Thursday, 14 January 2021 11:45

የወመዘክሩ የግድግዳ ስዕል

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(2 votes)

 ከባለታሪኩ ጋር የተገናኘነው ድንገት ነው፤ በአጋጣሚ፡፡ እኔ እዚሁ ሰፈር  ስጠጣ አምሽቼ አከራዮቼ በሩን ስለዘጉብኝና የማደሪያ ገንዘብ ስላልነበረኝ አንዱ ፌርማታ ጋደም ስል፣ እሱም እዚያው ተጋድሞ ወደ ሰማይ ሲያንጋጥጥ አገኘሁት፡፡ እንግዲህ ሁለት ሰካራሞች ማደሪያ አጥተው ፌርማታ ሲጋደሙ ሊያወሩት የሚችሉት ነገር ምን ሊሆን እንደሚችል ማንም ሰው ይገምታል።
“ብሮ.. ሲጋራ ይዘሃል?” የመጀመሪያውን ጥያቄ ሰነዘርኩኝ።
“አላጨስም”
“የት ይሸጣል?”
“ሰፈሬ አይደለም… አላውቅም”
“ሰፈርህ የት ነው?”
“አላውቀውም”’
ይሄስ የባሰበት በጬ ነው አልኩና፤
“ሙድ ትይዛለህ እንዴ!?”
“ኡነቴን ነው፤ ጠፍቶብኝ ነው”
“እንዴት?”
“ጀሞ እንደሆነ አውቃለሁ። ግን መንገድ ጠፋብኝ”
“ጊዜው አደገኛ ነው። ዛፓዎቹ እንዳይዠልጡን እግዜር ይጠብቀን።”
“ጁንታው ያልቅለታል… እያጠፋነው ነው!”
“ማናችሁ እናንተ?”
“የሰማይ ጦር!”
እንዲህ አይነት መደበሪያ ሰው በማግኘቴ ፈጣሪዬን እያመሰገንኩኝ፤
“በምንድነው የምታጠፉት?”
“የተራቀቀ መሳሪያ አለን፤ ከፈለግን ምድሩን ሁሉ ልንደመስስ እንችላለን”
“ኧረ ባክህ?! አንተም ከዚያ ነው የመጣኸው? ከሰማይ?” የነበረችኝን ግማሽ ቁሮ ሲጋራ እየለኮስኩኝ፡፡
“የኔን አላውቅም፤ እነሱ ግን ከዚያ ናቸው”
“ማናቸው እነሱ?”
“የኔ ጓደኞች”
“ማለት ምንድናቸው?
“አላውቅም፡፡ ወይ መልአክት ወይ ኤልያን”
“ኤልያን?”
“የሌላ አለም ሰዎች….. በጣም የሰለጠኑ…. በጣም የሚያምሩ… በጣም ግዙፎች…. በጣም ሃይለኛ…..”
“እንዴት ነው የተዋወቃችሁት… ማለቴ እንዴት መጡ?”
“አንዲት ጓደኛ ነበረችኝ…ሁሌ በኔ ላይ የምትጫወት፡፡ ገንዘብህ ሲያልቅ ልመና ትጀምራለህ እያለች ታሟርታለች፡፡ በዚያ ላይ የትም የምትንዘላዘል። እንዳለችው ገንዘቤ ሲያልቅ አፍንጫህን ላስ ብላኝ ዓይኔ እያየ ከሌላ ወንድ ጋር ጥላኝ ሄደች፡፡ ያን ሌሊት አምርሬ አለቀስኩኝ”
“እሺ”
 አሁን ነገሩ እውነት መሆን ጀመረ።
“ወዲያው እኩለ ሌሊት ላይ በጣም የምታምር፣ ወርቃማ ፀጉር ያላት፣ ረጅም ቆንጆ ሴት መጣች። ስሟን ልነግርህ አልፈልግም”
“በአካል?”
“አያታለሁ ታናግረኛለች፤ ረቂቅ ናት ጠጣር አይደለችም፤ ሁሉም ሰው ያያታል፤እሷን ለማየት ሁሉም ሰው ይሰባሰባል”
“ከዚያስ?”
“ከዚያ ደግሞ ሌሎቹ መጡ። በሌላም አገር ያሉ ሰዎች….. የአለም ዝነኞች በሙሉ ከኔ ጋር ናቸው። ሃይለኞቹ… ተቃራኒዎቹ ደግሞ…;
