Wednesday, 13 January 2021 19:21

ዛሬ “ንፍሮ በተንሽብኝ”፤ ነገ “ስንዴ አበድሪኝ”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

  "እኔ የምለው ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... የዘንድሮ ጎረቤቶች በድመት የተነሳ የማይጣሉት ለምንድነው! ድመት ጨምቶ ነው ወይስ በአንዳንዶቻችንና በድመት መሀል ያለው ልዩነት ስለጠበበ ነው!? (ቂ...ቂ...ቂ...)"
          
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ... በቃ ዘመን እንዲህ ልውጥውጥ ብሎ ይረፈው!
ጎረቤት አንድ፡— እዚህ ቤቶች! እዚህ ቤቶች! (የግቢው በር እንደ ጉድ ይደበደባል.)
ጎረቤት ሁለት፡— ማነው እሱ! ምንድነው የሰው በር እንደዚህ መቀጥቀጥ! (ይከፈታል) ውይ አንቺ ነሽ እንዴ! እኔ ደግሞ የማን ጥጋበኛ መጣብኝ ብዬ!
ጎረ. አንድ፡— ጥጋቡ ያለውማ እናንተ ዘንድ፡፡
ጎረ. ሁለት፡— ደግሞ በጠዋቱ ምን ሆንኩ ልትይ ነው?
ጎረ. አንድ፡— እናንተ ሰዎች... ለእናንተ ብለን ሀገር ለቀን መሄድ አለብን እንዴ!? 
ጎረ. ሁለት፡— አሁን ደግሞ ምን አደረጋችሁ ልትሉን ነው?
ጎረ. አንድ፡— ጭራሽ እኔኑ ትጠይቂኛለሽ! ይሄንን ጽልማሞት የመሰለ ድመታችሁን ለምንድነው አስር ጊዜ የምትልኩብን!
ጎረ. ሁለት፡— አንቺ ሴትዮ ምን ነካሽ! ምን ይሁን ብለን ነው ድመት እናንተ ላይ የምንልከው!
ጎረ. አንድ፡— የማታውቂ ይመስል ምን ትጠይቂኛለሽ፡፡ አሁን የእኛ ኑሮ ኑሮ ሆነና መተት ይደረግብናል!
ጎረ. ሁለት፡— አይ አልበዛም፣ ዝም ስልሽ የፈራሁሽ መሰለሽ! ይሄን አስር ክንድ ምላስሽን ሰብሰብ አድርጊልን፡፡
ጎረ. አንድ፡— ጭራሽ ምላሰኛዋ እኔው ሆንኩ እንዴ! ያንቺው አለ አይደል እንዴ... በሀያ  አራት ሰዓት ድፍን ሀገር ዞሮ የሚመጣ። (በሩ ድርግም!)
በማግስቱ...
ጎረ. አንድ፡— ስሚ፣ ሽሮ አልቆብኛል፡፡ ለአንድ ድስት ያህል አበድሪኝ እስቲ...
ጎረ. ሁለት፡— ኧረ የፈለግሽውን ያህል ውሰጂ፡፡
እኔ የምለው ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... የዘንድሮ ጎረቤቶች በድመት የተነሳ የማይጣሉት ለምንድነው! ድመት ጨምቶ ነው ወይስ በአንዳንዶቻችንና በድመት መሀል ያለው ልዩነት ስለጠበበ ነው!? (ቂ...ቂ...ቂ...)
ዘንድሮ... አለ አይደል... ጉርብትና የሚለው ነገር የቀነሰ ነው የሚመስለው፡፡ ኮንዶሚኒየም  ትንሽም ቢሆን ወደ ዘመናዊ ኑሮ ያስጠጋን ጀመር ስንል ጭራሽ እጎን ለጎን ሆነን፣ ማዶ ለማዶ አደረገንና አረፈው! አሀ... “ቀይ ክር አንገቱ ላይ አስራችሁ ጥልምያኮስ የመሰለ ድመት ላካችሁብኝ!” “በሬ ስር ንፍሮ በትናችሁብኝ አደራችሁ!” ለመባባል እኮ መጀመሪያ እንደ ጎረቤት ነገር መሆን ያስፈልጋል፡፡
ግን እኮ ውሎ አድሮ ከዛም ሳይሰነብት...አለ አይደል... ሳይቆይ “ንፍሮ በተናችሁብኝ” ብለው የከሰሱት ሰዎች ለ‘በታኞቹ’ ምን ቢሏቸው ጥሩ ነው... “ለእንትን በዓል ንፍሮ መቀቀል ፈልጌ እስቲ የስንዴ አህል ካለሽ ግማሽ ጣሳም ቢሆን ላኪልኝ፣” ሊሏቸው ይችላሉ፡፡ (እነሱ የሚቀቅሉት የሚበተን ሳይሆን የሚበላ ንፍሮ ነዋ!) እናላችሁ... የዘንድሮ በር ቆልፎ ማድፈጥ የሆነ፣ አንዱ ሲደናቀፍ “እኔን ይድፋኝ!” የሚል የጠፋበትን ጊዜ ስታዩ... አንዳንዴ እኮ የበፊቱ ‘ድመትና ንፍሮ የሚያስነሱት በአጥር ላይ የሚወረወር ጭቅጭቅ ይናፍቃችኋል፡፡ የምር ግን እኮ ይሄ የጉርብትና ነገር መቀዝቀዝ ለብዙ ችግሮቻችን ሰበብ የሆነ አይመስላችሁም!?
