Wednesday, 13 January 2021 19:20

ጐንደር ዩኒቨርሲቲ - ኮቪድና ሁለገብ እንቅስቃሴው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ኮቪድ ለፈጠራ ሥራዎች አነሳስቷል እስከ 2.ኪ.ግ ክብድት መሸከም የሚችል ድሮን ሰርተናል ዩኒቨርስቲው በኮቪድ መሃል ሆኖ ያከናወናቸው ተግባራት

            ጎንደር ዩኒቨርስቲ ባለፉት 6 አስርት ዓመታት በመማር ማሳተማር ሂደቱ፣በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎቱ ከፍተኛ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አሁንም እየሰራ ይገኛል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ሰሞኑን ለስራ ወደ ጎንደር ባቀናችበት ወቅት ዩኒቨርስቲው በኮቪድ ላይ ስለ ሰራቸው ጥናትና ምርምሮች፣ ሰሞኑን በክልሉ ጤና ቢሮ ስላገኘው እውቅና፣ በጎርጎራ ስላለው የጤናና የግብርና ጥምር የምርምር ማዕከሉ፣ በጤናው ዘርፍ እያደረገ ስላለው አበርክቶ፣ በመጪው ሳምንት ስለሚከበረው የጥምቀት በዓልና በተያያዝ ጉዳዮች ዙሪያ ከዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደ ወይን (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች እነሆ፡-

               በኮቪድ 19 ምክንያት ትምህርት ተዘግቶ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ ጥንቃቄ እየተደረገ ትምህርት እንዲቀጥል ከተደረገ በኋላ በዩኒቨርስቲያችሁ የመማር ማስተማር ሂደቱ ምን ይመስላል?
ኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ከተከሰተ ጀምሮ ለተማሪዎች ወረርሽኙን በተመለከተ በወቅቱ በነበረው ግንዛቤ ልክ እንዲያውቁና ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ትራንስፖርት አመቻችተን ወደ ቤተሰቦቻቸው የመሸኘት ስራ ሰርተናል። ከዛም በኋላ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ማለትም የማስተርስና የፒኤችዲ ፕሮግራሞቻችንን ቴክኖሎጂን በመጠቀም መማር ማስተማሩ እንዲቀጥል አድርገን፣ በሀገራችን የመጀመሪያው የሆነውን የበይነ መረብ የተማሪዎች የምረቃ ስነ-ስርዓት በኦንላይን  ሀምሌ 4 አካሂደናል። ይሄ  ደግሞ  በሀገራችን የመጀመሪያው ያደርገናል። ጊዜው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በማስተማር፣ በሽታውን ታሳቢ ያደረገና ርቀትን በጠበቀ መልኩ የተከወነ ሆኖ፣ ምረቃውም በዩኒቨርሲቲው ግቢ በተለያየ ቦታ በተሰቀሉ ስክሪኖች አማካኝነት፣ የተመራቂ ቤተሰቦችም በያሉበት ሆነው በተናጠል እንዲከታተሉ በማድሪግ የተሳካ የምረቃ ስነ-ስርዐት አካሂደናል።
ኮቪድን በተመለከተም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ለማህበረሰቡ ተሰርቷል። የትምህርትና ግንዛቤ ፈጠራ ግብረ ሃይል ከተለያዩ የትምህርት ባለሙያዎች ማለትም፡- ከኮሙኒኬሽና፣ ከጤና ባለሙያዎች የተውጣጣ ግብረሃይል ነበር የተቋቋመው። እናም በተለያዩ ሚዲያዎች፣ (ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ ማለቴ ነው ባለሙያዎቹ እየቀረቡ ግንዛቤ የመስጠትና ማህበረሰቡን የማንቃት ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በወረርሽኙ ምክንያት ኢኮኖሚያቸው የተጎዳባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በመደገፍ እገዛ አድርገናል። ይህን ድጋፍ ስናደርግ በዩኒቨርሲቲው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በግሉ ከደሞዙ ገንዘብ በማዋጣት፣ ለህፃናትና አረጋውያን መርጃ ማዕከላት፣ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የገንዘብ ችግር ላለባቸው አረጋውያን ከክፍለ ከተሞቹ አመራሮች ጋር በመሆን በርካታ ድጋፎች አድርገናል። ሀብት በማፈላለግ ረገድም፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አለም አቀፍም አገር አቀፋዊም ችግር በመሆኑ፣ ለመንግስት ብቻ የምንተወው ጉዳይ አይደለም በማለት በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ሰፊ ድጋፍ አድርገዋል።  ይህን ሀብት በማሰባሰብ በኩል በተደረገ ከፍተኛ ጥረት በበርካታ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ፣ የተለያዩ በሽታውን ለመከላከል የሚያግዙ ግብአቶች ከአገር ውስጥም ከውጪም በስፋት  ተልከውልናል። የ“Go Fund Me” አካውንት በመክፈትም ገንዘብ በመሰብሰብ እጥረት የታየባቸው ግብአቶች  እንዲሟሉ  አድርገናል። በዚህ አጋጣሚም በድጋፉ የተባበሩ በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት በአገር ውስጥም በውጪም ነበሩ፤ አሉም፡፡ እነሱን እጅግ አድርጌ ማመስገን እወዳለሁ።
ከዚያ ባሻገር መማር ማስተማሩ መቀጠል አለበት፡፡ ለዚህም የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ ነበረብን። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር ባስቀመጧቸው አቅጣጫዎች የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን መነሻ በማድረግ፣ በሽታውን እየተከላከሉ መማር ማስተማሩን ማስቀጠል አንደኛውና ዋነኛው ጉዳይ በመሆኑ ሰፊ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል።
ከዝግጅቶቻችን መካከል አንዱ በፔዳል የሚሰራ የእጅ መታጠቢያ፣ ተማሪዎች ወደ መመገቢያ አዳራሽ መጥተው ሲሰለፉ ርቀታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ምልክት የመስራት ስራ፣ ወንበርና ጠረጴዛ ተራርቆ እንዲቀመጥ ማድረግ፣ በቤተ መፃህፍትና በክፍል ውስጥም ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲማሩና እንዲያጠኑ የሚያስችል ዝግጅት አድርገን በዚሁ መሰረት ተማሪዎቻችንን ተቀብለን፣ በጥሩ ሁኔታ መማር ማስተማሩ እየቀጠለ ይገኛል።
በቀጣይ ጥር 15 ቀን በዚህ ሂደት ያለፉና በ2012 ዓ.ም መመረቅ የነበረባቸው የቅድመ ምረቃ ተመራቂ ተማሪዎቻችንን እንዲሁ ጥንቃቄ በተሞላበትና በፕሮቶኮሉ መሰረት እናስመርቃለን። ይህንን ለማድረግ በርካታ አካላት በብዙ መልኩ የደገፉን ቢሆንም፣ የጤና ባለሙያዎቻችንና ሀኪሞቻችን ከምንጊዜውም በላይ ሰፊ  ርብርብ በማድረግ፣ ሙያዊ ግዴታቸውን የተወጡበት ጊዜ ስለሆነ ለእነሱ ታላቅ ክብርና ምስጋና አለኝ። በበሽታው ብቻም አይደለም፤ አሁን በሀገራችን እየተካሄደ ባለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ፤ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሙያዊና የጤና ስነ-ምግባሩ የሚጠይቀውን ግዴታችንን በተገቢው መንገድ በማስተማሪያ ሆስፒታላችን ተወጥተናል፤ እየተወጣንም እንገኛለን፡፡
በዚህ ጉዳይ ጥቂት ማብራሪያ ቢሰጡን….?
