ይዘው እንደሚሄዱ ያውቅ ስለነበር “እኔስ ለምን የእመቤታችንን ታቦት ይዤ  አልዋጋምና ድል አልነሳም” በማለት ዛሬም ድረስ “ግብፃዊት ማርያም” የተባለች የምትጠራውንና ምስሏ በገዳሟ ምስራቃዊ ክፍል ላይ አሁንም የምትገኘውን ምስለ ማርያም አስሎ ማስመጣቱን ነው ታሪክ የሚናገረው።
እንደ ገዳሙ አባቶች ገለፃ፤ ኤስድሮስ ምስለ ማርያምን ከግብፅ እንዳስመጣ “ወዳጄ ሆይ ጠላቶችህን ድል ትነሳለህ” በማለት ለዚሁ የጦር መሪ በድምጽ መገለጧን ይናገራሉ።
ኤስድሮስ ምስለ ማርያምንና ታቦቷን ይዞ ጦሩን መርቶ ሽፍቶቹን ገጠመ እናም ድል ነሳ።
የጦር መሪው ኤስድሮስ ሽፍቶቹ ድል ከነሳ በኋላ በዚህ አካባቢ ለስሜ መጠሪያ የሚሆን አንድ ማስታወሻ ተክዬ መሄድ አለብኝ ብሎ አሰበ ዙሪያ ገባውንም ቃኘ። በዚህ ቅኝቱ አንድም ቤተ ክርስቲያን ባለማየቱ ጦርነቱን ድል እንዲነሳ ያገዘችውን ማርያም ቤተክርስቲያንን ለማሰራት ወሰነ ይላሉ የገዳሙ አባቶች።
እናም ለቤተ-ክርስቲያኑ ማቆሚያ የሚሆን 12 ዓምድ (ወጋግራ) የዝግባ እንጨት እንዲያመጡለት ሰራተኞቹን ወደ ጎጃም ዘጌ አካባቢ የላከው ኤስድሮ፤ 11ዱ እንጨቶች ተገዝተው ሲጫኑ 12ኛውን እንጨት ለመግዛት ከሻጩ ጋር በዋጋ መፋረሳቸውን ይገልጻሉ። ሰራተኞቹም 11ዱን ወጋግራ ጭነው መጡ። ይህ በዋጋ መፋረስ ምክንያት የቀረው አንድ ወጋግራ ባልታወቀ መልኩ በጣና ማዕበል እየተገፋ አሁን ገዳሟ ያለችበት ቦታ ድረስ መምጣቱን ይህም ተዓምረ ማርያም ሆኖ በገዳሟ ታሪክ የሚነገር ነው። ይህ 12ኛውና በማዕበል ተገፍቶ የመጣው አምድ (ወጋግራ) አሁን በገዳሟ የሴቶች መግቢያ በር በኩል ይገኛል።