ኮንዶሚኒየም..
አንድ፡— ስማ፣ ጎረቤትህ ያለው ሰውዬ ሥራው ምንድነው?
ሁለት፡— እየው ሥራው ምን ይሁን ምን ለማወቅ መጀመሪያ እኔ ጎረቤት እንዳለኝ ማወቅ ያለብኝ አይመስልህም!
አንድ፡— እስከ ዛሬ!
ሁለት፡— አዎ፡፡
አንድ፡— ጎን ለጎን ስትኖሩ ሁለት፣ ሦስት ዓመት አይሆናችሁም!
ሁለት፡— አራት ዓመት ሊጠጋን ነው፡፡ ግን ሳስበው የሆነ ወንደላጤ ነገር መሰለኝ፡፡
አንድ፡— እንግዲያው እኔ ምን እንደሆነ እነግርሀለሁ...
ሁለት፡— ቆይ እኔ አንድ ግድግዳ የሚለየን ሰውዬ ያላወቅሁትን አንተ ከሰፈርህ በሦስት ታክሲ አቆራርጠህ መጥተህ እንዴት አወቅህ?
አንድ፡— እሱ ምንም አያደርግልህም፡፡ ይልቅ ስማኝ፣ ቁርጥህን እወቅ፡፡ ጎረቤትህ የሆነ ፖለቲካ ድርጅት አመራር ነው አሉ፡፡
ሁለት፡— አትለኝም! ምን የሚሉት ፖለቲካ ፓርቲ ነው የሚመራው?
አንድ፡— እንትን የሚባል...
ሁለት፡— ምን! ጄሰስ ክራይስት! ይህን ሁሉ ጊዜ ዋነኛ ጠላቴ ጎኔ ነበር!
እናላችሁ... ጎናችሁ ያለው በር ዘግቶ፣ እናንተ በር ዘግታችሁ ነገ እኮ “ጎን ለጎን ተከራይታችሁ ትኖሩ የነበረው ዋነኛ ዳፋችን ነው" የሚል ሊመጣባችሁ ይችላል፡፡
ወይ ደግሞ...
አንድ፡— ያቺ ጎረቤትሽ እንዴት እንዴት ነው የሚያደርጋት? ሙሉ የሽቶ ብልቃጡን ቸልሳው ነው እንዴ የምትወጣው!
ሁለት፡— እባክሽ ነገሩ ወደዚህ ነው፡፡ ከቢሮ ሰዓት ውጪ ሌላም ሥራ ትሠራለች አሉ፡፡
አንድ፡— ምን አይነት ሥራ?
ሁለት፡— ምን አይነት እንድልሽ ፈለግሽ... ቡና ለቀማ ልልሽ ነው!
አንድ፡— ነው እንዴ!
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ዘንድሮ ያው የትዳር ያህል ፍቺም በዝቷል ይባል የለ፡፡ እናማ... የብዙዎቹ ምክንያት ‘እንትን ነገር’ ላይ ነው ይባላል፡፡ ግን ደግሞ አሁን እኮ ጊዜ ተለውጧል፡፡
ያን ጊዜ...
ባል፡— አንቺ ሴትዮ እስካሁን የት አምሽተሽ ነው? (ገና አስራ ሁለት ተኩል ነው እኮ!)
ሚስት፡— ለቅሶ ቤት የሴት እድር ሥራ ስንሠራ ነው፡፡
ባል፡— የሴት እድር! ይህን ያህል ሞኝ አደረግሽኝ እንዴ! የማላውቅ መሰለሽ!
ሚስት፡— ም..ምንድነው የምታውቀው?
ባል፡— የሴት እድር ሥራ እያላችሁ በለቅሶ ቤት ሰበብ የምትሠሩትን የምታመሹበትን የማላውቅ መሰለሽ!?
ሚስት፡—ምን አደረግን?...
ባል፡— በቃ!... አሁን ወሬ አልፈልግም። ከዛሬ ጀምሮ ከዚች ቤት ውልፍት እላለሁ ብትይ ዶሮ ጠባቂ ነው የማደርግሽ! ገባሽ?
ጭጭ፡፡
እና ደግሞ ዛሬ... (ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ‘ከች’ ይባላል፡፡)
ባል፡— አመሸሽ...
ሚስት፡— መቼ መሸ... ገና አራት ሰዓት እንኳን መች ሞላ?
ባል፡— ግን በደህና ነው?
ሚስት፡— ከጓደኞቼ ጋር ስንዝናና ቆይተን ነው፡፡
ባል፡— ስሚ ግን ይህን ማምሸት የሚሉትን ነገር ካልተውሽ... (በስህተት የተጀመረ ንግግር!)
ሚስት፡— ሁዋት! ጭራሽ አራት ሰዓት ሳይሞላ ምሽት ሆነና መቆጣት ተጀመረ ማለት ነው! (ዲሞክራሲ ለዘለዓለም ይኑር! ቂ...ቂ...ቂ...)
የምር ግን የትናንት የጉርብትና ማህበራዊ እሴታችን ከእነ ምናምኑ ውል ቢለንም አይገርምም፡፡ አለ አይደል.. እንዲህ ሲወጡ መቆለፍ፣ ሲገቡ መቆለፍ ከሆነ ኑሮ፣ ዛሬ “ንፍሮ በተንሽብኝ”፤ ነገ “ስንዴ አበድሪኝ፣” ሳይሻል አይቀርም፡፡  
 ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2007 times