በዚህ ሂደትም የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ እንዲሁም የአገር መከላከያ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን ቆስለው የሚማረኩ የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻዎችን በእኩልነት አስተናግደናል። የሙያ ስነ-ምግባሩም የሚጠይቀውን ህክምና እኩል በመስጠት ሙያዊ ሃላፊነታችንን ተወጥተናል። በዚያኛው ወገን ሆነው ሲዋጉ የነበሩትም በጥሩ ሁኔታ ታክመው ነው የወጡት። ለዚህ ስራ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ባጠቃላይ፣ የጤና ባለሙያውና ሃኪሞች በተለይ ያደረጉት ርብርብ በጣም የሚደንቅና የሚያኮራ ብሎም ታሪክ የማይረሳው ነውና በእጅጉ ኮርቼባቸዋለሁ፤ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።
በሌላ በኩል፤ የጎንደር ከተማ በጎ አድራጊ ወጣቶችም እንዲሁ ይሰሩት የነበረው ስራ በጣም የሚያኮራ የሚደንቅ ነው፡፤ ሙሉ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን በመስጠት በጦርነቱ ምክንያት ቆስለው ለገቡ የመከላከያና የልዩ ሀይል አባላትም ሆነ ቆስለው ለተማረኩ የህወሃት ወታደሮች በእኩልነት ምግብ  በማቅረብ፣ ልብስ በማልበስ፣ ፀጉራቸውን በመቁረጥ በማጠብና መሰል ሰብአዊ ድጋፎች  ሲሰጡ ነው የቆዩት። ይህም ትልቅ ስኬት ነው ብለን መውሰድ እንችላለን።
አሁን ምን ያህል ተማሪዎች ናቸው በትምህርት ገበታ ላይ ያሉት?
በአሁኑ ሰዓት እየተማሩ የሚገኙት  ከ5 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎች ናቸው። ጥር 15 ላይም ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እናስመርቃለን ማለት ነው።
ጎንደር ዩኒቨርስቲ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዙሪያ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን የተለያዩ ፈጠራዎችን ማውጣት መቻሉን ሰምቻለሁ፡፡ ሰሞኑን ከክልሉ ጤና ቢሮ እውቅናና ሽልማት ያገኛችሁት በዚሁ ጉዳይ ነው?
ኮቪድን በተመለከተ እንዳልሽው፤ እጅግ በርካታ የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል። ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፤ አንዱ ተግባር የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን በበይነ መረብ በተሳካ ሁኔታ ማስመረቃችን ነው። ከዚያ ባለፈ ኮቪድን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ምርምሮችን ማካሄድ አንዱና ትልቁ ስራችን ነበር። ከዚህ አኳያ ከ10 ሚ. ብር በላይ በልዩ ሁኔታ በመበጀት ጥናትና ምርምሮች እስካሁንም እየተካሄዱ ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም። ኮቪድን እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ከምናይበት ምክንያቶች አንዱ ፈጠራዎችን ማበረታታቱ ሲሆን፤ አንድነታችንንም አጠናክሯል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን በችግር ወቅት ምንጊዜም አንድ ነን። ጠላትም ሆነ ሌላ ችግር ሲመጣ አንድ ሆነን የምንቆምበት ሁኔታ እጅግ  የሚያስደስት ነው። የማህበረሰብ አገልግሎቶቻችን በጣም ሰፊ ነበሩ። ከዚያ በተጨማሪም ኮቪድን ለመከላከል ከተሰሩት መካከል “IV Stand” የተሰኘው የጉሉኮስ መስቀያ ተጠቃሹ ሲሆን ሆስፒታላችን በሚፈልገው መጠን በእኛው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራንና ተማሪዎች ሰርቷል።
ሜካኒካል ቬንትሌተር አንዱ ከሰራነው የፈጠራ ስራ ይጠቀሳል። ይሄ እጅግ ዘመናዊ የሆነው ቬንትሌተር በእኛው ነው የተሰራው። ኮቪድ 19 አንዱ የሚያጠቃው የመተንፈሻ አካልን በመሆኑ ለመተንፈስ የሚያግዝ መሳሪያ ያስፈልገናልና፡፡ ይሄንን ለማድረግ የሚያስችል ማሽን ተሰርቷል። ማሽኑን ከርቀት ለመቆጣጠር ከህመምተኛ ጋር ማገናኘት የሚያስችል አሰራርም ነው የተፈጠረለት። ሀኪሙ በአንድሮይድ ስልኩ በርቀት ሆኖ የታማሚውን አተነፋፈስና የተለያዩ ሂደቶችን መከታተል ያስችለዋል። ታማሚው ድጋፍም ካስፈለገው ሄደው ያስተካክሉታል። ድጋፍ የማይፈልግ ከሆነም በርቀት ሆኖ ስራውን እንዲሰራ የሚያስችል ፈጠራ ነው። የሀኪሙን ተጋላጭነትም የሚቀንስ ነው። አንድን ሜካኒካል ቬንትሌተር ለሁለት ታማሚ ማስጠቀም የሚችልም ስፒሊተር (የሚከፍል) ፈጠራ ተሰርቷል።
