Saturday, 16 January 2021 10:37

ኢዜማ ለምርጫው መጠነ ሰፊ ዝግጅት እያደረኩ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  “የፀጥታ መደፍረስ ምርጫው ትልቅ አደጋ ነው”

              ቀጣዩ ምርጫ ለሀገሪቱ  ፖለቲካ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የገለፀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ ለምርጫው መጠነ ሰፊ ዝግጅት እያደረግሁ ነው  ብሏል። በሌላ በኩል፤ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ መደፍረስ የምርጫው ትልቅ አደጋ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
ቀጣዩ የ2013 ምርጫ ተቀባይነት ባለው ሂደትና ውጤት ሊጠናቀቅ የሚችልበት እድል ያለው መሆኑን፣ የህዝብ የምርጫ ፍላጎት ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበት መሆኑና በህዝብ ተቀባይነት ያለው መንግስት ሊቋቋም የሚችልበት ዕድል መኖሩ፤ ፓርቲው ቀጣዩን ምርጫ በበጎ እንዲመለከተው እንዳስቻለው አመልክቷል።
ለምርጫው ልዩ ትኩረት መስጠቱን ያስታወቀው ኢዜማ፤ ፖሊሲዎች መቅረጹን፣ እጩዎች መመልመሉን፣ የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ ማዘጋጀቱንና በምርጫ ህግጋት ዙሪያም አባላቱንና ደጋፊዎቹን ሲያሰለጥን መቆየቱን አብራርቷል፡፡
ሌሎች ፓርቲዎችም የምርጫ ህግጋትን አክብረው በመንቀሳቀስ፣ ምርጫውን የሃገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማዋለጃ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በመተከልና በወለጋ ያለው ያልተቋረጠ የዜጎች ጥቃትና የፀጥታ መደፍረስ በዋናነት በቀጣዩ ምርጫ ላይ አሉታዊ ጥላ ማጥላቱን ያመለከተው ኢዜማ፤ በትግራይ ክልልም በድጋሚ ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር ተቋቁሞ የተረጋጋ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል፤ መንግስት በትግራይ የህግ ማስከበር  እርምጃ ሲወሰድበት በነበረበት ወቅት የሌላ ሃገር ወታደሮች ድንበር አልፈው ስለመግባት አለመግባታቸው  ማብራሪያ እንዲሰጥም ኢዜማ ጠይቋል፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ተቋማት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ተመሳሳይ ጥያቄዎችንና ግምቶችን  ሲሰነዝሩ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

Read 1876 times