“እነሱስ ማናቸው?”
“እኔን ይዋጉኛል። የምወዳቸውን ይዋጋሉ። ስለዚህ ጁንታው አንዱ ነው”
“ጁንታው እኮ የወያኔ ጦር ነው”
“እኮ! በነዚያ በኔ ጠላቶች በእርኩሶቹ ይደገፋል”
“ያንተስ ሰዎች?”
“መከላከያን ይደግፋሉ”
“ስለዚህ?”
“ቀጠቀጥናቸው!”
“በምን?”
“በሚሳኤል… በብዙ ሃይል”
“የታለ  ሚሳኤሉ?”
“ስልኬ ውስጥ…. ከዚያ በማዳመጫ እየሰማሁ አፈር አበላቸዋለሁ”
“እንዴት?”
“እኔ የምሰማውን ሁሉም ይሰማል፤ የማየውን ያያል፤ የማደርገው ይሆናል”
ይሄስ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው አልኩኝ-- በልቤ።
“ሴቶቹ ምንድናቸው?”
“ሚስቶቼ ናቸው”
“አሁን ጁንታው ተመቷል ነው የምትለው?”
“እኛ አጋንንቶችን ስንቀጠቅጥ መከላከያ ጁንታውን ይመታል፡፡ ዛሬ አጥርተነዋል”
“ሰክረሃል?”
“ምን ይገርማል! ለዚያ ነው ሰፈሬ የጠፋብኝ፤ በጠዋት አገኘዋለሁ”
“ከየት ነው የመጣችው ልጅቷ?
“እዚሁ ናት ዋናዋ… እዚህ ምድር…”
“ሌሎቹስ?”
“ከተለያየ ፕላኔት…. ለምሳሌ አንዷ ከሜጋ…”
ሁለት ፖሊሶች መጡና “ስማ ተንቀሳቀስ!” ሲሉን በርግገን ተነሳን፡፡  እኔ አስፋልቱን ተሻግሬ ሄድኩኝ፤ እሱ ደንብሮ የት እንደገባ አላውቅም፡፡
በነጋታው ላፕ ቶፔን ይዤ ታሪኩን ለመፃፍ ወደ ወመዘክር ቤተ መጻህፍት የአማርኛ ክፍል ገባሁ። መተየብ ስጀምር ግድግዳው ላይ ያለው ስዕል ቀልቤን ሳበው። ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በትረ መንግስታቸውን ይዘው ከቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት በሶስት አንበሶች ተከበው ተቀምጠዋል። በስተቀኛቸው ሚዛን ከያዘች ሴት እግር ስር የወደቀች ሴት ትታያለች። ፍትህን ያመለክታል፡፡ ከስዋ በስተቀኝ ህፃናት እየተማሩ፣ ከነሱ ጀርባ የጦር ሰራዊት፣ በስተግራቸው መፅሐፍ የያዙ ሰው የወደቁ ሬሳዎችን እያዩ፣ ከነሱ በስተጀርባ ፈረሰኛ ጦር፣ በነሱ ትይዩ ታንኮች። ሰማዩ ላይ ክንፍ ያላቸው አጋንንት ክንፍ ባላቸው መልአክት በሰይፍ ሲጨረገዱ፣ ከሳቸው በስተግራ ሶስት ጥቋቁር እርኩስ አሞሮች፣ በስተቀኝ ሶስት አውሮፕላኖች።
ይሄ ሰውዬ የሚያወራው እውነት ነው እንዴ? ብዬ አሰብኩና ፅሑፌን ለመከተብ መረጃ መሰብሰብ ጀመርኩኝ። መረጃ አንድ፡- ሜጋ? ኮምፒዩተሩ መለሰ። አስር ቢሊዮን የብርሃን አመታት የሚርቅ ጋላክሲ ውስጥ ያለች ፕላኔት፡፡
“ጉድ አያልቅም” አልኩና
“አንድ የብርሃን ዓመት?” ጠየቅሁኝ፡፡
"ዘጠኝ ትሪሊዮን ስምንት መቶ ቢሊዮን ኪሎ ሜትር”

Read 1909 times