ሌላም ከንክኪ ውጪ የመኪናንም ሆነ የቤትን ወይም፣ የቢሮን በር  ለመክፈት የሚያስችል ፈጠራም ሰርተናል። ሰው በጫማው ቫይረሱን ይዞ ከውጪ እንዳይገባ በር ላይ ዲስኢንፌክት ማድረጊያዎችም ተሰርተዋል።
እጅግ የሚገርመው ፈጠራችን ደግሞ እስከ 2 ኪ.ግ ክብደት ያለው እቃ መሸከምና ወደሚፈለገው ቦታ ማድረስም ሆነ ማምጣት የሚችል ድሮን ነው። በዚህ ድሮን ወደ ታማሚው ምግብ ወይም መድሃኒት ልንልክ እንችላለን፣ ታማሚው ደግሞ የተጠቀመበትን መገልገያ  ወደ እኛ መላክ ይችላል፡፡  ስለዚህ ይህንን ድሮን በርቀት እየተቆጣጠሩ በታማሚው መስኮት በኩል  የሚፈለገውን እቃ መላክ፣ከዛም ወደኛ ማምጣት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተሰርቷል።  ይህና መሰል ተግባራት የሚያሳዩት ኮቪድ 19 ለፈጠራ ማነሳሳቱን ነው።
የመምህራንንና ተማሪዎቻችንን አቅም አይተንበታል። በችግር ጊዜ ብቻም ሳይሆን በሰላም ጊዜም ለችግር መፍትሄ ጥረት ብናደርግ አቅም እንዳለ ያየንበት ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ እንደ ትልቅ ነገር ሊጠቀስ ይችላል፡፤ በሌላ በኩል፤ በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታላችን ሊታከሙ የሚመጡ  አሉ፡፡ በለይቶ ማቆያነትም በተለያዩ  ግቢዎች ስንጠቀም ነበረ። ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ለሰሜን ጎንደር ዞን፣ ለምዕራብም ሆነ ለምስራቅ ጎንደር ዞን መታከሚያ የእኛ ሆስፒታል ነበር። በኋላ ለይቶ ማቆያ፤ በተለይ በሱዳን በኩል የሚገቡ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ነበሩ፡፡ ከመሃል አገርም ከሌሎችም አካባቢዎች፡- ከኦሮሚያ፣ ከደቡብም ከጋምቤላም ከአብዛኛው የአማራ ክልልም የሄዱና ከሱዳን የሚመለሱ ነበሩ። እነዚህ ወገኖች ይመጣሉ። ምዕራብ ጎንደር ዞን ላይ ማቆያ ይገባሉ፡፡ እነሱ ሲቆዩ የሚያስፈልጋቸው የምግብ፣ የመኝታ ፣ የሙቀት ልየታ መሳሪያና በኋላ ደግሞ ከማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን PCR ማሽን በመስጠት ምርመራው እዛው እንዲጀመር የማድረግ ስራም ሰርተናል። ከድንበር ወደ ምዕራብ ጎንደር የሚያመላልስ የትራንስፖርት ችግርም ስለነበራቸው፣ በቋሚነት አውቶብስ በመስጠት፣ ለምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ድጋፍ አድርገናል። የነበረው ጫና ቀላል አልነበረም፤ ሆኖም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ የዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች፣  የክልልና የፌደራል ቅንጅት ጥሩ ስለነበር፣ አብዛኛውን ችግር አልፈነዋል የሚል እምነት አለኝ።
አሁንም ቢሆን ግን ችግሩ አለ። ህመሙ አሁንም በስፋት እየታየ ነው፡፡ በአንፃሩ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት ይታያል፡፡  ይሄ ችግር ስለሆነ በቀጣይ ብዙ ስራ ይጠይቀናል። በተለይ ክትባቱ አገራችን ገብቶ ሁሉም አገልግሎቱን እስከሚያገኝ ድረስ ከፍተኛ ስራ ይጠይቀናል።  ዩኒቨርስቲያችን ቫይረሱን በመከላከል፣ በምርምርና በፈጠራ ስራ፣ ማህበረሰቡን በመደገፍ፣ በዩኒቨርስቲ ሆስፒታላችን በህግ ማስከበሩ ሂደት ለተጎዱ ወገኖች አስፈላጊውን ህክምና በማድረግ አገራዊና ወገናዊ ግዴታን ከመወጣት አኳያ በጣም ሰፋፊ ስራዎችን ሰርተናል። ለዚህም ነው በኮሮና ቫይረስ መከላከል ጉልህ አስተዋፅኦ  ያደረጉ የተለያዩ አካላት በክልሉ ጤና ቢሮ እውቅና የተሰጣቸው። በዚህም ዩኒቨርስቲያችን በቅድሚያ ከተሸለሙና እውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ ሊሆን በቅቷል።
በተለይ ከኮቪድ  በፊት ሀገሪቱ በአብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ አለመረጋጋትና ረብሻ በነበረበት ወቅት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጀመረውና በእጅጉ የተወሰደበት ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎን ከጎንደር ቤተሰብ ጋር የማገናኘት ፕሮጀክት ነበር። ይሄ ፕሮጀክት በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው?