ደብረ ሲና ማርያም ገዳም  በምን ትለያለች?
ይህ አሁን ጐርጐራ የሚባለው አካባቢው ኤስድሮስ ሽፍቶቹን ካሸነፈ በኋላ በአብዛኛው የወታደሮች መኖሪያ ሆኖ መቀጠሉ ይነገራል። ከብዙ ጊዜ በኋላ በዚህ አካባቢ ያሉ ወታደሮች ሌላ ጦርነት ገጠማቸው። ወደ ጦርነቱ ከመሄዳቸው በፊት በወቅቱ የገዳሟ አስተዳዳሪ ለነበሩት አባ ተስፋ ማርያም ለተባሉ አባት ስዕለት ተሳሉ። “ጦርነቱን አሸንፈን ጠላቶቻችንን ድል ነስተን ከተመለስን የደብረ ሲና ማርያም ገዳምን የሳር ክዳን በቆርቆሮ እንቀይራለን” ብለው። ወታደሮቹ ያለ ብዙ ጉዳት ጦርነቱን አሸንፈው ተመለሱ፤ እናም ስለታቸውን ለማድረስ ቆርቆሮ ገዝተው የሳር ክዳኑን ገፍፈው ቆርቆሮ ሲመቱ ዋሉ ይላሉ የገዳሟ አባት።
ይሁን እንጂ ቆርቆሮ ክዳኑ ነፋስ ጣና ውስጥ ይክተተው ምን ውስጥ ይውደቅ ምን ይሰውረው ከጣሪያው ላይ ጠፍቶ አደረ። በነጋታው መደናገጥ ተፈጠረ፣ ቆርቆሮውን ገዝተው ጣሪያውን ያለበሱት ከጦርነት የተመለሱትም ወታደሮች ግራ ተጋቡ። ነገር ግን የወቅቱ የገዳሙ አስተዳደሪ አባ ተስፋ ማርያም “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ቆርቆሮ ከላዬ ላይ አንሳልኝ በሚል በህልሜ ተገልጣልኛለች”
በማለት ተናገሩ። ይህም ለገዳሟ ሌላው ትልቁ ተዓምረ ማርያም ሆኖ የሚነገር ሲሆን እነሆ ይህቺ ጥንታዊት ገዳም አሁንም ድረስ የሳር ክዳን ያላት መለያዋም ሆኖ ቀጠለ እንደሆነ ነው በጉብኝታችን ወቅት የሰማነው። አባቶችም ይህቺን ገዳም ቆርቆሮ ለማልበስ አቅም ጠፍቶ እንዳልሆነና በማርያም ፈቃድ የሆነ ነው ይላሉ። ገዳሟ በ700 ዓመት ዕድሜዋ ውስጥ የጣሪያዋ የእንጨት እድሳት በ1974 ዓ.ም አንድ ጊዜ ብቻ ከመቀየሩ በስተቀር ወጋግራውም ሆነ ግድግዳው እስከዛሬ የተነካ ነገር እደሌለ ነው የሚነገረው። እርግጥ ነው የሳር ክዳኑ በ30 ወይም በ40 ዓመት አንዴ ይታድሳል ብለዋል።
በዚህ ገዳም ውስጥ ቀንና ሌሊት ፀሎት አይቋረጥም የገቢ ምንጯም ከውጭና ከሀገር ውስጥ የሚመጡ ጎብኚዎች ነበሩ። አሁን በኮቪድ ምክንያት ጎብኚ በመቋረጡ ገቢዋም ተቋርጧል ይላሉ የገዳሙ አገልጋዮች። አልፎ አልፎ የሚያጋጥም የፀጥታ ችግርና ከአንዳንድ ተቋማ ጋር ያለ የይዞታ ጭቅጭቅ ከገዳሟ ተግዳሮቶች ውስጥ የሚጠቀሱት ናቸው።

ጐርጐራ ከተማ ስያሜዋ እንዴት አገኘች
ጐርጐራ የደብረሲናን መመስረት ተከትሎ የተቆረቆረች በዙሪያዋ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች የከበቧት ነገር ግን የከተሞች መሪ ሆና የተፈጥሮ ሀብት ታቅፋ በስልጣኔና በመሰረተ ልማት ጭራ የሆነች ከተማ ስለመሆኗ በቦታው ሶስት አራት ጊዜ ስመላለስ ታዝቤያለሁ።
ከተማዋ ስያሜዋን ያገኘችው ከአራቱ ሽፍታዎች አንዱ ከነበረው ባሻ ጐርጐር ስያሜ ተነስቶ ጎርጎራ እንደተባለችይነገራል። በነገራችን ላይ  በአራቱም ሽፍቶች ስም የተሰየሙ ቦታዎች አሉ።
ባሻ ጎርጎር በጐርጐራ ሲታወስ ባሻ ስማን በሚለው ስማን ተክለሃይማኖተ ገዳም ድ በሚለው ሲሰየም ባሻ ጎራድ በተሰኘዉ ሽፍታ ደግሞ በዚያው አካባቢ ጎራንድ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሚገኝ ይገኛል። ባሻ አትርፍ በሚለው ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረች ጊዜ  የኢትዮጵያ ህዝ አገሩን ለማትረፍ ያደረገውን ተጋድሎ ለማስታወስ የሞሰሎኒ ሀውልት እየተባለ የሚጠራው ግንብ አትርፍ እየተባለ እደሚጠራ የገዳሙ አገልጋይ ዲያቆን ቀለመወርቅ መልካሙ በጉብኝታችን ወቅት ገልጾልናል።
ጐርጐራ እንደ ዕድሜዋና እንደ ታሪኳ ብዙ ነገር ሊኖራት ሲገባ፣ የአካባቢው ነዋሪ ብዙ መሰረተ ልማት ሊኖረው ሲገባ እስከዛሬ ምንም ያልተሰራበት አካባቢ ነው። በጣም የሚያሳዝን አካባቢ አንጀት የሚበላ ህዝብ። አሁንስ ጐርጐራ ተስፋዋ ማን ነው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አይደለምን?

Read 8974 times