Saturday, 16 January 2021 11:13

ለብቻዬ ስንጥር ከምሆን ከሀገር ጋር እርፍ ልሁን

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ ልዑል ከቤተ መንግስት ራቅ ብሎ ወደ ሚገኝ አንድ ትልቅ ጫካ ሄዶ፣ አደን ሲያድን ውሎ በፈረሱ ወደ ቤተ መንግስት ሲመለስ፣ አንድ ባላገር ያገኛል፡፡ ባላገሩ ልዑሉ ማን እንደሆነ አያውቅም ነበርና አንዳችም እጅ ሳይነሳ፣ ሰላምታም ሳይሰጥ ዝም ብሎ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ልዑልም የባላገሩ ነገር ገርሞት፤
“ሰማህ ወይ ወዳጄ፤ ለመሆኑ እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቃለህ ወይ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ባላገሩም “በመንደራቸውን ባለው ጫካ ውስጥ በገዛ ፍቃድህ ገብተህ አደን ስታድን እንደቆየህ አይቻለሁ፡፡ በሰላም የተቀመጡትን አዕዋፋት ስታባርራቸው፣እንስሳትንም መጠጊያ ስታሳጣቸው የነበርከው ሰው መሆንህንም ተመልክቻለሁ” አለው፡፡
ልዑልም፤ ምን ስሰራ  እንደቆየሁ ፣ማወቅህ መልካም፡፡ ማንነቴንስ አውቀኸዋል ወይ?” ሲል ደግሞ ጠየቀው፡፡
ባላገሩም፤”አላውቅም” አለው፡፡
ልሑል “ንጉስ ማለት ምን ማለት እንደሆነስ ታውቃለህ ወይ?”
ባለገር፤”አላውቅም፡፡”
ልዑሉ፤ “እንግዲያውስ ና ፈረሴ ላይ ውጣና አብረን ወደ ከተማ እንሂድ፡፡ ንጉስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እዚያ ታውቃለህ” አለው፡፡
ልዑሉ ባላገሩን አፈናጦ ወደ ከተማ ይዞት ሔደ፡፡ በመንገድ ላይም “ንጉስ ማለት የተከበረ፣ በሄደበት ቦታ ሁሉ ህዝብ እጅ የሚነሳው፣ መንገደኛው ሁሉ ቆሞ የሚያሳልፈው ትልቅ ሰው”  አለው፡፡
ከተማ ሲደርሱ፣ ህዝቡ ልዑሉን ሲያይ እየቆመ፣ እጅ እየነሳ አሳለፈው፡፡ ግማሹም አቤቱታውን አሰማ፡፡
ይሄኔ ልዑል ወደ ባላገሩ ዞሮ “አሁን ንጉስ ማን እንደሆነ አወቅህ? ንጉስ ማን ይመስላል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ባላገሩም “እንግዲህ፤ ወይ እኔ ወደ አንተ መሆናችን ነዋ” ሲል መለሰ፡፡
“ቡመራንግ” ማለት ይሄ ነው -ለሌላው የወረወሩት ቀስት ተመለሶ ወደ ራስ!
ህዝቦችና መሪዎች ሲጠፋፉ የሚፈጠረው ግራ መጋባት አይጣል ነው! የክልል፣ የቀጠና፣ የወረዳና የቀበሌ መስተዳድር፣ የቢሮና የሚኒስቴር ኃላፊዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከህዝብ ሲርቁ ከላይ እንደተጠቀሰው ባላገር ማንነታቸው ብቻ ሳይሆን ምንነታቸውም ለህዝብ ግራ የሚገባበት ደረጃ ይደርሳል። ህዝቡ ልቡ ክፍት ነው። ህዝብ የነገሩትን ይሰማል። የተረጎሙለትን፣ እውነት ብሎ ይቀበላል። ያወጁለትን አዋጅ፣ ይበጀኝ ብሎ ያከብራል። የደነገጉለትን ህግ፣ በወጉ ሊተዳደርበት ይነሳል። ያወጡለትን መመሪያ አመራበታለሁ ብሎ ይስማማል። እቅዶች አምረው ሲያያቸው ሰምረው አገኛቸዋለሁ ብሎ ተስፋ ያደርጋል። ችግር