ትክክል ነሽ!     “የጎንደር የቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክት” እንደቀላል ቢጀመርም ያገኘነው ምላሽ እጅግ እጅግ የሚያበረታታና ከጠበቅነው በላይ መልካም ግብረ መልስ ያገኘንበት ፕሮጀክት ነው። ወደፊትም አጠናክሮ ለመቀጠልና የአንድ ወቅት ስራ እንዳይሆን በማሰብ የራሱን የማስተባበሪያ ፅ/ቤት ከፍተንለታል። ይሄ ማለት ፕሮጀክቱ ራሱን የቻለ ባለቤት ኖሮት ቀጣይነት እንዲኖረው ተቋማዊ አሰራር ዘርግተንለታል። ስለዚህ “የጎንደር የቃልኪዳን ቤተሰብ ጽ/ቤት” የሚል ጽ/ቤት ከፍተንለት ይህ ቢሮ አጠቃላይ ሂደቱን እየተከታተለ ባለፉት ዓመታት የጀመርናቸውን ቃልየ ኪዳን ቤተሰብ የማገናኘት ስራዎች በምን ሁኔታ ላይ ነው የሉት? በቀጣይ አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎቻችን የቤተሰብ ባንክ የመያዝ ሁኔታው እንዴት በስፋት ይቀጥል የሚለውን እየሰራን ነው። አየሽ ተማሪዎቹን የፈለገ ሰው ስለፈለገ ብቻ አይወስድም።
ለምን?
ይሄ ማለት  ምን ማለት ነው… አንድ ሰው የቃልኪዳን ቤተሰብ ሆኖ ተማሪ ለመውሰድ ፍላጎት ሊኖረው ይችላል። ፍላጎቱ ብቻ በቂ አይደለም፤ በፕሮጀክታችን ስር የተቀመጡ መስፈርቶች ግን አሉ። አንደኛ ይህን የቃልኪዳን ቤተሰብነት ሊሸከም የሚችል ሰብዕና ሊኖረው ይገባል። ሁለተኛው ባለትዳሮች መሆን አለባቸው። ሌላው በአካባቢው የሚታወቁ፣ በማህበራዊ ሃላፊነት የተመሰገኑ፣ የራሳቸውን ቤተሰብ የመሰረቱ መሆን አለባቸው። ይህንን መስፈርት የሚያሟሉ ቤተሰቦችን በመመልመል፣ የቤተሰብ ባንክ የመያዝ ስራ በዚሁ ጽ/ቤት ይሰራል ማለት ነው። ጽ/ቤቱ ደግሞ ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ጋር በመቀናጀት የሚሰራ ሲሆን ከከንቲባ ጽ/ቤት ለዚሁ ስራ የተመረጡ ሰዎች አሉ። የምልመላ ሂደቱም በዚህ መልኩ ይካሄዳል። የኛ የፕሮጀክቱ ጽ/ቤት ያስተባብራል። ይህንን ፕሮጀክት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ ብራንድ (መለያ) አድርገን ነው የምንወስደው። ፕሮጀክቱ በእኛ ዩኒቨርስቲ ብቻ እንዲወሰን አንፈልግም። ሌሎች አቻ ተቋማትም እንዲተገብሩት የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን። በአሁን ወቅት በአገራችን  ከብሄር፣ ከጎጥና መሰል አስተሳሰቦች እንድንወጣ የሚያግዝ ስለሆነ ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች ቢተገብሩት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። እስካሁን የእኛን ልምድ ያካፈልናቸውም አሉ።
እርስዎም ሁለት ተማሪዎችን የቃልኪዳን ቤተሰብ ሆነው ወስደው ነበር። ት/ቤት በተዘጋ ጊዜም ሆነ አሁን ግንኙነታችሁ እንዴት ነው?
ትክክል ነው። ሁለት ተማሪዎች ወስጃለሁ። አሁንም ግንኙነታችን የጠበቀ ነው። አንደኛ ዓመት ስለሆኑ አሁን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ነው ያሉት። ሲመጡ እኔ ጋር ያርፉና ከልጆቼ ከቤተሰቤ ጋ ተጫውተው እረፍት አድርገው ነው ትምህርት የሚጀምሩት። ወደ ቤተሰባቸው ሲሄዱም በዚያ መንገድ ነው የሄዱት። እናም ግንኙነታችን አሁንም አልተቋረጠም፤ ወደፊትም ይቀጥላል። ሌላውም ቤተሰብ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማረጋገጥ ሞክሬ ነበር፤ አሁንም ይገናኛሉ። ሲሄዱ የአውሮፕላን ትኬት ቆርጦ የላከ አለ። በአውቶቡስም የላከ አለ። ሁሉምእንደየአቅሙ ለቃል ኪዳን ልጁ አድርጓል። አንቺም ለልጅሽም ቢሆን የምትችይውን ነው የምታደርጊው አይደለም?! ስለዚህ እንደ አቅሙ እያደረገ ነው። ወደፊትም ይቀጥላል። ይህ ባህልን፣ ቋንቋን እሴትን ከመለዋወጥና ይበልጥ ከመተዋወቅም አንፃር ብናየው አትራፊ ግንኙነት ነውና እንደ አገርም ልናስብበትና ልንተገብረው የሚገባ ጉዳይ ነው። በዚህ መንገድ ኢትዮጵያዊነት እንደገና እንዲያብብና እንዲለመልም የምናደርግበት መንገድ መሆን ይችላል።
ሰሞኑን ጎርጎራ ወደሚገኘው የጤናና የግብርና ጥናትና የምርምር ማዕከላችሁ ጎራ ብለን ጎብኝት አድርገን ነበር። በተለይ ለጎርጎራ ከተማ ነዋሪ ብቸኛው ጤና ጣቢያችሁ እየሰራ ያለውን ስራና በግብርናውም ለአርሶ አደሩ የምታደርጉትን ድጋፍ ተመልክተናል።  ሆኖም በተለይ ጤና ጣቢያችሁ ብዙ መሟላት ያለባቸው ነገሮች  ባሉበት በጫና ውስጥ እንደሚሰራ ነው የነገሩን። እስኪ በግብርናውም በጤናውም ዘርፍ ጎርጎራ ላይ ስለምታከናውኑት ስራችሁ ከእርስዎ እንስማ?