የሚፈጠረውና ፀብ የሚመጣው፣ አንድም  በተግባር ሲተረጎሙ በመዛባታቸው፣ አንድም ባወጣቸው ክፍል በራሱ በቃ-አባይት እንደሌሉ ሲካዱ /ሲሻገሩ/ ነው። “Law-maker Law- breaker”   እንዲል ፈረንጅም። ያስቡልኛል ያላቸው መመሪያዎችና ኃላፊዎች “አንተና አንቺ” ብለው ከናቁት፣ ያወጡትን መመሪያዎች በሱው ላይ መጠቀሚያ ካደረጓቸው፣ በግልፅ ወገናዊነት “ሁሉም ህዝቦች እኩል ናቸው። አንዳንዶቹ ግን የበለጠ እኩል ናቸው” ካሉት፣ አዋጅም፣ ህግም፣ መመሪያም እንደ ብዙዎቹ ተግባር-አልባ የፕሮጀክት ጥናቶች ያማሩ ወረቀቶች ሆነው ነው የሚቀሩት።
እቅድ በስራ ላይ መዋሉን ለማየት በሚል “የግምገማ” ስብሰባ፣ ጥንት የሚታወቀው “ድርጅታዊ አሰራር” ከተንፀባረቀ፣ “በእኔ አስተያየት” በሚል የጠግል ካባ ቡድናዊ ስሜት የሚስተጋባ ከሆነ፣ አመራርና ተመሪ መራረቁ የማይቀር አባዜ ይሆናል። ህዝቡን በግማገማ ማረቅ አይቻልም! መሪዎችንና መመሪያዎችን እንጂ! እነሱንም በጄ ካሉ! ግምገማዎችም የእውነት ከሆነ! በአንድ ወቅት ስለ ሂስና ግለ-ሂስ ሲወሳ “ሂስ እያሉ ሌላውን መዘርጠጥ፣ ግለ-ሂስ እያሉ ራስን ማዋረድ አይገባም!” ያሉ እንደነበሩ ያስታውሷል። መታረም፣ መተራረም፣ መቻል፣ መቻቻል የሚችለው ትክክለኛ ሂስ ማቅረብ ሲቻል ነው። እዚህ ጋ ድክመት አለ ተብሎ ሲጠቆም ነው። እሱም ቢሆን በጨዋ ቋንቋ ኢትዮጵያዊ ባህልና ወጉን ሳይለቅ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሂስ የሚቀርብበትን ሰው ሳያንጓጥጡ ሃሳቡንና ጉዳዩ ላይ ብቻ በማተኮር በቀጥተኛ በማቅረብ፡፡ ህይወት “መካር- አሳስቶኝ”፣ “ፋርሽ-ባትሉኝ” የምንልበት የዕቃ -ዕቃ ጨዋታ አይደለም። መማማር ያስፈልጋል። ሆኖም ትምህርቱ መታወቅ፣ አስተማሪና ተማሪውም አስቀድሞ መለየት አለበት። ገጣሚው ኦማር ካህያም እንዳለው፤ እኔስ ማነኝሳ ቁጭ ብዬ እምማር “አንተ ማነህ እሱ የምታስተምር፣ ሳንባባል ለመቀጠልና ለመማማርም መቻቻል አለብን። አለበለዚያ አንድ አዋቂ የሀገራችን ፀሐፌ- ተውኔት ባንደኛው ቴያትራቸው ውስጥ እንደፃፉት ይሆናል። አንዱ ገፀ-ባህሪ
“ምነው ተጠፋፋን ጓድ”  ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓዱም ሲመለስ፤ “የአብዮት ጊዜ አይደለም እንዴ? መጠፋፋት መች ገደደ?!” ነበር ያለው፡፡ ይህን መሰል የፖለቲካ ሰዎች ፈሊጥ ህዝቡ ውስጥ እንዲገባ መደረግ የለበትም፡፡ ሕዝቦች እንዲኖሩ እንጂ እንዲጠፋፉ፣ እንዲቻቻሉ እንጂ፣ እንዲናቆሩ መሆን የለባቸውም፡፡ ቅን ልቦና፣ ፅናትና ለሀገር ማስበ ሲኖር መቻቻል ይቻላል፡፡ መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ መቻቻል ይችላሉ። ዋናው፤ “ለብቻዬ ስንጥር ከምሆን ከሀገር ጋር እርፍ ልሁን!” ማለት ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ “ህገ ወጥ አደን” ከሚል ማስታወቂያ በኋላ “አተረማመሰው” ይዘፍናሉ እንደተባለው ይሆንብናል፡፡


Read 13539 times