እውነቱን ለመናገር ጎርጎራ ላይ ታሪኳን፣ ቅርሷንና የተፈጥሮ ሀብቷን በሚመጥን ልክ የተሰራ ነገር የለም። እዚያ አካባቢ ላይ ብዙ መስራት ይቻል ነበር ግን አልተሰራም ማለት ይቀላል። በአንፃሩ ደግሞ  እስከዛሬ ያጣችውና የዘገየባትን ሊያካክስ የሚችልና ታሪኳን ሊመጥን የሚችል ነው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የሚል እምነት አለኝ። ይህንን ፕሮጀክት መፈቀድ ተከትሎ ብዙ መነቃቃት እየታየ ነው። ባለሀብቱም ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እያሳየ ነው።  ሌሎችም ፕሮጀክቱን ተከትለው እየመጡ ያሉ አድሎች አሉ። ስለዚህ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የጎርጎራን መለወጥ እኛም ከውበቷ ከተፈጥሮ ሀብቷ ጋር የሚገባንን እድል የማየት ጊዜው  እየተቃረበ ይመስለኛል።
እንደ ጎንደር ዩቨርሲቲ እስካሁን ሁለት ትልልቅ ነገሮችን ሰርተናል ማለት እችላለሁ። አንደኛው ግብርና ነው። ይህ የግብርና ኮሌጃችንን እንደ ቤተ-ሙከራ ነው የምንጠቀምበት። በተለይ የድህረ ምረቃ ተማሪዎቻችን ለእነሱ ላብ ነው። እናም እዛ ሄደው ይመራመራሉ ከሌላ አካባቢ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እያመጡ ያለምዳሉ። አርሶ አደሩን ያሰለጥናሉ። አርሶ አደሩ ስልጠና ወስዶ ወደ ትግበራ እንዲገባ ያደርጋሉ። የገበያ ትስስርም ይፈጥራሉ። ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ከጐርጐራ የገበታ  ለሀገር ፕሮጀክት መፈቀድ ጋር ተያይዞ የጤና አገልግሎቱ መስፋፋት ስላለበት ክሊኒካችንን ወደ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የማሳደግ እቅድ አለ። ለወጣቱም የስራ እድል በመፍጠር ብዙ እየሰራን እንገኛለን።
በቀጣዩ ሳምንት ለሚከበረው ደማቁ የጥምቀት በዓል የዩኒቨርስቲችሁ ድርሻ ምንድን ነው?
ጥምቀት በጎንደር ሃይማኖታዊ በዓል ብቻ አይደለም። የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ጭምር ነው። ስለዚህ ጥምቀት በጎንደር ሲከበር ብዙ ተቋማዊ ስራዎች ይጠበቁብናል። በዋናነት እዚህ ከተማ ውስጥ ያለው ብቸኛው ሆስፒታል የዩኒቨርስቲው ሆስፒታል ነው። የሆስፒታል አገልግሎታችን ለድንገተኛ ህክምና በደንብ ዝግጅት ማድረግ አለበት። ባለፈው ዓመት እንደምታስታውሽው፤ ያ አሳዛኝ ክስተት ሲፈጠር ሆስፒታሉ ከፍተኛ ርብርብ በማድግ የበርካታ ወገኖችን ህይወት ለማትረፍ ተችሏል። እንዲህ አይነት ሰው በብዛት የሚኖርባቸው ዝግጅቶች ሲሰናዱ በተለይም ጥምቀት ሲኖር የህክምና ግብአቶቻችንን በማሟላት፣ ባለሙያዎችን ዝግጁ እናደርጋለን። ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ዜጎችም ስላሉ የኢትዮጵያን ብሎም የጎንደርን መልካም ገፅታ እንዳያጠለሽ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር የተለያዩ ዝግጅቶችንና እገዛዎችን እናደርጋን። የባለፈው ዓመት ችግር እንዳይከሰትም ርብራቡን በመስራትና በማማከር በኩል የእኛ የምህንድስና ባለሞያዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ሙያዊ እገዛም እያደረግን እንገኛለን።
ከዚህ በተጨማሪ ጥምቀት የሃይማኖትም፣ የባህልም የታሪክም መገለጫ እንደመሆኑ በጥናትና በምርምርም በኩል የቱሪዝም የትምህርት ክፍላችንና የታሪክና ቅርስ አስተዳደር፣ አንትሮፖሎጂና ከዚህ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሙያዎችን አብረው በዚህ በኩል እንዲያጠኑና እንዲያግዙ እየሰራን ነው የምንገኘው። ስለዚህ ከተራ ፣ ጥምቀትና ቃና ዘገሊላ ሶስቱ ቀናት በሰላምና በድምቀት ተከብረው፣ ታዳሚዎቹም ተደስተው እንዲመለሱ ዩኒቨርስቲያችን የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል ማለት ነው። በዚህ አጋጣሚ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ጥምቀትን በጎንደር በደስታ እንዲያሳልፉና በቀጣይ ቀናት ያለውን የተማሪዎቻችንን ምርቃት እንዲታደሙ እጋብዛለሁ። አመሰግናለሁ።

Read 706 times